በውጭ ምንዛሪ ሸፍጥ 112 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፤ 519 የባንክ ሂሳብ ታገደ

Date:

አዲስ ሪፖርተር – አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ በቅርቡ የውጭ ምንዛሬን በሕገወጥ የሚያዘዋውሩ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው ነበር። በዚሁ ማሳሰቢያቸው መንግስት በቂ መረጃ እንዳለው አመልክተው እርምጃ እንደሚወስድም ግልጽ አድርገው ነበር። ዛሬ እንደተሰማው አንድ መቶ አስራ ሁለት “ ሕገ ወጥ” የተባሉ የውጭ ምንዛሬ አሻሻጮች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በተቀናጀ መንገድ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው 112 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና 519 የባንክ ሂሳብ መታገዱን ያመለከተው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ነው። አገልግሎቱ እንዳለው ዘመቻው ሚስጢራዊ ነበር።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሚዲያዎች ባሰራጨው መረጃ እንዳለው መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጻረር በተደራጀ መንገድ በሚፈጽሙ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮች ዙሪያ በተቀናጀ መልኩ ምስጢራዊ የመረጃ ስምሪት ሲከናወን ቆይቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል የፀጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ ጥቆማ በተደረገ የተቀናጀ ሥምሪት በፋይናንስ አሻጥር የተሰማሩ 112 ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ከሕገ ወጥ ተግባሩ ጋር ትስስር የነበራቸው 519 የባንክ አካውንቶች የታገዱ ሲሆን፣ የተለያዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውም ተጠቅሷል፡፡

ሕገ ወጥ ሃዋላዎች ፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራዎች ፣ የግብር ስወራዎች፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰልና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችንና የታጠቁ ቡድኖችን ለመደገፍ ሲውሉ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በተለይም ሕገ ወጥ በሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፣ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፣ ሕገ ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች፣ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈፀሙ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ አካላት የማያዳግም ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱ ተጠቁሟል፡፡

በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በሚጥስ ሁኔታ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ የቆዩ ሕጋዊ ፈቃዳቸው በፈጸሙት ተደጋጋሚ ጥፋት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰረዘባቸው ዓለም አቀፍ የሃዋላ አስተላላፊዎችና ሕገ ወጥ የሃዋላ ድርጅቶችም ርምጃው የተወሰደባቸው ናቸው።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሀብትን ከሀገር በማሸሽ ላይ ያሉ ድርጅቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካለት ላይም ርምጃ ተወስዷል፡፡

በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ላይ በማነጣጠር ሲፈጸም የነበረው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማስተጓጎል፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ በተቀናጀ መንገድ ሲፈጽሙት እንደነበረ ነው የተገለጸው፡፡

የሀገርን ደኅንነት ስጋት ላይ በሚጥሉ እና የሀገርን ኢኮኖሚ በሚጎዱ አሻጥሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በመከታተል የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡ መላው ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰል ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር ባልተፈቀዱ የውጭ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተቀናጀ ርምጃ መውሰድ መጅመሩን፣ ርምጃው እንደሚቀጥል አመልክቷል።

ባንኩ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት በመጠቀም ድንበር ዘለል የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባራትን በሚፈጽሙ ደላሎችና ገንዘብ አቅራቢዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድን የሚያካትት እንደሆነ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

እየተወሰደ የሚገኘው ርምጃ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓት ተአማኒነትን ለመጠበቅና የውጭ ምንዛሪ ፍሰት በሕጋዊ፣ ግልጽና መደበኛ በሆኑ መንገዶች መከናወኑን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ ነው።

ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመፈጸም መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓትን መጠቀም የውጭ ምንዛሪ ገበያን ተአማኒነት የሚያኮሰስና የሀገሪቱን የገንዘብ ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ እንደሆነ በማንሳት የማስተካከያ ርምጃዎቹ ሕገ ወጥ የሐዋላ ዝውውርን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት አካል መሆናቸውን አብራርቷል።

ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ላልተገባ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላትን በመለየት ተገቢ ርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

አንዲሁም ባንኩ የውጭ ሐዋላ ፍሰት መደበኛ አካሄድን ተከትሎ አንዲፈጸም የሚረዱ ርምጃዎችን ለማጠናከርና በባንኮችና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የገንዘብ አስተላላፊዎች አማካይነት በቂና ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩን ለማረጋገጥ ተግቶ ይሠራል ነው ያለው፡፡

እነዚህ የባንኩ ጥረቶች የሐዋላ ፍሰት ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በሆነ መንገድ አንዲፈጸም ለማድረግና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋትና የልማት ግቦች ለማሳካት የታለሙ ናቸው፡፡

ሕዝቡ ሕጋዊ የውጭ ሐዋላ አገልግሎት አቅራቢዎችን ለይቶ ማወቅ ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግን ተከትለው በውጭ ምንዛሪ ገበያ አንዲሳተፉ የተፈቀደላቸውን የሐዋላ አስተላለፊ ድርጅቶች ስም ዝርዝር በድረ ገጽ አድራሻ https://nbe.gov.et/mta/ ማግኘት ይችላል፡፡

ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ኃይሌ ገብረስላሴ “አረቄን እጠቀም ነበር” በማለቱ ዕግድ ተጣለበት፤ እግዱ ለዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ማህበራት ተበትኗል

አዲስ ሪፖርተር - አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አረቄን ከዶፒንግ ጋር...

“የኢትዮጵያዊያ መከራ የሆነውን ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያና ትግራይ ምድር መንቀል ዋና ዓላማችን ነው”

አዲስ ሪፖርተር - እስካሁን በመላው ኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ምስቅልቅሎች፣ በትግራይ...

የአማራ ክልል የወሲባዊ ጥቃት አሳስቧል፤ “በማንና እንዴት ይፈጸማል? ለሚለው በጥናት የተረጋገጠ መረጃ የለም” ጤና ቢሮ  

አዲስ ሪፖርተር - በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለው ጦርነትና...

በሻዕቢያና ህወሃት መካከል አለመተማመኑ ሰፍቷል፤ የሚታወቁ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ከእነ ሞንጆሪኖ ቡድን እየወጡ ነው

ስጋት ትልቁ ምክንያት ነው። ሻዕቢያ በተግባር የተፈተሸ ከሃጂ በመሆኑ...