አዲስ ሪፖርተር – በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለው ጦርነትና አለመረጋጋት ሳቢያ በተለያዩ የኧድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ለጾታ ጥቃት ያላቸው ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ለአዲስ ሪፖርተር ገልጿል። አስገድዶ መድፈር ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ቢጨምርም ባምንና እንዴት እንደሚፈጸም ለማረጋገጥ በጥናት የተደገፈ ማስረጃ እንደሌለ አመልክቷል።
በክልሉ በተለይም ወሲባዊ ጥቃት ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የሕክምና ፣የስነልቦና ድጋፎች ለመስጠት የጤና ባለሞያዎች አለመቻላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት የታጠቁ ኃይሎች ባለሞያዎችን የመንግስት አጀንዳ አስፈፃሚ አድርገው በማሰባቸው እንደሆነ በቢሮው የሴቶች ሕፃናት ጉዳይ ክፍል አስተባባሪ ትዕግሥት ብሩ ለአዲስ ሪፖርተር አመልክተዋል።
አስተባባሪዋ ወቅታዊ ሁኔታን መሠረት አድርጎ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ በተለይም ወሲባዊ ጥቃትን ከመከላከል አንፃር ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ገልጸዋል። “ጥቃቱ በማንና እንዴት ይፈጸማል” በሚል የሚታውቅ መረጃ ካለ በሚል አዲስ ሪፖርተር ለተየቃቸው አስተባባሪዋ “ጥቃቱን የሚያደርሱ አካላት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ቢሮ የተለያዩ ጥናት ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ የተጠናቀቀ ጥናት አለመኖሩን፣ የተጀመረውም ጥናት በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡን ጠቁመዋል።
በጥናት ሳይደገፍ፣ በቂ መረጃ በባለሙያ ሳይሰበሰብና አግባብ ያለው ምርመራ በነጻነት ባልተከናወነበት ሁኔታ ውስጥ አንድን አካል ላይቶ “አብዛኛውን ጥቃት አድራሽ ነው” ብሎ ለመናገር ከሙያም ሆነ ከአሰራር አንጻር አግባብ አለመሆኑን አስተባባሪያዋ አስረድተዋል።
በዋናነት ቢሮ በወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን በአፋጣኝ ሕክምና መስጠት እንጂ ጥቃት ያደረሰባቸው አካል ማንንነት መለየትት ላይ ትኩርት ማድረግ ቀዳሚ መርህ እንዳልሆነ አስተባባሪዋ አመልክተዋል። መረጃ በመስተት ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አምልክተው በይበልጥ የማጣራት ስራ የሚያከናውነው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽ እና የፍትህ ቢሮ እንደሆነ ገልጸዋል።
የጥቃቱ ሰለባ ያልሆኑትን የመከላከል፣ የመጠበቅ እንዲሁም ጥቃት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እና እንክብካቤ የመስጠት ሥራ ቢሰራም በቂ አለመሆኑን ከአስተባባሪዋ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። ለዚህም ምክንያቱ በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ እንደሆነ አመልክተዋል።የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ረገድ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ሴቶች በግጭት ውስጥ ሁሌ ግንባር ቀደም ተጠቂ በመሆናቸው ሊታዘንላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
አያይዘውም፤ ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል ረገድ የህብረተሰብ አመለካከት ለውጥና ወንዶችን ያማከለ ሥራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ተለይተው በሕግ የሚጠያቁበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀኢትዮጵያ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ሕጎች እና ፖሊሲዎችን ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች መሆኑ መዘገባችን የሚታወስ ነው።
በክልሉ በነጻነት መንቀሳቀስና ሙያዊ የምርመራና የማጣራት ስራ ሳይካሄድ ከሩቅ ሆነው መረጃ የሚሰጡ አካላት ፍትህ እንዲዛባ አስተዋጾ ከማድረግ የዘለለ ትርጉም ያለው ስራ ሊሰሩ እንደማይችሉ ከዚህ በፊት ሁሉንም ጉዳይ ፖለቲካ በማድረግ የተሰሩ ስህተቶችን የሚያነሱ ወገኖች በተደጋጋሚ ምክር እየሰጡ ነው።
በቅርቡ ትህነግ ያዋቀረው ቡድን በትግራይ ተፈጸም ስለተባለ ጄኖሳይድ ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ “ ራሱ በወንጀሉ የሚጠረጠር ቡድን ራሱ አጣሪ ሆኖ ያቀረበውን ሪፖርት ያጯጯሁ ሚዲያዎች ሊያፍሩ እንደሚገባ አቶ ጠዐመ ለአዲስ ሪፖርተር መናገራቸው ይታውሳል። በወንጀሉ የሚጠረጠር ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት ማራገብ አንድም ተአማኒ አይደለም፣ ሲቀጥል የተበዳዮችን የፍትህ ደጅ መዝጋትም ጭምር እነደሆነ አመልክተው፣ ትልልቅ ጉዳዮችን በስሜት ለፖለቲካ ማገዶነት መጠቀም ከሞራል አንጻር ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም አምልክተው ነበር።





