ጊዜን ጋላቢው ሠዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን ንጉሡ “ከሩቅ አልመህ ቅርብ አትርመጥመጥ”
አዲስ ሪፖርተር – የጥበብ ግብሩ ሰውን ለስላሳ ፍጥረት ማድረግ ነው ይላሉ እጓለ ገብረዮሐንስ፡፡ ሻካራው የሰው ፀባይ በጥበብ እንዲገራ፣ እንዲለሰልስ ግድ ከሚላቸው ምሁራን ውስጥ አለ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት አቅኝው በቀለ መኮንን (ፕ/ር) ፊተኛው ነው፡፡ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ከሆኑትም አንዱ ነው፡፡ ሠዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን ንጉሡ (ፕ/ር)፡፡
ግጥም ሲጽፍም ይቀርጻል የሚባለው በቀለ (ፕ/ር) ሲቀርጽ ከተራረፉት ቃላት አንስተን ስለሕይወቱ ስለመንገዱ እንዳስሳለን፤ ለክብሩ የሚሆኑ ቃላትም እናኖራለን፡፡
ሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ በሚገባው ልክ አልተከበረም ብሎ ሲናገር “ሀገሩ የኔ ጨው ነው ብሎ ጣዕሙን ካላወጀ ሁሉም ድንጋይ ነው ብሎ ይወረውረዋል” ይላል። ቀራጺው በቀለ የኪነት ጣዕምና ለዛ የሚገደው ያመሰግንሃል፤ ምስጋናም አዋጅ ነው ብለን ጨዋታ እንጀምር ለበቀለ አካዳሚያዊ ጉዞ እና ኪናዊ ሕይወት፡፡
በቀለ ገና ልጅ ሆኖ ነው ወደ አዲስ ነገር መሄድ የለመደው፤ ማቃናት እና መቃኘት ግብሩ ሆኖ አደገ፡፡ ስሙን እንኳን በሥዕል ንድፍ ይጽፍ ነበር፡፡ የእጁ ጣቶች አሥር ናቸው፣ ቁስ ሲሸከሙ ግን የሃምሳ ያህል ናቸው፡፡
የብረት ቁርጥራጭን ሥጋ እና አጥንት ያለው የኛው ዘመድ አድርጎ ያሳየናል። የባህር አረፋ ሲገፋው የኖረን ድንጋይ በእጆቹ ቀርጾ በአንድ ዝክር ወመዘክር ያቀራርበናል።
እንደቀድሞዎቹ ጠቢባን ሁለገብ (Polymath) ነው። ቀራጺ፣ ሠዓሊ፣ ገጣሚ ይፋ አያወጣውም እንጂ ክራር ሲከር እንኳን ጥሩ ተጫዋች ነው ይሉታል ወዳጆቹ።
የኢትዮጵያን የሥነ ጥበብ ትምህርት አቋቋሚም ነው፤ የገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ ማዕከል መሥራችና ዳይሬክተር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በጥበብ የዘመናዊነት ፈር ባለአደራ፣ ባህላዊውን የጥበብ ጽንሰ ሐሳብ ከዘመናዊው ያቀራረበም ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በማስተማር በርካታ ተማሪዎችን አፍርቷል።
በቅኝ ግዛት የመጡ ውርሶችን ይተቻል፣ ማሕበራዊ ሕይወትን የሚከልሉ ያልተገረዙ ሥልጣኔዎችን አጥብቆ ይቃወማል። ጥበብ የማሳየት ብቻ ሳይሆን የመለወጥ፣ የመጠየቅ፣ የመግራት ባህርይው መነጠቅ የለበትም ብሎም በጽኑ ያምናል።
ይህ የውበት የኪን ፍቅሩ ከየት መነጨ ብለን ከልጅነቱ መልስ ብንፈልግ በቀለ ውልደቱም ዕድገቱም ከውበትና ሕይወት የራቀ አልነበረም። በሐይቆች ተከባ የውበት ዘይት ከሚፈስባት ቢሾፍቱ ጥር 6 ቀን 1956 ዓ.ም ነው የተወለደው። ግዕዛዊ ልቡና ያዘ፡፡ አቡጊዳ ፊደል ፈድሎ፣ ዳዊት ደግሞ ሳመ፡፡
የአርቲስትነት ጉዞው ድንገቴ አይደለም፤ ይልቁንም ከአካዳሚው ጋር ተቀይጦ የዳበረ ስሜት ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአጼ ልብነድንግል ወሰንሰገድ ትምህርት ቤት እየተማረ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ሐዋርያ ቢሆናቸው የሚመኛቸው መምህሩ የሥዕል ዝንባሌውን እንዲከተል መከሩት፡፡
“ከሩቅ አልመህ ቅርብ አትርመጥመጥ“
ሰግተህ ከምትቆም ስትጋልብ ፍረጥ።›› ሲል ‹‹ቼ በለው›› በሚል ግጥሙ ሲጋልብ ይታያል፤ ጊዜ ለበቀለ ፈረስ ነው ከጋለብከው ከምትፈልገው ቦታ ያደርስሃል፡፡
ሠዓሊና ቀራጺነቱ ዋናው የመታወቂያ ሥራዎቹ ይሁኑ እንጂ በወጣትነቱ ተውኔት ሲተውን፣ ግጥም ሲገጥም፣ መፈክር ሲፈክር፣ ደብዳቤ ሲጽፍ እንደሚዋጣለት አብሮ አደጎቹ ያውቃሉ፡፡ ግጥም ላይ ግን ይበረታል፤ በተለይም የፍቅር ግጥሞቹን ሲያስታውሳቸው በሰዎች ልብ ለመቀረስ የሚችሉ እንደሆነ ትዝ ይለዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ልዕልት ተናኘወርቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማር ጥበብ በቴክኒክ ከማቴሪያልና ከውሑድ ብቻ ሳይሆን ዓለምን ለማየት ዐይንን ከመክፈት እንደሚጀምር በመምህሩ ተረዳ። የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናውን የወሰደው በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፤ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መሠናዶ ሲያደርግ ለጥበቡም እጁን እያፍታታ ነበር፡፡
እንደሀገር አቀፍ ፈተናው እኩል ፈተና ሆኖበት የነበረው የዛን ጊዜ አዲስ አበባ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት የአሁኑ አለ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ነው፡፡ ለመግባት ደጅ ጠና፡፡ 1 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ተፈትነው ከ14ቱ ያለፉት ውስጥ አንዱ ሆነ፡፡ 1971 ዓ.ም መሠረቱን ወጠነ፣ ‹አለ› ተምሮ መሠረቱን አፀና።
በትምህርት ቤቱ 5 ዓመታት አለፉ፤ በ1975 ዓ.ም ዲፕሎማውን ያዘ። ጊዜንም እንደፈረስ መጋለብ የሚወደው በቀለ በማዕረግ ተመርቆ በዚያው ተቀጠረ፡፡
የድግግሞሽ ተግባሩ ወደ ጥበብ ወሰደው። በጊዜው ልብሶችን እየመላለሰ ይሰፋል፣ ጫማዎችን እየደጋገመ ይጠግናል፣ ግጥሞቹን እንኳ እየከለሰ ይጽፍ ነበር።
የመጀመሪያ ሥራው ቁሳዊውን ዓለም በተቃርኖ የሞገተ ነበር። በአዲስ አበባ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ገብቶ ሳለ ለጥበብ ሥራዎች የዘመኑ መንፈስ “ሶሻሊስት ሪያሊዝም” የገነነበት ነበር። ጊዜው ወታደራዊ ግዳጅ ያጠላበት በመሆኑ ከአንድ የጥበብ ሥራ ይልቅ አረር የተፋ ብረት በክብሩ ይልቃል።
የሙያ ክህሎቱን ወደሚያቃናለት የዛኔው ሶቭየት ሕብረት (ሩሲያ) የትምህርት ዕድል አገኘ። የሞስኮ ስቴት የሥነጥበብ ኢንስቲትዩት (ሱሪኮብ) ገባ።

‹ቀኑ ደመናማ ነው› ብሎ ይጀምራል የሞስኮ ሰማይ፤ በጭጋግና በጭፍናው ውስጥ የበቀለ ዓይኖች ውበት ለማየት አልተከፈቱም፡፡ ለ6 ዓመታት ሲቆይ የሕይወትና የውበት አመለካከት ኮምፓሱን ለወጠ። ከተክለሰውነት ጀምሮ በርካታ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በማጥናቱ ለቀራጺነቱ መሠረት ሆነው። በ1985 ዓ.ም በቅርጻ ቅርጽ የማስተርስ ዲግሪውን አገኘ።
‹‹እንዴት እንደዋዛ ይሸኛል በደጅ›› ትላለች ህብስት ጥሩነህ፤ በቀለ ከሩሲያ ዕውቀትና አቅሙን ቀርቅቦ ተመለሰ፡፡ ከሞስኮ አካዳሚያዊ ዕውቀት ብቻ አይደለም ይዞ የተመለሰው፤ ሩሲያ ርዕዮተዓለሙ ሲናጥ፣ ዐለት የመሰለው ፖለቲካ ሲናድ ተመልክቷል። ብሉይ ዘመንን (Classical period) በንባብ በማወቁ ሥልጣኔን ከታሪክ ጋር እየፈከረ ይመለከተዋል፤ በሥራዎቹም ይህን ጭብጥ እንደ ፈትለነገር (Theme) ተገልግሎበታል፤ የሚጨሰው ጠረጴዛ አንዱ ሥራው ማሳያ ነው።
በቀለ ከሩሲያ ይዞት የመጣው ዕውቀትና ጥሪ ብሉይ በሆነ በሬ ኢዲስ እርሻ እንደ መትለም ነበር። ዘመናዊነት ቀድሞ የተማረበትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዛሬው አለ ሥነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት መልሶ ተቀላቀለ። በሥነጥበብ ታሪክ ማስተማር ጀመረ፤ ከዚያም የንድፍ ጥናትና ሌሎች ኮርሶችን ማስተማር ቀጠለ፡፡
ትምህርት ቤቱ እስክንድር ቦጎስያን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ እና ሌሎችንም ያበቃ የዘመናዊነት ምሽግ ነው። የትምህርት ሥነዘዴው ባህላዊ በመሆኑ “ሙዚየም” የመሆን አደጋ ወድቆበት ነበር። በቀለ ትምህርት ቤቱን አዘመነው፤ ለዓለም ባዳ ያልሆነ ለአካባቢውም ንቁ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት እንዲኖር ታገለ።
አካባቢን መምሰል ከሥም ይጀምራል፤ ኮሌጁ መጠሪያውን የለወጠው በ2009 ዓ.ም ገደማ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ አለ ፈለገ ሰላምን የሚዘክር ስም ይዞ የቀጠለውም እርሱ ዲን ሆኖ በሠራው ሥራ ነው፡፡
ሥራዎቹ ዲሲፕሊን የሚሻገሩ ናቸው፡፡ የሚዲያ አውድ መለዋወጡን ሲረዳ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው የፊልም ጥናት እንዲከፈት ከአቋቋሚዎች ዋነኛው ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ገንኖ እንዲታይ ቅርጻ ቅርጽ ብቻ ሳይሆን ፊልም እንደሚያስፈልገን ቀድመው ከተረዱት ነው።
በይነ ዲሲፕሊናዊ ንባብ አድርገው ከሚያስተምሩት ውስጥ በቀለ ቀዳሚው ነው፤ ያስተማራቸው ተማሪዎችና ያማከራቸው ምሁራን ይመሰክሩለታል፡፡ የማስተማር ግብሩና ብያኔው የቀደመውን ማፍረስ ነው፡፡ መበተን (Deconstruction) እና ደግሞ መገንባት የማስተማር አካሄዱ ነው።
ዓለም አቀፉን ቀኖና የወረረውን አውሮፓ ተኮር የጥበብ ታሪክ ተማሪዎቹ እንዲጥሉት ይሞግታል። ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ባዕድ (Exotic) አተያይ አካዳሚያው ነጻ ማውጣት እንዳለበት ያምናል።
በቀለ ዘመናዊ ብቻ አይደለም፤ ዘመን ዐይ፣ ዘመን ተመልካች ነው፣ የዘመናዊነትም አደራ ጠባቂ ነው፡፡ የሀገራችን አጥኚዎች ገብረክርስቶስን ሲገልጹት በአካሉም በመንፈሱም ንቁ፣ የሕይወት ተንቀሳቃሽ፣ ሸንቃጣ፣ ቀበጥባጣ፣ አዲስ ነገር ወዳጅ ነው፡፡ የአውሮፓ ምሁራን ግብሩን ሲገልጡት፣ ከሰሃራ በታች አንድ ቅልጥ ያለ ዘመናዊ ሠዓሊ አለ እርሱም ገብረክርስቶስ ደስታ የሚሉት፡፡ ይህን ጠባቂው በቀለ መኮንን ነው፡፡
የዘመናዊነት አደራ ጠባቂነቱ ገብረክርስቶስ ደስታ (1924 እስከ 1973) የጥበብ ማዕከል መዘክርን ከማቋቋም ይጀምራል፡፡
የገብረክርስቶስ የሥዕል ዘይቤ አብስትራክት ኤክስፕረሽኒዝም ነው። በዚህም ከወግ አጥባቂዎቹ ፖለቲከኞች ከፍተኛ የተቃውሞ ጣጣ ገጥሞት ነበር። አዲስ ነገር አበሳ አያጣውም፤ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ከሩሲያ ተምረው “ፋቡላ” ይዘው ሲመጡ እንዲሁ አልሠመረላቸውም ነበር።
ገብረክርስቶስ ያየው ልማዳዊ የጥበብ ደፈቃ ነፍሱን ቢደብታት በአሜሪካ ተሰዶ አረፈ። የተበታተኑ ሥራዎቹ በጥናት ተለቅመው ከጀርመን ሠላሳ ሥራዎቹ ተመለሱ፤ ይህ እንዲሆን የበቀለ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። እናም በቀለ ማዕከሉን በገብረክርስቶስ ሥራዎች እየታወሰ እና ንቁ የጥበብ ሥራዎች መታያ እንዲሆን አደረገው።
በቀድሞው አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ቤተመንግሥት ውስጥ የተገነባው ማዕከሉ በርካታ ሠዓሊያን ኤግዚቢሽን አድርገውበታል፤ ውይይቶችና ሙግቶች ቀርበውበታል፤ ለዕውቀት፣ ለሐሳብ፣ ለንግግር ክፍት መሆን የሚወደው የበቀለ ስብዕና በማዕከሉ በኩል ነጥሮ ይታያል። ማዕከሉ በርግጥም የትውልድ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እንዲከውን የበቀለ ድርሻ ታላቅ ነው።
በቀለ መኮንን (ፕ/ር) የመጀመሪያ የሥዕል ዐውደ ርዕዩን በፊላንድ ያቀረበው በትምህርት ላይ እያለ የሠራቸውን ሥራዎች ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በቁጥር ያልተሰሉ፣ በግብር የረቀቁ፣ በግዝፈት የተለቁ ሥራዎችን አሳይቷል፡፡
ቅርጻ ቅርጽን እንደ ድርሰት በተለዋጭ (Metaphorically) ያጫውተዋል፡፡ አንዳንዴም ሐሳብን እንደ መልዕክት ማስገሪያ ተገልግሎ በድብልቅ ሚዲያ (Mixed Media) ሥራዎቹን ያቀርባል፡፡
በ1996 ዓ.ም ‹እንቆቅልሽ› የተሰኘ ሥራው ዛሬም ድረስ ማሳያ ሆኖ የዘለቀ ነው፡፡ ‹ዕድልና ምርጫ፣ ባሩድና ብርጉድ፣ ጤፍና ነጻነት…› በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያቀረባቸው ሥራዎቹ ናቸው፡፡
የበቀለ ቁሶች ፖለቲካዊ ‘ተነካናኪነት’ አላቸው፤ በአዲስ አበባ ጣራ ላይ የሚታየው ቆርቆሮ የከተማዋ ቁርበት ነው። ድሆችን የሚያስጠልል። በፀሐይና በዝናብ ፍርርቅ የዛጉ ቆርቆሮዎችን አንስቶ ኢኮኖሚያዊ እውነታ ማሳያ ያደርጋቸዋል።
የቅኝ ግዛት አሁንም በአፍሪካ መቀጠሉን (post-colonial thought) ያሳየበት የሚጨሰው ጠረጴዛ (The Smoking Table) ሥራው ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን አግኝቷል። አፍሪካውያን ነጻ ከወጡም በኋላ በውጭ ተጽዕኖዎች በራስ መተማመናቸውን እንደተነጠቁ እና ሌሎችንም መልዕክቶች የሸሸገ ነው፡፡
የሥነጽሑፍ መምህር ቴዎድሮስ ገብሬ (ዶ/ር) ሥራዎቹን በመፈተት ‹በብሔራዊ ትዕምርት ፍለጋ ውስጥ› በሚል ርዕስ ‹ጤፍና ነጻነት› የሚል ሥራውን ጥልቅ ምርምር አድርጎበታል፡፡
የዘመናዊነት የጥበብ ፈር ይዘው የተሠሩት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኪነሐውልት፣ አብርኆት የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ደጅ ላይ ያለው የእውቀት ትዕምርት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት… ማሳያ ሥራዎቹ ናቸው፡፡
የቺካጎ አርቲስቶች ዓለም አቀፍ ሽልማትን በ1990 ዓ.ም ያሸነፈ ነው፤ በሽልማቱም ብቸኛው አፍሪካዊ የሥነ ጥበብ ባለሙያ ነበር። በአውሮፓውያኑ 2006 በአሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ የIIE ፕሮግራም የሆነውን የ’Scholar Rescue Fund’ ሲቀበልም የመጀመሪያው የሥነ ጥበብ ሰው ነበር።
ከዚህ ሁሉ የሚልቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለርሱ ትልቁ ሽልማቱ ነው፡፡ በታሕሣሥ ወር የዩኒቨርሲቲው 75ኛ ዓመት ልደት ይሆናል፣ በጥር ወር ደግሞ በቀለ መኮንን (ፕ/ር) 62ኛ ዓመቱን ይዞ ‹‹ቼ በለው›› እያለ ጊዜን እየጋለበ ይቀጥላል፡፡ ሽማግሌው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕድሜው ሳይጫነው አካዳሚውን እያደሰ፣ የዘራውን እያበቀለ መኮንን አድርጎ ይዟል፡፡
በዐምደወርቅ ሽባባው ፋና ብሮድካስት
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






