አዲስ ሪፖርተር – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው አገር ዓቀፍ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲደርግ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ የተቀናቃኝ ፓለቲካ ፓርቲዎች ሞግተውታል። ያነሱት መከራከሪያ የጸጥታ ጉዳይ ነው። በመከራከሪያቸው አጠቃላይ የጸጥታን ችግር ያንሱ እንጂ ቦታና ለይተው፣ ስም ጠቅሰው ምርጫ ማካሄድ የማይቻልባቸውን ስፍራዎች አላስታወቁም።
ቦርዱ ለምክክር በሚል የጠቅላላ ምርጫውን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ በአገሪቱ በይፋ የተመዘገቡትን ፓርቲዎች ሰብስቦ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ለውይይት ያቀረበው ምክረ ሐሳብ ከፓለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተቃውሞ እንደገጠመው የገለጹት በስብሰባው የተሳተፉ ናቸው። ተቃውሞውም በቀጣይ የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የመከናወን እድሉ እጅግ ጠባብ ይሆናል ከሚል ጥቅል መደምደሚያ ነው።
ቦርዱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረገው ምክክር ላይ ጋዜጠኞች አልተጋበዙም። ይህንኑ አስመልክቶ ከፓርቲዎቹ ተወካዮች ስሞታ ተነስቶ እንደነበር ስብሰባውን ከተከታተሉት መካከል ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል። ቦርዱ ኝ ይህ ገና ቅድመ ንግግር በመሆኑ ሚዲያ መጋበዙ ብዙም አስፈላጊ እንዳልሆነና ከስብሰባው በሁዋላ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት በሚፈልጋቸው መልኩ ለሚዲያ እንደሚያደርሱት የሚታወቅ በመሆኑ ሚዲያ ተገኘ አልተገኘ ብዙም ልዩነት የለውም ማለታቸው ተሰምቷል። እንደተባለውም ከስብሰባው መጠናቀቅ አፍታም ሳይቆይ ሚዲያዎች ጉዳዩን ተቀባብለውታል።
ቦርዱ ምክክሩን በዝግ ያደረገበት ምክንያት ለመጠየቅ አዲስ ሪፖርተር የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የእጅ ስልክ ላይ ደውሎ ነበር። ሰብሳቢዋ ለጊዜው በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይኾኑ ቀርተዋል።
የሕግ ባለሙያዎች እንዳሉት ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሱት ጥያቄ አግባብ ቢሆንም ቦርዱ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በአገሪቱ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ በራሱ መንገድ ካመነ የጊዜ ሰሌዳውን ያለ ምንም ምክክር ማሳወቅ እንደሚችል አስታውቀዋል። ይህን ማድረግ እየቻለ ውይይት መጥራቱን ፓርቲዎች በመጀመሪያ በበጎ ማየት ይኖርባቸዋል። ይህን አድርገው የጎደለ የሚሉትን ቢያቀርቡ፣ ስጋታቸውን ቢያስቀምጡ ግንኙነቱን ጤናማ ያደርገዋል ብለዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የፓለቲካ ፓርቲዎች ምክክሩ ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ ሆኖ እንዲከናወን የተደረገበው ውይይቱ ለሕዝብ ተደራሽ እንዳይሆን ተፈልጎ ነው ሲሉ ከሰዋል። ስብሰባው የመገናኛ ብዙሃን ባይገኙበትም፣ ሚስጢር አለመሆኑ እንዲያስረዱ ከጠየቅናቸው መካከል ሁለቱ ” ሚስጢር አይደለም ግን የመገናኛ ብዙሃን እንዲሳተፉበት አለመደረጉን አግብብ አይደለም ለማለት ነው” ብለዋል።
ስካይ ላይት ሆቴል በተደረገው ስልሳ የፓለቲካ ፓርቲ ኃላዎች የተሳተፉበት ሰብሰባ ቅሬታ የተስተናገደበት እንደነበር ከተሰብሳቢዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ገሚሶቹ የተስማሙበት ነጥብ በአገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል እድል ስለመኖሩ ስጋታቸውን ያቀረቡበት ነው።
በአገራቱ አሁን ላይ ባለው የፀጥታ ኹኔታ ምርጫ ለማድረግ አስተማማኝ አይደለም ከሚለው አንስቶ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ለፓርቲዎቹ ያስተዋወቀው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ለማስፈፀም ያለው አሁናዊ አቅም ውስንነት ዙርያ የፓለቲካ ፓርቲዎቹ በስፋት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ናቸው ተብሏል።
ምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳ 37 ተግባራት የሚከናወኑበት መኾኑን እና የጊዜ ሰሌዳውም በቀን እና በወራት ከፋፍሎ የቀረበ መኾኑን የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ የሚያትተው ሰነድ መመልከት ችለናል። ከነዚህ ነጥቦች አንዱ መራጮች በቴክኖሎጂ የታገዘ ራሳቸውን መመዝገብ የሚችሉበት ሁናቴ መዘጋጀቱን አንብበናል።
መራጮች በቴክኖሎጂ የታገዘ ራሳቸውን መመዝገብ የሚችሉበት አግባብ ተሞክሮ ስለማያውቅ፣ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰው ፓርቲዎቹ ቅሬታ እንዳቀረቡ ተሰምቷል። ከዚህም በተጨማ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ነው። አሁን ላይ የድርጅቶቹ እንቅስቃሴ ገደብ ያለበት እንደሆነ በስብሰባው ላይ ተነስቷል።
በነሐሴ ወር አጋማሽ የተጀመረው የምርጫ ታዛቢ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባም ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ እንደተጠናቀቀ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው ላይ አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ በተያዘው ጥቅምት ወር የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች በኩል ያለውን እንቅስቃሴ ስምንት ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን ባስተዋወቀው በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ዘርዝሯል።
ምርጫ ቦርድ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ያለውን የስራ ግንኝነት እንዳያሻሽል እና ለዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋፋት ከወዲሁ የሚጨበጥ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ከፓለቲከኞቹ በኩል መጠየቁንና የተቋማትን ተሳትፎ እግረ መንገዱ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መኾኑንና ኃላፊነቱ እንዲወጣ ተጠይቋል። ቦርዱ እንዲያስበበት የተጠየቀው ጉዳይ ዝርዝር እንዳልቀረበ ከተሳታፊዎች ለመረዳት ተችሏል።
በሌላ በኩል ከተነሱ አበይት ጉዳዮች አንዱ መገናኛ ብዙሐን የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሊያደርጉት የሚገባ እንቅስቃሴ እና የምርጫ ሒደቱ ላይ የሚኖሩ የዘገባ ነፃነትን ጨምሮ ለፓለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የአየር ሰዓት ድልድል ቦርዱ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ፣ አንዳንድ ፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አጥብቀው መጠየቃቸውን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
በዚሁ ምክክር ምርጫ ቦርድ የሰባተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮ ምርጫ የሚሆን ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ እንደሆነ በጊዜ ሰሌዳው ላይ መረዳት ችለናል።
ይሁንና ፒለቲከኞቹ በምርጫ ዝግጅቱ ላይ እስካሁን የተሰሩ ተጨባጭ ስራዎች አሉ ብለው የማያምኑ ፓለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውንና አጠቃላይ ለሰባተኛው አገራዊ ምርጫ የተደረጉ ዝግጅቶች በቂ እንዳልሆነ የሚገልፁ ፓርቲዎች እንደነበሩ በስብሰባው ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ፓለቲከኞች ለአዲስ ሪፖርተር ነግረዋል።





