አዲስ ሪፖርተር – የአርሲ ዞን ነዋሪዎች ምስክርነት ” ለሟች የኃይማኖት ታርጋ እየተለጠፈ ወንጀለኞች ከተጠያቂነት እየዳነ ነው” የሚለው ስጋታቸው እያየለ ነው፤ የቀድሞ ቂም አጋጣሚን ተንተርሶ፣ በአርሲ አክቲቪስቶች ታጅቦ የፖለቲካ ማገዶ መሆኑን በርካቶች እየገለጹ ነው፤ በዚህ ምክንያት ወነጀለኞች በኃይማኖት ከለላ ተጀቡነው ይኖርሉ”
በአርሲ ዞን በተደጋጋሚ እስከ ቅርብ ቀን ድረስ ሲፈጸም የነበረው ግድያ በደፈናው ከኃይማኖት ጋር የሚያያዝ ሆኖ ከመቀረቡ ውጪ በጥናትና ምርመራ፣ በጥልቅ ክትትል የሚጨበጥ ማሰረጃ ቀርቦበት አያውቅም። የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቅርቡ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ሪፖርት ሲያደርግ ካለውና ከስጠው ፍንጭ ውጪ በተቋም ደረጃ የተነፈሰ የለም።
በአርሲ ዞን የሚፈጸመውን የንጹሃን ግድያ ለራሳቸው የፖለቲካ ማገዶነት የሚጠቀሙበት ቡድኖች፣ ፖለቲከኞች፣ ተናበው የሚሰሩ ፓርቲዎችና ሚዲያዎች ስለገዳዮች ማንነት ለማጣራት በግል፣ በቡድን፣ በፓርቲ ወይም በድርጅት ደረጃ ሲታትሩ አይታይም። አይሰማም።
ግድያው ሲሰማ አምርረው “ህዝባችን፣ ኃይማኖታችን” በሚል መግለጫና ተቃውሞ ከሚያሰሙት መካከል ቀዳሚ የሚባሉትን አዲስ ሪፖርተር “ስለምን ገዳዮቹ እንዲታወቁ በማንነታቸው ላይ ትኩረት አያደርጉም?” በሚል ላቀረበችላቸው ጥያቄ የተሰጠው ግብረ መልስ “እንዴት እንደዚህ እንጠየቃለን” የሚል ስድብ አዘል መልስና ማስፈራሪያ ነው። በጭሩ የበርካቶቹ ዕምነትና ፍላጎት የገዳዮቹን ማንነት፣ የግድያውን ምክንያት ማወቅ ሳይሆን። “ክርስቲያኖች ተመርጠው ተገደሉ” በሚል ዜናውን ወደ ኃይማኖት ግጭት የማሳደግ ዝንባሌ የሚታይበት ነው።
“የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስለምን ይህን ተደጋጋሚ ጉዳይ አላጠናውም” በሚል ለአንድ ኃላፊ ጥያቄ አቅርበን “ ኮሚሽኑ በራሱ አሰራርና አካሄድ እየሄደበት ስለሆነ ለጊዜው ምንም ምላሽ የለውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ካነጋገርናቸው ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዳሉት ለጊዜው ፓርቲያቸው ዝምታን መርጧል። ምክንያቱ ደግሞ ጉዳዩ ማጣራት የሚያሻው በመሆኑ ነው። ማጣራትና ጥንቃቄ ከጉዳዩ ስስነት አንጻር ቁልፍ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በፓርቲው መዋቅር መሰረት ማጣራቱ በጥንቃቄ እየተሰራ ነው።
አዲስ ሪፖርተር ይህንኑ የሚድበሰበስ ጉዳይ ለማጥራት ከአርሲ ዞን ነዋሪዎች ላይ አስተያየት ለመስብሰብ ሙከራ አድርጋለች። ቢያንስ ላለፈው አንድ ዓመት ንጹሃን በተናጥልና በቡድን ሲገደሉ “ኃይማኖት ተኮር ጥቃት የሚመስል” እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። “ኃይማኖት” ሲሉ ግን ከተለመደውና በተደጋጋሚ የንጹሃንን ነብስ የግል ፍላጎታቸውና ፖለቲካ ማገዶነት ከሚጠቀሙበት አውድ በተለየ ነው።
የንጹሃኑን ግድያ አስመልክቶ “ከተለመደው ፈፅሞ ተቃራኒ ነው” ሲሉን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ ፣ በዞኑ የሚኖሩ ከዓመታት በፊት ቂምና ቁርሾ መኖሩን ያስታውሳሉ። ይህ የኖረ ቂም በቀል አሁናዊ ሁኔታን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እርስ በእርስ እንደሚገዳደሉ አመልክተዋል።
አጋጣሚውን በመጠቀም ግድያውን እንዴት እንደሚያከናውኑት ለተጠየቁት፣ የአስተያየት ሰጪዎቹ ምላሽ በምሳሌ የተደገፈ ማብራሪያ ነበር። መጀመሪያ መበቃቀል ወይም ድምን በደም መመለስ የተለመደ መሆኑን ያስረዳሉ። ያክኩና ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ ሰው የአባቱን ፣የአያቱን ገዳይ ለመበቀል ጊዜ ሲያማትር ኖሮ አሁን ሁኔታው ስለተመቸ ቀን ሲቆጥርለት የነበረውን ሰው ጨለማን ተገን ያደርግና ገሎ ይጥለዋል።
“ደሙን በደም ካወራረደ በሁዋላ አጋጣሚውን ይጠቀማል” ሲሉ የሚናገሩት እነዚሁ የስፍራው ነዋሪዎች፣ ገዳይ በሕግ ላለመጠየቅ የሚጠቀመው ዘዴ “ሟች ኦርቶዶክስ ስለሆነ የታጠቁ ኃይሎች ገድለው ጥለውታል” በማለት በመንደሩ ወሬ ማውራት ይጀምራል።
አንዳንዶች የሚነዛው ወሬ እውነት አለመሆኑን ቢጠራጠሩም ፣ከመሀል ድንገት ከማንም ጋር የደም ንክኪ የሌለው የሆነ ግለሰብ ተገድሎ ሲጣል ኃይማኖታዊ የአለባበስ ስርዓት እንደሚደረገለት ነዋሪዎቹ “አየን” ያሉትን ተናግረዋል። የተገደለውን ሰው አለባበስ ያዩ ነዋሪዎች ሳይፈልጉ እንዲያምኑ የሚገደዱትም በዚሁ ምክንያት የተነሳ መሆኑን አመልክተዋል። ይሕንን አካሄድ ሥራዬ ብሎ የሚያጣራና የሚመረመር የዞኑ ሀገረ ስብከት ሆነ ፣ጠቅላይ ቤተክህነት እንደሌለም አመልክተዋል።
የዞኑ አገር ስብከት “እንዲህ ብለህ ሪፖርት አድርግ ተብያለሁ” ሲል ሲኖዶስም በተመሳሳይ ከዞኑ አገር ስብከት የተላከለትን ሪፖርት እንደሚያደርግ ቀደም ባሉት በአዲስ ሪፖርተር ዘገባዎ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።
“በሌሎች ዓለማት ለምሳሌ ሂዝቦላ፣ አልቃይዳ፣ አልሸባብ ወዘተ ግድያም ሆነ እገታ ሲፈጽሙ ንብረት ሲያወድሙና የጅምላ ወንጀል ሲፈጽሙ ኃላፊነት ወስደው መግለጫ ያወጣሉ። በመግለጫቸው ወይም በቃለ ምልልስ ሳይሸማቀቁ የፈጽሙትን ድርጊት ለምን እንደፈጸሙም ያብራራሉ። ይህ የተለመደ ነው። ” የሚሉት እነዚሁ የህግ ባለሙያዎች ” በአርሲ በተደጋጋሚ ደረሰ የተባለው ግድያ የጥቃት አድራሺዎቹን ማንነት እነሱ ራሳቸው ኃላፊነት ወስደው ባያስታውቁም የአገሪቱ ሚዲያዎች የግልና የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ የሚደብቁበት ምክንያት አሳሳቢ ነው” ማለታቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግድያዎቹን አስመልክቶ ሁለቱም አካላት የሚያምኑት ፣የገዳይ ጀሌ የሆኑትንና እነሱ “ትንንሽ እግዚአብሔሮች” ሲሉ የሚጠሯቸውን አካላት ነው። እነዚህን አካላት “የሚዲያ ካህናትና ጳጳሳት፣ በአርሲ ዞን የሚገኙ አክቲቪስቶች” ሲሉ ይጠሩዋቸዋል።
የስልቱን መለያያትና አጋጣሚውን የመጠቀሙ ጉዳይ በተለይ ገዳይ ገንዘብ ካለውና ፣የሚግባባቸው ሰዎች ካሉት ነገሮች በቀላሉ ይከናወኑለታል። ይህ አገላለጽ ሚዲያዎች አንድ ግድያ በተፈጸመ ቅጸብት ዜናውን በተፈለገው አግባብ ሕዝብ ላይ ለመጫንና ከፍሉን በመሬት፣ ከፊሉን በኃይማኖት ግጭት ለማሳተፍ እንደሚጠቀሙበት ከተጠቆመው ጋር የሚመሳሰል ሆኗል።
“አሁን ላይ በኃይማኖታቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ከሚያጡ ዜጎች በቂም በቀል ተነሳሽነት እርስ በእርስ የሚገዳደሉ የዞኑ ነዋሪዎች ቁጥራቸው ከፍ ይላል” የሚሉት እነዚሁ ወገኖች “ይህን ሲሉ ኦነግ ሸኔና የፋኖ ታጣቂዎች ምንም በደል አልፈጸሙም ለማለት እንዳልሆነ አመልክተዋል። በዚህ እነሱ በሰጡት መረጃ አግባብ ቢጠና ቁልፉ ችግር እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ነባራዊ ሁኔታን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ነዋሪዎቹ በየግላቸው መተላለቅን ምርጫቸው ማድረጋቸው ያስታወቁት የዞኑ ነዋሪዎች፣ በአከባቢው በአብዛኛው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑ ግለሰቦች በርካታ መሆናቸው ቢገለጽም ፣በዛው ልክ የወንጌል አማኞች እና የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
በአሁን ወቅት አንድ ገዳይ በእነዚህ ምቹ አጋጣሚዎች ምክንያት ከሕግ ቅጣት በይፋ ሲድን እንመለከታለን ይላሉ ነዋሪዎች።
በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች አልፎ አልፎ መኖራቸውን ያመለከቱት ነዋሪዎቹ፣ ታጣቂዎቹ ወደ ሌሎች አከባቢ የሚጓዝን አንድ የአርሲ ዞን ነዋሪን ቢያገኙት የሚበላ፣ የሚጠጣ ነገር ይዞ ከተገኘ ከመቀበል ውጭ ሌሎች እርምጃዎችን ሲወስዱ ብዙም እንደማይሰተዋል ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ አመልክተዋል።
መረጃውን ለአዲስ ሪፖርተር የሰጡት ወገኖች ስጋታቸውንም አኑረዋል። በበቀል መነሾ አንድን ሰው የገደሉ ግለሰቦች ሟችን በዕምነቱ ሳቢያ እንደሞተ በማስመሰል ራሳቸውን ከተጠያቂነት የሚሻሸሹ መሆናቸው ነው። ሚዲያዎችም ይህን ጉዳይ ቢያስቡበት እንደሚሻል ጠቁመዋል።
“ይሕ ማለት ግን ይላሉ የዞኑ ነዋሪዎች በሸኔ እና በፋኖ የሚገደሉ ንፁሃን ዜጎች የሉም ማለት አይደለም” ሲሉ ነዋሪዎቹ ምርመራ የሚያደርጉ አካላት ጥቆማቸውን ከኝዛቤ እንዲከት አሳስበዋል።
እንደ አከባቢው ነዋሪዎች የአከባቢው ንጹሃን ዜጎች ሰቆቃና ጭንቀት ከዚህም ክስተት የሚሰፋና ከፍ ያለ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ መገናኛ ብዙሃን ጋር የደረሰው የባለፈው ሳምንት ክስተት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ወዲህ ከአከባቢው ተለይቶ የማያውቅ አፈና እና ግድያ አንዱ ማሳያ እንጂ ብቸኛው አይደለም ነው የሚሉት።
“አሁን የአፈና እና የተናጥል ግድያ ጥቃቱ የአርሲ ዞን ሁሉንም ቀበሌ አዳርሷል ማለት ይቻላል” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ መሰል ጥቃት ባሌ አዋሳኝ ወረዳዎች ድረስ የሚዘልቅ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በርካታ የእስልምና እና ክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ለዓመታት ተከባብረው በኖሩባት አርሲ ዞን የቅርብ ጊዜያት ወዲህ መልኩን መቀየሩ ከስሩ ሊጠናና መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






