አዲስ ሪፖርተር – ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማለዳ በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ በመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አማካኝነት የተገነባውን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረቁት ይኸው ፕሮጀክት በዝናብ ውኃ ላይ የተመሰረተው የአካባቢውን የግብርና ልምድ የመቀየር አላማ እንዳለውና በአከባቢው ያለውን የገፀ ምድር ውኃ ሐብት በመጠቀም የመስኖ ግብርናን ለማቀላጠፍ እቅድ እንዳለው ታውቋል። ፕሮጀክቱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ፣ ስራ ላይ ሲውል ቢያንስ 9 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬትን የሚሸፍን መኾኑንና ለአከባቢው አርሶ አደሮች አስተማማኝ የመስኖ አቅርቦት ይሰጣል የሚል እቅድ እንደተያዘለትና ከ20 ሺህ በላይ የአከባቢውን አርሶአደሮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመረቁት የወልወል ወንዝን ልማት ፕሮጀክት በአካባቢው የውኃ አስተዳደር ተቋማት እንደሚደራጅለት የተገለፀ ሲኾን ዘላቂነት ያለው የውኃ (መስኖ) አጠቃቀም በመፍጠር መንግስት ለያዘው በምግብ ሉዓላዊነት የማስጠበቅ እቅድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል የሚል እምነት የተጣለበት መኾኑን በመረጃው ተጠቅሷል።
ፕሮጀክቱ፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳ ከመኾኑ በተጨማሪ በድርቅ የማይበገር ከባቢን ለመፍጠር ያለመ ሲሆን በቆላማ አከባቢዎች በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የውኃ ችግር ፕሮጀክቱ የመቅረፍ አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አማካኝነት የተጀመሩ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ የሚገኘውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረቁት ፕሮጀክት የመስኖ እርሻ ልማት ከዝናብ የተላቀቀ በማድረግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው ተብሏል።





