አዲስ ሪፓርተር አዲስ አበባ – በኢትዮጵያ አፋር ክልል የሚገኘው ሃይሊ ጉቢ (Hayli Gubbi) የተባለው እሳተ ገሞራ፣ እስከ 12,000 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈንድቶ ከፍተኛ የአመድ ደመና ወደ ከባቢ አየር ልኳል። ባለው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ዕለት ፍንዳታውን የጀመረው ይህ እሳተ ገሞራ እስከ 15 ኪሎ ሜትር ከፍታ ድረስ አመድ እና ሰልፈር ዳይኦክሳይድ (Sulfur Dioxide) ወደ ከባቢ አየር መልቀቁን የአውሮፓ ሕዋ ምርምር ኤጀንሲ በድህረ ገፁ ከለቀቀው የሳትላይት ምስል መረዳት ችለናል።

በአካባቢው ምንም ዓይነት የሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ የደረሰ አደጋ ሪፖርት ባይኖርም፣ አመዱ በአካባቢው የሚኖሩ የአፋር አርብቶ አደሮችን የከብቶች ግጦሽ አካባቢ ሊጎዳ እንደሚችል ተገልጿል።
የእሳተ ገሞራው አመድ ደመና በከፍተኛ የአየር ግፊት በመታገዝ ከ4,300 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ የየመን፣ የኦማን እና ሰሜናዊ ፓኪስታንን የአየር ክልል አቋርጦ ወደ ህንድ ደርሷል።
አመዱ ህንድ የገባው በራጃስታን በኩል ሲሆን፣ ሰኞ ምሽት ላይ ወደ ዴልሂ-ኤንሲአር፣ ሃርያና እና ፓንጃብ ግዛቶች አየር ላይ ሊንሳፈፍ ችላል። ይህ ክስተት በህንድ የአየር ትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሯል፤ በርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲሰረዙና እንዲቀየሩ ምክንያት እንደሆነ እየተዘገበ ይገኛል። ለምሳሌ ኤር ኢንዲያ (Air India) እና ኬኤልኤም ሮያል ደች አየር መንገድ (KLM Royal Dutch Airlines) በረራዎችን ሲሰርዙ፣ የህንድ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክቶሬት (DGCA) አየር መንገዶች አመድ የበከለውን የአየር ክልል እንዲያስወግዱ አስቸኳይ የደህንነት ማስጠንቀቂያ አውጥቷል ።

እሳተ ገሞራው በአፋር ስምጥ ሸለቆ (Afar Rift) ውስጥ የተከሰተ ሲሆን፣ ይህም ሶስት ቴክቶኒክ ሳህኖች የሚገናኙበት እና ከዓለማችን እጅግ ንቁ የጂኦሎጂ አካባቢዎች አንዱ ነው። የአመዱ ደመና በከባቢ አየር ከፍታ ላይ (በ15,000 እና 45,000 ጫማ መካከል) በመገኘቱ ፣ በህንድ ውስጥ ባለው የአየር ጥራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አላደረሰም ተብሏል። የህንድ ሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት (IMD) ማክሰኞ ምሽት ላይ የአመድ ደመናው የህንድን የአየር ክልል ሙሉ በሙሉ ለቆ ወደ ቻይና መጓዙን አስታውቋል ። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎች ተጨማሪ ፍንዳታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመግለጽ ፣ ሁኔታው ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተደጋጋሚ የእሳተ ጎሞራ ስንዳታ የሚከሰትበት ይህ አካባቢ ዘወትር ፊታቸው ድኝ በሚባለው አዋር ተሸፍኖ እንደሚታይ በዛው አካባቢ የሚሰሩ ይናገራሉ፤ ይህ ኃይለኛ መርዝ የሚያስከትለው አደጋ የከፋ በመሆኑ ነዋሪዎችን አስምኖ ወደ ሌላ አካባቢ ማስፈር ግድ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
tiktalk – https://www.tiktok.com/@addisreporter3
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





