የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን “የመድኃኒዓለም ረዳት” (Co-Redemptrix) እና “ሴት አማላጅ” ስሞች አገደች

Date:

አዲስ ሪፖርተር – የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ በፊት ለማርያም ተሰጥተዋት የነበሩትን “የመድኃኒዓለም ረዳት” (Co-Redemptrix) እና “ሴት አማላጅ” (እናት አማላጅ) (Mediatrix) የሚሉትን ስሞች ለማርያም እንዳይውሉ ውሳኔ አስተላለፈች። ውሳኔው በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ሊመሠረት ለታቀደው ኅብረት ድጋፍ ሰጪ እንደሆነም ተነግሮለታል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የአስተምህሮና ሥነ-ስርዓት የሚመራው “በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጽ/ቤት” (Dicastery for the Doctrine of the Faith (DDF)) በኅዳር ወር መጀመሪያ “የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝብ እናት” (Mater Populi Fidelis) በሚል ርዕስ ሰፊ ማብራሪያ ይፋ አድርጓል።

ሰነዱ “የመድኃኒዓለም ረዳት (Co-Redemptrix) የሚለው ለማርያም የተሰጠው ማዕረግ ማርያምን ለማወደስ የሚረዳ አይደለም” ይላል። ለማርያም የተሰጠው ይህ ማዕረግ እንዲያውም የጌታች ኢየሱስ ክርስቶስን ልዩ የሆነውን የማዳን ሚና የሚያደበዝዝ ነው በማለት ያብራራል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያጸደቁት ይህ ሰነድ የማርያምን የማዕረግ አጠራሮችን አስመልክቶ ዘመናትን ላስቆጠረው ክርክር ዕልባት የሰጠ እንደሆነ በምሑራን ዘንድ አስተያየት ተሰጥቶበታል። በተለይ “የመድኃኒዓለም ረዳት” (Co-Redemptrix) (ወይም “ቤዛዊተ ኩሉ ዓለም”፤ የዓለም ሁሉ ቤዛ) የሚለው መጠሪያ በተለያዩ የክርስቲያን ሃይማኖቶች መካከል አንድነት ለማምጣት ለሚደረገው ሥራ ዕንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የጸደቀውን ሰነድ በፊርማቸው ይፋ ያደረጉት የእምነት አስተምህሮ ጽ/ቤት ኃላፊው ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፌርናንዴዝ፤ ሰነዱ “ክርስቶስ ብቸኛ አማላጅና አዳኝ (መድኃኒዓለም) የመሆኑን ምሥጢር ከማሳየት አንጻር የማርያምን ከምዕመናን ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ምን ቦታ ላይ እንደሆነች ለማሳየት የታለመ ነው፤ ይህም የካቶሊክን እውነተኛና ታማኝ ማንነት በማሳየት አብያተ ክርስቲያናትን ወደ ኅብረት ለማምጣት ከሚደረገው ጥረት (ecumenical effort)” ጋር አብሮ የሚሄድ ነው ብለዋል።

ሰነዱ “የጸጋዎች ሁሉ እናት” (‘Mediatrix of All Graces,’) የሚለው የማርያም መጠሪያ ውሱንነት ያለውና የማርያምን ልዩ ቦታ በቅጡ የማያሳይ ነው ብሎታል። “የአምላክ እናት” እና “የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝብ እናት” የሚሉት የማርያም መጠሪያዎች እንዲቀጥሉም ማደፋፈሪያ ሰጥቷል።

ማርያም በልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የዳነች መሆኗን በተመለከተ “ልዩ እና ከጊዜው በቀደመ መልኩ” አጽዕኖት ሰጥቶ ሰነዱ ተናግሯል። ሲያብራራም፤ “ተወዳዳሪ የሌለው የማርያም ታላቅነት የሚገኘው በተሰጣትና መንፈስ ቅዱስ በእርሷ እንዲሠራ በታማኝነት በመፍቀዷ ላይ ነው። ከክርስቶስ ሚና እኩል ወይም ጎን ለጎን የሆነ ሚና ስንሰጣት አቻ የሌለውንና የእርሷ ብቻ የሆነውን ውበቷን እንነፍጋታለን” በማለት ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ይሰጣል።       

ይህ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተወሰደውን አቋም በተመለከተ የምስራቃዊ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምንም በይፋ ያወጡት መግለጫ የለም። ምክንያቱም በኦርቶዶክሳውያኑ ዘንድ ማርያም እንደ ካቶሊካውያን በእነዚህ የማዕረግ ስሞች ስለማትጠራ ነው። ይህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት በኦርቶዶክስና በካቶሊክ መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ለማጥበብ ብዙ ዕድል እንደሚሰጥና ከተቻለም ውኅደት ለማምጣት እንደሚረዳ በሁለቱም ወገን ተነግሯል።  

የማርያም ማዕረግ ዝቅ የተደረገበት ሰነድ በይፋ የሆነበት ሮም በሚገኘው የኢየሱሳውያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት (Jesuit Curia) ንግግር ያደረጉት ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፌርናንዴዝ፤ ሰነዱ “… አብያተ ክርስቲያናትን ወደ ኅብረት ለማምጣት ከሚደረገው ጥረት (ecumenical effort)” ጋር አብሮ የሚሄድ ነው ማለታቸው የዓቋም ለውጥ የማደረጉን አንድ ምክንያት በግልጽ ያሳየ ነው።

በፕሮቴስታንቱ ዘንድ በይፋ የወጣ ሁሉንም የሚወክል መግለጫ ባይኖርም በተናጠል ሃሳባቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ የገለጹ እንደሚሉት ውሳኔው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል። ይህ ከዚህ በፊት ስንጠይቀው የነበረ ጉዳይ ነው ያሉ አንዳንድ የፕሮቴስታንት አስተያየት ሰጪዎች ውሳኔው ለአብሮነትና ለመቀራረብ በር ከፋች ነው ብለዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ውሳኔ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችው መግለጫ ባይኖርም በማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ መልዕክቶችን የሚያቀርቡ የተሃድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች ውሳኔውን በበጎ መልኩ ተቀብለውታል። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድና ማርያምን መጽሐፍ ቅዱስ ከሰጣት ክብር የበለጠ ከመስጠት ቤተ ክርስቲያን እንድትቆጠብ ጠይቀዋል።

ከወራት በፊት የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል “የሰባ ገብዣ” በሚል ርዕስ ስቅለት ዕለት ባቀረቡት መልዕክት ከፍተኛ ውግዘትና ፍረጃ ተሰንዝሮባቸው ነበር። ሊቀ ጳጳሱ በመልዕክታቸው፤ “አትደንግጡ፣ ማርያም የዓለም ቤዛ አይደለችም! … ቤዛ ልጇ ክርስቶስ ነው” በማለት ነበር የተናገሩት። የአቡነ ገብርኤል ስብከት በቤተ ክርስቲያኗ በኩል ውግዘት ቢያስከትልም በርካታ የፕሮቴስታንት መምህራን ለስብከታቸው አድናቆትና ድጋፍ በመስጠት፤ ኅብረት የምንፈልግ ከሆነ በማርያም ጉዳይ ላይ መግባባትና ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልገናል ሲሉ የተደመጡም ነበሩ።

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባሳተሙት “ደቂቀ እስጢፋኖስ” በሚለው መጽሐፍ በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት (1426-1460) የማርያም ማዕረግ እጅግ ገንኖ እንደወጣ ጽፈዋል። የንጉሡ እናት የበፊት ልጃቸው ስለሞቱባቸው “ያሁኑ ፅንሴ ተወልዶ በጤና ካደገ” ለማርያም እሰጠዋለሁ ብለው ተስለው የነበሩ መሆኑን መጽሐፉ ይጠቅስና ስለ አፄ ዘርአ ያዕቆብ ሲናገር፤ “(ንጉሡ) በእመቤታችን እርዳታ በሰላም በጤና ስለተወለደ ለሷ ከፍ ያለ ግዴታ የተሰማው ይመስላል። አባቱ ዳዊት የጀመረውን በፈረንሳይ፣ በእስፓኝ፣ በግብጽ፣ በፍልስጥኤም የተሠሩትን ታምሮቿን ወደ ግዕዝ መተርጎም በሰፊው ቀጠለበት፤ የውጪውን አገር ማስተርጎም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሠራቻቸውን ተአምራት ሁሉ፤ እየሰበሰበ በጽሑፍ አሰፈራቸው። ጸሐፊዎችን ሰብስቦ፣ ተአምረ ማርያምን እያስቀዳ በቅዳሴ ጊዜ እንደ ወንጌል በሥርዓት ቆመው እንዲያነቡት ለየገዳማቱ ላከላቸው፤ ይኽም አንድ የጭቅጭቅ ምንጭ ሆነ፤ ለየገዳማቱ በላከላቸው የተአምረማርያም መጽሐፍ መግቢያ ውስጥ “ፍጥረት ሁሉ ስለ እመቤታችን ተፈጠረ” የሚል” እንደነበረበት የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ደቂቀ እስጢፋኖስ” መጽሐፍ ይናገራል (ገጽ 25)። በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመንበረ ፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና የምዕመናን ቤቶች ውስጥ ባብዛኛው አውሮጳዊ መልክ ያላት ምስለ ማርያም ተሰቅላ ማየት ያልተለመደ ያልሆነው።

የተሐድሶ እንቅስቃሴ ዋና መምህር የሆኑት መሪጌታ ጽጌ ሥጦታው ለማርያም የሚሰጠው ከልክ ያለፈው ክብርና ውዳሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለውም ሲሉ አጥብቀው ይሞግታሉ። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ መሪጌታ ጽጌ የሰጡትን ሰፊና በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ እነዚህ ቪዲዮዎችን በማዳመጥ መረዳት ይቻላል፤ (“የማርያም ህይወት”፤ “ትንሣኤዋ – ጾመ ፍልሰታ”፤ ስለ ማርያም “ብዙ ጥያቄ ፤ አንድ መልስ!”)።

በታሪክ “የጨለማው ዘመን” ተብሎ የሚጠራውና በዳንኤል 7፡25 ትንቢት እንደተነገረው ለ1,260 ዓመታት (538 ዓም – 1798 ዓም እኤአ) የዘለቀው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበላይነት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ በካህናቱ ካልሆነ በቀር ማንም እንዳያነብብ ታግዶ ነበር። በዚህም ምክንያት ሰዎች ከቤተ ክርስቲያኗ የሚነገራቸውን ማንኛውንም አስተምህሮ በእምነት ይቀበሉ ነበር።

የፈረንሳዩ ንጉሥ ናፖሊዮን የጳጳሳዊ ሥልጣንን ከማስወገዱ በፊት የተነሳው የፕሮቴስታንት ተሃድሶ መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች በቋንቋቸው እንዲያነቡ በር የከፈተ ነበር። ፕሮቴስት ማድረግ መቃወም እንደመሆኑ የፕሮቴስታንት እሳቤ በካቶሊክ የሚሰጡት አስተምህሮዎችን በመቃወም የተጀመረ ነበር። ይህ ከአምስት መቶ ዓመት በፊት የተካሄደ ታላቅ ንቅናቄ አሁን ላይ በሃይማኖት ኅብረት ስም መስመሩ እየደበዘዘ መጥቷል። ለኅብረቱ እውን መሆን ከካቶሊክ በኩል የሚደረጉ የአስተምህሮ ለውጦች ጥሩ መደላድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው ይህ የማርያምን ማዕረግ ዝቅ የማድረጉ ውሳኔ የሒደቱ አንድ አካል ተደርጎ የሚታይ ነው።

ኅብረት መፍጠርና አንድ መሆን በራሱ መልካም ቢሆንም በአንድነት ስም የሚደረጉ ውሳኔዎችን በማይቀበሉ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖና ውግዘት ቀላል አይሆንም። ዓለም ወደ ሃይማኖታዊ አንድነት መምጣቱን ተከትሎ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያላቸው ውሳኔዎች መተላለፋቸው አይቀሬ ነው (ዳንኤል 3)። እነዚህን ውሳኔዎች አንቀበልም በሚሉ ላይ አስገዳጅ ውሳኔዎች አብሮ ይተላለፍባቸዋል። ሰዎች ሁሉ ውሳኔዎቹን አምነው እንዲቀበሉ (“በግምባራቸው”) ወይም በግድ (“በቀኝ እጃቸው”) እንዲቀበሉ ይደረጋሉ (ራዕይ 13:15-17)።

ፕሮቴስታንቶች ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን ልዩነት አጥብበው በኅብረት ስም የአስተምህሮ ስምምነት ላይ በመድረስ ፕሮቴስት ማድረጋቸውን አቁመው ወደ ኅብረት እንደሚመጡ አስቀድሞ የተነገረ ነው። “ታላቁ ተጋድሎ” በሚለው መጽሐፍ 36ኛው ምዕራፍ ላይ የተሰጠውን ሰፊ ትንታኔ እዚህ ላይ ማንበብ ይቻላል። የአስተምህሮ ልዩነታችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስለሆነ ወደ ስምምነት ለመምጣት አንችልም፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች መካድ አንችልም የሚሉ የኅብረቱ ተቃዋሚ ተደርገው በመቆጠር ለከባድ መከራና ስቃይ ይዳረጋሉ። 

“ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል”። (ራዕይ 13:15-17)።

ምንጭ ጊዜው

ዝግጅት ክፍሉ / ለዚህ ጽሁፍ መልስ ወይም መቃወሚያ ወይም እርምት ወይም መከራከሪያ ለሚያቀርቡ ሁሉ መድረኩ ክፍት እንደሆነ ይገልጻል። ዜናው የጊዜው የድረገጽ መጽሄት ብቻ ነው!!


Cardinal Fernández, Co-Redeemer, Co-Redemptrix, ecumenical effort, Mater Populi Fidelis, Mediatrix, Mediatrix of All Graces, The Mother of the Faithful People of God, መሪጌታ ጽጌ, ደቂቀ እስጢፋኖስ

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ነፃ የሃሳብ ሪፐብሊክ፣ የሁምቦልድት ፍልስፍና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሪፎርም እይታ

ቢልዱንግ እና የሃሳብ ትውልድ እሳቤዎች ሲቀናጁ ምሁራን የቆዩ የትርክት...

የኤርትራ አፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች ግንባር ፈጠሩ፤ “ስምምነቱ ለሻዕቢያ አስደንጋጭ መርዶ ነው” አቶ አብዲ ሼኽ መሐመድ

አዲስ ሪፓርተር - በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች...

የፕሮፌሰሩ እይታ “ጠንቋይ የሰዉን እንጂ የራሱን አያዉቅም” አብይ አሕመድ ነጥብ አስጥለዋል

ሀገር የምትገነባው መንግስት ያድርግ በሚሉ ጥያቄዎች ሳይሆን እኔ ይሄን...