አዲስ ሪፖርተር ብሔራዊ ባንክ እና የብሔራዊ መታወቂያ በጋራ ባወጡት አዲስ የአተገባበር ሥርዓት መሰረት የፋይናንስ ተቋማት ብሄራዊ ኦፕሬተር በሆነው ኢት-ስዊች በኩል ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የማስተሳሰር ሥራ መስራት መጀመራቸው ተገልጿል።
እስካሁን 10 የሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የማስተሳሰሩን ሥራ ጨርሰዋል ሲባል ሌሎች ባንኮች በሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይለበስ አዲስ ይህ አሰራር ባንኮች አገልግሎታቸው ቀልጣፋ እንዲሆንና ማዕከላዊ የመረጃ አያያዝ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። አክለውም ትስስሩ ባንኮች ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን አገልግሎት ያሳልጥላቸዋል፤ ወጪንም እንደሚቆጥብላቸው አመልክተዋል።
የኢት-ስዊች ቺፍ ፖርት ፎልዮ ኦፊሰር (CPO) አቤኔዘር ወንደሰን በበኩላቸው ከዚህ በፊት ደንበኞች አካውንት ሲያወጡ ባንኮች የደንበኛውን መታወቂያ ለማረጋገጥ ሁለት መቶ ብር በአንድ ሰው ክፍያ እንደሚጠበቅባቸው ለቲክቫህ ከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል።
በአዲሱ አሰራር ባንኮች ስንት እንደሚከፍሉ ተመን ባይወጣላቸውም ክፍያው ሲወሰን ከሀምሳ ብር እንደማይበልጥ አስታወቀዋል። ይህም ባንኮችን ከበርካታ ወጪ እንደሚያድናቸው ተናግረዋል። አቶ አቤኔዘር ባንኮች እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ ጥምረት አድርገው መጨረስ እንዳለባቸውም አታወቀዋል።
በአሰራሩ ባንኮቹ ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በቀጥታ ትስስር አይኖራቸውም። በጥምረቱ ትስስር የሚኖራቸው በኢት-ስዊች በኩል ነው።
ኢት-ስዊች ሁሉንም ባንኮች ያስተሳሰረ ስለሆነ ብሔራዊ መታወቂያ ከኢት-ስዊች ጋር በመቀናጀት ሁሉንም ባንኮች በአንድ ጊዜ ማግኘት ይችላል።
የባንክ አካውንት ሲከፈት ባንኮች የብሔራዊ መታወቂያ ቁጥሩን ወደ ኢትስዊች ልከው ኢት-ስዊች ባንኩ ስለደንበኛው የሚያስፈልገውን መረጃ (KYC) ከብሔራዊ መታወቂያ ተቀብሎ ለባንኮቹ መልሶ ይልካል።
የብሔራዊ መታወቂያ የጣት አሻራን በክፍያ ወቅት እንደ ይለፍ ቃልም መጠቀም እንዲቻል አሁን ላይ የተጀመሩት ትስስሮች እንደሚያግዙም ተጠቅሷል።
ኢት-ስዊች የፋይናንስ ሪፖርቱን በቅርቡ ሲያቀርብ በባለፈው በጀት ዓመት፥ ጠቅላላ ገቢው 2.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሶ ከታክስ በፊት 1.42 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ34% ጭማሪ ማሳየቱን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





