አዲስ ሪፓርተር ጆሃንስበርግ ፡- ይህ ሳምንት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬቶች የተመዘገበበት እንደሆነ ተገለፀ። ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ የማሌዠያን ጠቅላይ ሚንስቴር በመቀበልና በማስተናገድ የሁለቱን ሃገራት ሁለትዮች ግንኙነት ስለሚጠናከርበት ሁኔታ በመምከር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ስለሚሰሩበት ሁኔታ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። በጥቅሉ ከጉባኤው ጎን ለጎን የታየው የዲፕሎማሲ ስራ “ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ኮሰመነች ለሚሉት ትልቅ መልስና ሃፍረት ሆኗል” ተብሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 (G20) ጉባኤ ላይ እንደተጋባዥ ሃገር መሳተፏ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን ስኬት የሚያሳይ የሚያሳይ ነበር። ይህ ተሳትፎ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞችን እንድታስከብር እና ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እንደሚከፍትላት የአፍሪካ ቀንድ የጂኦፓለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ምስከር አቢይ ለአዲስ ሪፓርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ ምስክር ኢትዮጵያ የቡድኑ ቋሚ አባል ባትሆንም፣ በጉባኤው ላይ መገኘቷ ዓለም አቀፍ መድረክ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቃሚ ሃገር መሆኑዋን ያሳየ ሲሆን የብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማራመድ ጥሩ መድረክ ፈጥሮላታል ብለዋል። ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸውን ሃገራት አንድ ላይ የሚያገናቸው ይህ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ገፅታዋን ዳግም ለመገንባት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድትፈጥር እድል ፈጥሮላታል።

የአፍሪካ አጀንዳ መሪነት ሚና መወጣት
በዲፕሎማሲው መስክ፣ ኢትዮጵያ በቡድን 20 ሃገራት ጉባኤ ላይ መሳተፏ በርካታ ቁልፍ ጥቅሞችን አስገኝቷል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከምዕራባውያን ከፍተኛ ጫና ገጥሟት የነበረ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ መገኘቷ ይህን ግንኝነቷን ይበልጥ ለማጠናከር የስቻለ ምሳሌያዊና ተጨባጭ እርምጃ ሆኗል። ከዓለም መሪዎች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ መቀመጥ በጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አሕመድ የሚመራው የኢትዮጵያ ልኡክ የሃገራችንን ጥቅማነ ፍላጎት በቀጥታ እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል፣ ይህም ይበልጥ ገንቢና ሚዛናዊ የሆነ ውይይት እንዲፈጠር ረድቷል። በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ክብደት ያላትና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ መድረኩን በመጠቀም አህጉራዊ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማንፀባረቅ ችላለች። ከእነዚህም መካከል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ማሻሻል፣ ለታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ፋይናንስን ማሳደግ እና ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የንግድ ልምዶች አስፈላጊነትን በጉባኤው አንፀባርቃለች። በዚህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ግንባር ቀደም ድምፅ በመሆን አህጉራዊ መሪነቷን አሳይታለች።
የሁለትዮሽ ግንኙነቶች እንደ ማጠናከሪያ መድረክ
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ከጉባኤው ጎን ለጎን ወሳኝ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ስብሰባዎችን አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከኃያላን ሀገራት መሪዎች፣ የብሪክስ (BRICS) አባል ከሆኑትና ከተለመዱት ምዕራባውያን አጋሮች ጋር አስፈላጊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ዕድሉን ተጠቅመዋል። እነዚህ የጎንዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር፣ በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ አቋሞችን ግልጽ ለማድረግ እና ለሰላም እና ልማት ተነሳሽነቶች ግንዛቤ ለመፍጠር ወሳኝ እንደነበር መረዳት ይቻላል። በተጨማሪም ጉባኤው ከሌሎች ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሃገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ምቹ መድረክ ሆኖ አገልግሏል። እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ብራዚል እና አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪካ ካሉ ሀገራት ጋር የተደረገው የጎንዮሽ ውይይት የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ ግብ በማሳካት ረገድ ወሳኝ ሲሆን፣ አጋር ሃገራትን በማስፋት በአንድ ወገን ላይ ብቻ ጥገኛ መሆንን ለመቀነስ አስችሏታል።
የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ እድሎች
የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎቹ ከሚጨበጡ የኢኮኖሚ ተስፋዎች ጋር ቀጥተኛ ትስስር ነበራቸው። የኢትዮጵያ ልዑካን በፖለቲካዊ ንግግሮች ከመወሰን ባለፈ ሃገሪቱ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኑዋን ለማስተዋወቅ በንቃት ተጠቅመውበታል። በቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኢነርጂ፣ ሎጅስቲክስ እና በማኑፋክቸሪንግ የኢንቨስትምነት ዘርፎች ያሉትን ሰፊ እድሎች አስተዋውቀዋል። ይህም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) ምቹ ሁኔታ በር ከፋች ነበር። ከዚህም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ከተገኙት ቁልፍ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ባንክን ጨምሮ፣ ጋር ውይይት አድርጋለች። እነዚህ ውይይቶች በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና ለኢኮኖሚያዊ መረጋጋት በጣም አስፈላጊ የሆኑትን የገንዘብ ድጋፍ፣ የዕዳ ማዋቀር ዝግጅቶችን እና ለመሠረተ ልማትና ለማህበራዊ ፕሮግራሞች አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ወሳኝ እንደነበሩ ተገልጿል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ በቡድን 20 ጉባኤ መሳተፏ ከትዕምርታዊ ምልክትነት እጅግ የላቀ ነበር። ግልጽ የሆነ ጥቅም ያስገኘ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነበር። በዲፕሎማሲው ረገድ፣ ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነቷን ለማደስ፣ የአፍሪካ አጀንዳ ቀራጭነትና መሪነቷን ለማጠናከር እና አዲስ የዲፕሎማሲ የግንኙነት በሮችን ለመክፍት አስችሏታል። በኢኮኖሚው በኩል ደግሞ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ፋይናንስን ለማፈላለግ እና ንግድን ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል። እንዲሁም ጉባኤው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ተዋናይ እና በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የራሷ ድርሻና ሚና እንዳላት በግልፅ አሳይቷል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





