ሰኞ , ታህሳስ 1, 2025

ባለቤት አልባ ውሾች አደጋ እያስከተሉ ነው፤ የማን መብት ይቅደም?

Date:

አዲስ ሪፖርተር – ነዋሪነታቸው አውሮፓ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ” እኔ ባለሁበት አገር አንደኛ ሴት፣ ሁለተኛ ልጅ፣ ሶስተኛ ውሻ፣ አራተኛ ወንዶች ነን …” ብለው በደረጃ እንዴት የክብር ቅድሚያ እንደሚሰጥ አብራሩ፤ ለዚህ መነሻቸው በአዲስ አበባ እንዳሻቸው የሚንጎራደዱትን ውሾች ነበሩ። በሚኖሩበት ኖርዌይ ውሻ ልዩ ክብር እንዳለው ገልጸው አንድ ውሻ ሰው ከነከሰ ግን እንደሚወገድ ተናገሩ። ሰው የሚነክስ ከሆነ ውሻ አይከበርም። ሰው እስካልነከሰ ድረስ የቤተሰብ አባል ነው። ሁሉም ነገር ልክ እንደ ሰው ይደረግለታል። ውሻ የሚወደደውና የሚከበረው ሰው እስካልነካና ባለቤቱ በተመዘገበ የህክምና ጣቢያ ጤናው ተጠብቆ ሲኖር ብቻ ነው።

እኚሁ እንግዳ የአዲስ አበባው የውሻ መንጋ ባለፉበት ባገደሙበት ሰላም ነስቷቸዋል። ብለከፍስ ብለው ፈርተዋል። ጥቁር አንበሳ ለጉዳይ ሄደው በርካታ ሰዎች በተልከስካሽ ውሾች ተነክሰው እንደሚመጡ ሰምተዋል። እናም ያረፉበት የቤተሰቦቻቸው ቤት የሚገኝበት መንደር ውስጥ የውሻ መንጎች ስላሉ በስጋት የፈለገ ነገር ቢሆን በእግራቸው አይሄዱም። እሳቸው እንደሚሉት የአዲስ አበባ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ተኝቷል።

አዲስ አበባ ውሻ አጥለቅልቋታል። የውሾች መብዛት መዘዙም እየከፋ ነው። ድሮ ድሮ በክረምት ብቻ የመራቢያ ድሪያ ያደሩ የነበሩት ውሾች አሁን አሁን ወቅት መምረጥ የሚባለውም ተፈጥሯዊ ጉዳይ የተውት ይመስላል። በየጎዳናው ለመራባት ሲረባረቡ ነው የሚታየው። በዓለማችን ላይ እጅግ ከሚወደዱ የቤት  እንስሳት መካለል ውሾች ተቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ብዙዎች በመኖሪያ ቤታቸው  እና በአካባቢያቸው ላይ ውሾችን አንድም ከሌባ እና መሰል ነገሮች እንዲጠብቋቸው አንደም  ካላቸው ፍቅር የተነሳ ውሻዎችን ያሳድጋሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን አዲስ አበባ የባለቤት አልባ ውሻ ቁጥር ከየትኛውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መጥቷል።እንደ አስተያየት ሰጪዎች ከሆነ የባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀርብም የአዲስ አበባን መልሶ ማልማትና የውሾቹ የራሳቸው ተፈጥሯዊ የመዋለድ ፍጥነት ለቁጥራቸው መጨመር ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡ አሉ።

የተለያዩ ጥናቶች ባስቀመጡት ግምት መሠረት፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በውሻ ንክሻ ምክንያት እስከ 97,000 የሚደርሱ ሰዎች ከውሻ ጋር ተያያዞ ለሚመጣ በሽታው ይጋለጣሉ።ይህ ማለት ከመቶ ሺህ ሰዎች መካከል ከ12 እስከ 137 ሰዎች ለበሽታው ተጋላጮች መሆናቸውን የሚያሳይ ስሌት ነው።  

በአዲስ አበባ ከተማም ችግሩ ሰፊ ነው። ለምሳሌ፣ ከ2015 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 9,592 ሰዎች በውሻ ንክሻ ምክንያት በኢትዮጵያ ህዝብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የድህረ-ንክሻ ክትባት (Post-Exposure Prophylaxis – PEP) ወስደዋል። ይህ በአማካይ በዓመት ከ1,000 በላይ ሰዎች በከተማዋ ህክምና እንደሚፈልጉ ያሳያል።

ሌላ ጥናት (2012-2016) በአዲስ አበባ በየ100,000 ሰው በአማካይ 46 ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆኑ አሳይቷል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ  በዓመት 2700 ሰዎች በዕብድ ውሻ በሽታ የሚሞቱ ሲሆን ይህም ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሃገር ያደርጋታል።

ቁጥሩ (2,700) በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC) እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የሚጠቀስ ግምት ነው። ትክክለኛው የሞት መጠን ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

የአማራ ክልል ጤና ኢንስቲትዩት በ2017 ባወጣው ሪፖርት ደግሞ በዓመት ከ8000 ሺህ ሰዎች በላይ በታመሙ ውሾች ይነከሳሉ። ይህ ካሉት የውሾች ቁጥር አንፃር የአዲስ አበባውም ከዚህ ጋር ተመጣጣኝ ቁጥር ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል።በሽታው በዓለም አሳሳቢና በገዳይነቱ የሚታወቅ ሲሆን አንድ ሰው የህመሙን ምልክት ካሳየ በ3 እና በ 4 ቀናት ውስጥ ወዲያው ሊሞት ይችላል። እንግዲህ አዲስ አበባና ነዋሪዎቿ ከዚህ አደገኛ የሞት ወረርሽኝ ጋር ነው ጎን ለጎን እየሄዱ ያሉት።

የሰርክ ስራውን ለመከወን  የሚሯሯጠው ነዋሪ ከውሾች ጋር በተያያዘ እየተፈጠረበት ያለው ጣጣ፣ የማህረሰብ ጤናና ቀውስ በየጊዜው እየጨመረ ያለውን አደጋ ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ ምን መላ ተበጅቷል በሚል ለሚነሳው ጥያቄ መልስ የለም።

በሚገርም ፍጥነት እየበዛ ያለውን የውሾች መራባት ሀይ ባይ የሚለው አካል እንደሚያስፈልግ የሚወተውቱ ያሉትን ያህል “ የውሾች መብት” በሚል ክርከር የሚገጥሙም እየተሰማ ነው። የአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሯቸው ዙሪያ ሳይቀር የውሾች መናኸሪያ መሆኑን የሚጠቁሙ የሚያቀርቡትም አሳብ አለ። አንዳንድ ጉዳዩ ያሳሰባቸውና በዘርፉ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ባለቤት አልባ ውሾችን ቁጥር ለመቀነስ ሁለት አማራጮች አሉ።

የመጀመሪያው ውሾችን  እየሰበሰቡ ወደ ማዕከል ማስገባት ውሻዎችን ማሳደግ ፈልገው ለሚመጡ ሰዎች መሰጠት ሲሆን ሁለተኛው የህክምና መንገድን ተጠቅሞ ውሻዎችን ማምከን መከተብ እና መመለስ CNVR (Collect, Neuter, Vaccinate, and Return)  ነው። ይህም ማለት ወንድም ሆነ ሴት ውሻዎችን ህክምናን በመጠቀም እንዳይወልዱ ማድረግ ነው ።

የባለቤት አልባ ውሾች በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች  ሀገራት ላይም ችግር ፈጣሪዎች ናቸው በአንድ ወቅት በባለቤት አልባ ውሾች ብዛት  ምክንያት ኔዘርላንዳውያን እጅግ ተቸግረው የነበረ ሲሆን   የውሾቹን ቁጥር ለመቀነስ የተጠቀሙበት ዘዴ  የህክምና መንገድ   CNVR (Collect, Neuter, Vaccinate, and Return)  ነው። በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ላይ ያሉ ባለቤት አልባ ውሾች ቁጠር ዜሮ በሚባል ደረጃ ወርዷል።

በቀደመው ጊዜ በሀገራችን  ባለቤት አልባ ውሾችን ለማስወገድ  ውሾችን በመግደል እንደ መፍትሔ የተወሰደበት ጊዜ ቢኖርም ይህ ድርጊት  የእንስሳቱን መብት የሚጋፋ እና ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እርምጃው እንዲቆም ከተደረገ ሰንብቷል።

ነገር ግን ይህ ድርጊት ከተከለከለ በኋላ  ባለቤት አልባ ውሻዎችን በተመለከተ የሚሰሩ ስራዎች ሙሉ ለሙሉ ቆመዋል ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ላይ ይገኛል። ይህ ስራ የሚመለከተው የከተማ ግብርና ቢሮ በዚህ ዙሪያ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አለመኖራቸው በየመንደሩ የውሻዎት ቁጥር  አሻቅቧል። እያደረሱት ያለው ጉዳትም ከፍተኛ ሆኗል።

በእነዚህ ውሾች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመመልከት ከሌሎች ሀገራት ልምድን በመቅሰም በሀገራችንም መሰል አይነት እርምጃዎች መውሰድ ግድ ነው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ አደጋው እየከፋ በመሄዱ የሚመለከታቸው ሁሉ አንድ ሊሉ ይገባል።

በማስተዋል ለዓይኔ


ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ 0981866434 

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related