አዲስ ሪፖርተር – የታላላቅ አገራት የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ የሚያመለክተው የአገራቱ ባለስልጣናት በሄዱበት፣ በተጋበዙበትና በሚሳተፉባቸው መድረኮች ላይ መርሃቸው ሁሉ አንድና አንድ ነው። እሱም የብሄራዊ ጥቅማቸው ባሪያ መሆን ነው። አገራዊ የአመራርና የዓላማ አንድነትን ማስጠበቅ፣ የታቀደ፣ የተናበበ፣ ከዋናው የአገርቱ ብሄራዊ ጥቅም ብቻ የተቀዳ፣ አቋም ማራመድ ቀዳሚ ተግባራቸው ነው። ከዚህ ውጭ በሄዱበት፣ ባለፉበት፣ ባገደሙበት፣ ተቀርጾ ከሚሰጠው ውጪ ሲዘባርቁ አይታዩም። በየአደባባዩና በተገኘው መድረክ ሁሉ ከኪሳቸው እያወጡ እንዳሻቸው ሲተፉና አገራቸውን ሲያራክሱ አይስተዋሉም። ይህ በቁጥጥር የሚደረግ ሳይሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ራስን በመግዛት የሚያደርጉት ነው፡፡ ከዚህ ፈቀቅ ማለት ስልጣንም ክብርም ያሳጣቸዋል። ስህተት እነደሰሩ ሲያምኑም “በቃኝ” ይላሉ፤ አቶ ጌታቸውስ?
ይህ ያነሳነው በአገራችን ይህ አካሄድ ካለን ደካማና ሊሻሻል ያልቻለ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ አንጻር አገርና የሚሰሩ መሪዎችን ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ ነው። የዛሬው ደግሞ ጭራሽ የባሰ ነው። በበረሃና የጫካ የፕሮፓጋንዳ ልቡና … እስኪ እናብራራው።
በቅርቡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያስመዘገበችው ስኬት በተለይም በቡድን 20 ሃገራት ጉባኤ ላይ ያገኘችው ተሳትፎ እና የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) አስተናጋጅ ለመሆን መመረጧ እጅግ የላቀ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ስትራቴጂካዊ ተግባር ነበር። ስኬቱም እንዲሁ እንደ ሾላ ፍሬ ዱብ ያለ ሳይሆን ብዙ የተደከመበት ነው።
ይህ ክስተት ሃገሪቱ ከጦርነት እና ከግጭት አገግማ ወደ ዓለም አቀፉ መድረኮች ወደፊት በመምጣት የአፍሪካ ድምፅ በመሆን መሪነቷን ያሳየችበትም ነው። መልካም ስሟን በማደስ በሯን ለንግድና ኢንቨስትምነት በመክፈት የብልፅግና ጉዞዋን ለማሳለጥ የሚያስችላትን ምቹ ሁኔታ ያገኘችበት ነበር።
ይህ የዲፕሎማሲ ስኬት ለሀገር ብልጽግና ሊፈጥር የሚችለውን ፋይዳ በሕዝብ ግንኙነት ሥራ በሕዝቡ ዘንድ በማስረጽ፣ ትኩረቱ ሰላምና ልማት ላይ መሆን እንዳለበት ማስገንዘብ ሲገባ፣ በሆይ ሆይታ እንደዋዛ ታልፏል። ይህ የሕዝብ ግንኙነት ስራ ላይ ወገብን ጠበቅ አድርጎ መስራት ላይ ጉዳለት እንዳለ ማሳያ ነው። ይህ የሕዝብ ግንኙነቱ ስራ የላይኛውን የአገሪቱን መሪዎች አካሄድ በማስላት በመናበብ፣ በፖለቲካ ብቃት፣ በዕውቀትና በትጋት፣ እንዲሁም በከፍታና በፍጥነት የሚሰራ እንጂ በቅኔና በተረት የሚደገፍ የጅምላ ስራ አይደለም።
እንዲህ ያሉ ከፍተኛ ተግባራት በተፈጸሙበት ማግስት፣ የስኬቶቹን ዝርዝር ሕዝብ በወጉ እንዲረዳና እንዲከተል ማድረግ ሲጠበቅ በተቃራኒ ሌሎች ሆነ ብለው በደገሱት ድግስ መዋኘት ግድ ሆኗል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ሎንዶን ተገኝተው፣ በሚታወቁ የኢትዮጵያ ጠላቶች ታጅበው ከአልጃዚራ ጋር የተናዘዙት ኑዛዜ ሰሞኑን ኢትዮጵያ ያሳካችውን ታላላቅ ስኬቶች ማደብዘዣ ይሆን ዘንድ ሆነ ተብሎ የተሰራ ስለመሆኑ ዝግጅት ክፍላችን ጥርጥር የለውም። አቶ ጌታቸው ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ ለማማማት ወደ ሎንደን የተጓዙት በመንግስት ወጪ ይሁን በአዘጋጆቹ ግብዣ መረጃ ባይኖረንም፣ አብረዋቸው የነበሩት ወደ ሎንዶን ያመሩት በሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንደሆነ አሰራሩ ያስረዳል።
የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ ሚኒስቴር አቶ ጌታቸው ረዳ በአልጀዚራ “ፊት ለፊት” በተሰኘ ፕሮግራም ላይ የሰጡት ቃለመጠይቅ በርካታ ጉዳዮችን እንድናነሳ ያስገድደናል። ይህ ቃለመጠይቅ የመንግስትን የሰላም፣ የምክክርና እርቅ ጥረት በሚያዳክም መልኩ አከራካሪና ጥርጣሬን ፈጣሪ ከመሆኑም በላይ፣ ሃገራዊ አመራርና የዓላማ አንድነትን የሚሸረሽር ሆኖ አግኝተነዋል። ይህ ድርጊት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ የሌሎች ሃይሎች አስተዋጽኦ ቢኖርበትም፣ የመንግስትን ስትራቴጂካዊ የሕዝብ ግንኙነት አደረጃጀትና ቅንጅት ጉድለት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ አያነጋግርም። ይህን እውነታ ለመከላከል መሞከር ዳግም ሌሎችም በተመሳሳይ በሌሎች የታቀደና የተጠና ድግስ እንዲንቦራጨቁ ፈቃድ ከመስጠት የዘለለ አይሆንም።
የስትራቴጂክ ቅንጅት ችግር
የመንግስት ዋነኛው ችግር ስትራቴጂካዊ የሕዝብ ግንኙነት ተግባራትን በታቀደ፣ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መምራት አለመቻሉ ነው። አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ይህን የሕዝብ ግንኙነት ደካማነት ችግር ለመፍታት ዓመታት መውሰዱ ነው። የደነዘዘ የኮሙኒኬሽን አመራር መድቦ ወርቃማ ስራዎቹን ጨለማ ውስጥ ቆልፎ ያሳለፈው ጊዜ ሳያንስ መንግስት አሁንም በስትራቴጂክ አካሄድ ችግር ነጥብ እየጣለ ነው። ይህ አያስኬድም። ሊቆም ይገባል። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ዋጋ ያስከፍላቸዋል።
ትልቅ ዓለም አቀፍ ስኬት በተገኘበት ማግስት እንደ አቶ ጌታቸው ዓይነት ቃለ መጠይቅ የሕዝብን ትኩረት በሚሰርቅ፣ አወዛጋቢ እና የሃገርን ገፅታ ግንባታ የሚጎዳ ርዕሰ ጉዳይ ለምን የሃገሪቱን ጠቅላላ የመረጃ ከባቢ (Information Ecosystem) ሊቆጣጠረው ቻለ? ዓላማውስ ምን ነበር? ለምን ዛሬ? ይህን ጥያቄ የሚመለሰው ማን ነው?
አቶ ጌታቸው ቃለ መጠይቁን ሲሰጡ በምን አቋም እንደነበረ ግልጽ አይደለም። እንደ መንግሥት ባለሥልጣን? እንደ ስምረት ፓርቲ አመራር? ወይስ እንደ ግለሰብ? የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ስለዚህ ቃለ መጠይቅ ያውቅ ነበር? ዓላማው የመንግስትን ስትራቴጂካዊ ግብ ማሳካት ነበርን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ግልጽ ካልሆነ፣ የሕዝብ ግንኙነቱ ሥራ በታቀደ፣ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ሳይሆን በዘፈቀደ እየተመራ መሆኑን ያመለክታል። ያሳዝናል። አቶ ጌታቸውስ ያለፈው ሳያንሳቸው፣ በተሰጣቸው ይቅርታ አዝነው አገርና ሕዝብ መካስ ሲገባቸው በተሰጣቸው ምህረት ላይ እንዲህ ያለ ቲዊስት ሲደነሱ እንዴት ነው ዝም የሚባሉት? እሳቸውስ ስንት ኣመት ነው የሚዘላብዱት? ወይስ የሚወራባቸው እውነት ነው?
በመሰረቱ ማናቸውም የመንግስት ስትራቴጂካዊ ተግባቦት ጥረቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ የሰላም እና ደኅንነት ስትራቴጂካዊ ግቦችን ለማሳካት ያለሙ መሆን አለባቸው። የቡድን ሃያ ሃገራት ተሳትፎ እና የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ COP32 ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧ ትልቅ የዲፕሎማሲ፣ ሃገራዊ ገፅታና መልካም ስም የማደስ ስትራቴጂካዊ ግብን ያሳካ ነበር። ይህ ስኬት ወዲያውኑ በአወዛጋቢና አጥፊ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሸፈን መፈቀዱ ከስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ያፈነገጠ ተግባር ነው። እንደ አዲስ ሪፖርተር አቋም የማረቂያ እርምጃ ሳይመሽ ያስፈልግላል።
ለም አቀፉን ተጨባጭ ሁኔታ መረዳት
በዚህ ፈጣን እና ተለዋዋጭ ዓለም ዓቀፍና ሃገራዊ ሁኔታ፣ ሃገራት ጂኦፓለቲካዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በእጃቸው ያለውን ብሄራዊ የተፅዕኖ መሳሪያዎች የሚጠቀሙበት ዘመን ላይ እንገኛለን። እንደ አልጀዚራ እና መሰል ዓለም ዓቀፍ ተፅዕኖ ያላቸው ሚዲያዎች የሃገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ስትራቴጂክ መሳሪያዎች እንደሆኑ መረዳት ይገባል። በመሆኑም በአልጀዚራ አነሳሽነት በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ የሚሰጡ መረጃዎች፣ መግለጫዎች እና ቃለ-መጠይቆች የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቁ ወይም የሚጎዱ ስለመሆናቸው ቀድሞ ተፈትሾ መሆን ይገባዋል። እያንዳንዱ ቃል እና አውድ የሃገርን ዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚ፣ ሰላምና ደህንነት ለጥቃት የሚያጋልጥ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። ይህ ላይደገም መፍትሄ የሚበጅለት ቁልፍ ጉዳይ ነው። በዚህ ይብቃ!!
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያሳየችውን አዎንታዊ ገፅታ በቸልተኝነት በተሰጠ ቃለ መጠይቅ እንድታጣ መፍቀድ የለባትም። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂውን በማጥበቅ፣ የቅንጅት ሥርዓት በመዘርጋት እና ትኩረትን በስኬቶች ላይ በማቆየት የመልካም ስም ማደስ ስትራቴጂውን በጥብቅ መተግበር አለበት። የሕዝብ ግንኙነት በዘፈቀደ የሚደረግ ተግባር ሳይሆን የጦርነት ስልት አንድ አካል እንደሆነ መታሰብ ይኖርበታል።
ደግመን ደጋግመን እንደምንለው ዛሬም የኮሙኒኬሽን / የህዝብ ግንኙነት ያለህ እንላለን። አቶ ጌታቸውም መዘላበድ ከስልጣን እንደሚያስነሳና ተራ የቀበሌ ነዋሪ እንደሚያደርግ ቢያዉቁ ድግ ነው እንላለን። አሁን ያሉት በበረሃ ቃል አቀባይነት ሳይሆን በመንግስት ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ነውና አደብ ግድ ነው። የእርስዎ የበዙና ታሪክ የማይረሳቸው ቀይ መስመሮች ህያው ናቸው!! የሕዝብንም ሆነ የመንግስትን ምህረት ካናናቁ ወደ ነበሩበት የስራ ኃላፊነትዎ ይመለሱ!!
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





