አዲስ ሪፖርተር – በአማራ ክልል የእብድ ውሻ በሽታ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንና በዚህም ሳቢያ በየሳምንቱ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች በበሽታው እንደሚጠቁ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ለአዲስ ሪፖርተር ገልጿል። በሽታው ለክልሉ ከታጠቁ ኃይሎች ተጨማሪ ሌላ ቀውስ እንደሆነ ነዋሪዎች አመልክተዋል።
የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር መጨመር መንስኤዎች ውስጥም የክልሉ ነባራዊ የፀጥታ ሁኔታ፤ሕብረተሰቡ ውሻን አስከትቦና በግቢ ውስጥ አስሮ መያዝ ብዙም ትኩረት ስለማይሰጠው ውሾቹ ለበሽታ በመጋለጣቸውን በኢንስቲቲዩቱ የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ የሙያያተኞች ቡድን ሰብሳቢ አቶ ሐብታሙ አለባቸው ናቸው ለአዲስ ሪፖርተር የተናገሩት። አዲስ ሪፖርተር የባለቤት አልባ ውሾች መስፋፋት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሶ ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባን ችግር ግዝፈት ማስታወቁ አይዘነጋም።
ኃላፊው እንዳሉት በክልሉ ውሻን በግቢ ውስጥ አስሮ መንከባከብ እምብዛም አልተለመደም። በተጨማሪም በነዋሪዎች ዘንድ፤ውሾችን ማስከተብ ፣ማሰር እና መጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ አይደለም ብለዋል፡፡ በክልሉ ካለው የፀጥታ ችግር ተዳምሮ በርካታ እብድ ውሾች በከተሞች ሳይቀር እንዲበራከቱ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡ ባለቤት አልባ ውሾች በመንጋ ስለሚንቀሳቀሱ አንዱ ከታመመ ሁሉም የመበከል እድላቸው ሰፊ በመሆኑ አደጋው አስከፊ እንደሆነ አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያ አስረድተዋል። አክለውም የተነከሰ ሰው ከ90 በመቶ በላይ በሽተኛ ሊህፕን እንደሚችል በመጠቆም ወዲያ ወደ ሕክምና መሄድ እንደሚገባ አመለክተዋል።
“በዕብድ ውሻ የተጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ጤና ተቋም የመሄድ ልምድ ዝቅተኛ መሆን በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጐታል” ሲሉ የችግሩን ግዝፈት አሳይተዋል። ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በክልሉም ሆነ በአገራችን ትኩረት ያልተሰጠው ትልቁ የህብረተሰብ የጤና ችግር መሆኑን የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ ሲሉ ገልጸዋል። በአገር ዓቀፍ ደረጃ ችግሩን አስመልክቶ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም ዓቀፍ ሕጎች ቀደም ሲል የተለመደውን እርምጃ ለመውሰድ ከልካይ መሆናቸውን ባለሙያዎች አስረድተዋል።
በሽታው በሰው ላይ ምልክት ካሳየ ሙሉ በሙሉ ገዳይ የሆነ፣ ነገር ግን ምልክት ከማሳየቱ በፊት በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ክትባቱን በመከተብ ሙሉ በሙሉ ከበሽታው መዳን እንደሚቻል ኃላፊው አስታውቀዋል። ኃላፊው ችግሩ አመላክተው መፍትሄ ለማበጀት ያልተቻለበትን ምክንያት ሲያብራሩ ” መፍትሄ የመፈለጉ ጉዳይ ከኢንስቲትዩቱ አቅም በላይ ነው” ብለዋል። ባለቤት አልባ ውሾችን በዘመቻ በመከተብና በማስወገድ ችግሩን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። በጅምላ ማስወግድ ያሉትን ግን አላብራሩም።
ሕብረተሰቡ ውሾቹን እንዲያስከትብ፣ በአግባቡ እንዲንከባክብና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲስፋፉ በማድረግ፤ በሽታውን በመከላከል ረገድ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑንም ጎን ለጎን ጠቁመዋል።
በበሽታው የተጠቁ ግለሰቦች ወደ ጤና ተቋማት በፍጥነት መሄድ እና ሕክምና መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ጤና ተቋም እስኪደርሱ ጉዳት የደረሰበትን የሰውነት ክፍል በውሃና በሳሙና መታጠብ እንደሚገባም ጨምረው አስገንዝበዋል፡፡
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





