አዲስ ሪፖርተር የግብፅን ቅኝ ገዥ አስተሳሰብና የድርድር እምቢተኝነት እንደማይቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። “ኢትዮጵያ በወሰኗ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም ከማንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ የለባትም” ብሏል
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን ድርድርን በአጽንዖት የሚጥል እና ግልጽ ማስፈራሪያዎችን የያዘ ንግግር እንደማይቀበል በማስታወቅ ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ይህ አካሄድ የግብፅ መንግሥት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል አለመቻሉን የሚያሳይ መገለጫው መሆኑን አመልክቷል።
“አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናት በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ተዘፍቀው፣ በናይል ወንዝ ውሃ ላይ የብቸኝነት ባለቤትነት እንዳላቸው ያስባሉ” ያለው መግለጫው፤ እነዚህ አካላት የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን እና ታሪካዊ መብቶች የሚባሉትን በመጥቀስ በአባይ ላይ ያላቸውን የሞኖፖል ፍላጎት ደጋግመው እንደሚያንጸባርቁ ገልጿል።
በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተገዥ፣ ደካማ እና የተከፋፈሉ ሀገራት የካይሮን ፍላጎት እንዲፈጽሙ የሚያስበው የግብጽ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ጸጥታ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ የሚያካሂደው በዚሁ ጊዜው ባለፈ እሳቤው ከሚመነጭ መርሁ እንደሆነ መግለጫው አስታውቋል።
ይህ የተሳሳተ አካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአመራር እና የአስተሳሰብ አለመዘመን ወይም ውድቀት ሲል አጠንክሮ ኮንኖታል። እንዲህ ያለው የግብጽ መገለጫ ኢትዮጵያን በፍጹም የማያስደነግጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በአማራ ክልል ጠብመንጃ ያነሱ ኃይሎች የውጭ አገር ደጋፊዎችና አመራሮች መሆናችውን የሚገልጹ በገሃድ ከግብጽ ጋር አብረው በመወገን እንደሚሰሩ በይፋ በተቃዋሚነት ከሚታወቁ ልሳኖች ጋር በተደጋጋሚ በሚያደርጉት ውይይት መናገራቸው የሚታወስ ነው።
“ኢትዮጵያ የአፍሪካዊነት (Pan-Africanism) መርህን ለረጅም ጊዜ ያቀነቀነች እና በመላው አህጉር ያሉ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሎችን የደገፈች ረጅም እና ኩሩ ታሪክ ያላት ሀገር ነች” ሲልም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የቆመችበትን ይማይዛነፍ አቋም በመግለጫው አስታውቋል።
“በጥንታዊ ሥልጣኔዎች ታሪክ የተመሠረተች እና ጠንካራ የአፍሪካ አብሮነት ልምድ ያላት በመሆኗ፤ ካይሮ ለማስወገድ የምትቸገረውን የቅኝ ግዛት ቅሪት ለመቀበል ምንም ዓይነት ቦታ የላትም” ካይሮ በየአጋጣሚው ለምታዜመው ዜማ ቁርጥ ያለ የአቋም ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ከኢትዮጵያ ማህጸን ተነሥቶ የሚፈሰው አባይ ወንዝ ለናይል ተፋሰስ ሰማኒያ በመቶ ያህሉን ውሃ እንደሚያበረከት ያስታወቀው የውጭ ጉዳይመግለጫ፣ ልክ እንደማንኛውም ተፋሰስ ሀገር ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በዚህ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት እንዳላት ማንም ሊረዳ እንደሚገባ አመልክቷል።
ይህም ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና እኩል የመጠቀም በመሠረታዊ የዓለም አቀፍ ሕግ መርህ የሚመራ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ በወሰኗ ውስጥ በሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠቀም ከማንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ የለባትም” ብሏል፡፡
“ባለፉት ጊዜያት ግብፅ በድርድር ውስጥ የምትሳተፍ በማስመሰል፣ በግትርነቷ እና በብቸኝነት የይገባኛል ጥያቄዋ አማካኝነት የድርድሩን እድገትንና መፍትሔዎችን ስታደናቅፍ ቆይታለች” ያለው ሚኒስቴሩ፤ አሁን ግን ትርጉም ያለው ድርድርን በመቃወም የማስመሰል ፖሊሲዋ ይፋ እና ቀጥተኛ ሆኗል ሲል አስታውቋል።
“ግብፅ ድርድርን በመተው እና ግጭት ለመፍጠር በግልጽ በማሰብ የጥላቻ ንግግሯን አጠናክራለች” ብሏል መግለጫው። ይህ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት በሁሉም ተዋናዮች መወገዝ እንዳለበት ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
“እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የኢትዮጵያ የልማት ምኞቶችና ፕሮጀክቶች የአፍሪካ የራስ መተማመን እና እድገት መገለጫዎች ናቸው። ካይሮ አሁን በያዘችው አቋም እና ንግግር ከመጠመድ ይልቅ፣ የኢትዮጵያን ልማት ተቀብሎ እና ለጋራ ብልጽግናና ልማት የሚጠቅም የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር በቅን ልቦና መሥራት ብልህነት ነው” መሆኑን በማመላከት ወጭ ጉዳይ ለግብጽ ምክር ለግሷል።
ስለሆነም ዓለምም ሆነ አፍሪካ የሚያስፈልጋቸው ግጭትና ግብግብ ሳይሆን፣ የበለጠ ትብብርና ውይይት ነው ሲልም መግለጫው አክሏል።
በመጨረሻም አሁን ላይ ያሉትም ሆነ የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት ኢትዮጵያ በአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷን አጥብቃ እንደምትጠብቅ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ በፍትሐዊነትና እኩልነት መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ ለሁሉ ተጠቃሚነት የሚበጅ መፍትሔዎችን ለመቀበልና አብሮ ለመስራት ክፍት መሆኗን አረጋግጧ።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






