አዲስ ሪፖርተር – ታሪካዊ ጠላታችን ግብፅ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላትን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የምትጠቀመው የመጀመሪያ አማራጭ እቅድ (plan A) ኢትዮጵያን በቅጥረኞች አማካይነት ከውስጥ ማዳከም፣ማዛል፣ ከዛም አልፎ ማፈራረስ ነው። ራሳቸውን “የፓለቲካ ሃይሎች” የሚሉትን ቅጥረኞች በመሳሪያነት በመጠቀቀም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነቷን በማደፍረስ በመንግስት ላይ ከፍተኛ አስተዳደራዊ ወጪ በማጦዝ፣ አቅሙን በማዛል የኢኮኖሚ አሻጥር ተዋንያኖችን በቻለው ቀዳዳ ሁሉ በትኗል። አሰልፏል።
ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ላይ የምታከናውናቸው የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲያቋረጡ ስፍር ቁጥር የሌላው ደባ ሸርቧል። ሃብቱን ከስክሶ የማዕቀብ ስትራቴጂ (Containment Strategy) አካሂዷል። የሚችለውን ኃይልና ተቋማት ባንዳነት መለያቸው ከሆኑት ጎረቤቶቻችንና የእነሱ አሽከሮች የሆኑትን በአንድነት አግተልትሎ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።
የግብጽ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ የማይቀየርና ዘላለማዊ እንደሆነ በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ሃይሎችን ለመርዳት ከሚያደርጉት ጥረት መረዳት ይቻላል። ለግብጽ ባርነት ያደረችው ኤርትራ ኢትዮጵያን የሚያተራምሱ ታጣቂዎች ከማሰልጠንና አሰልጥኖ ከማሰማራት የቦዘነችበት አንድም ወቅት የለም።
የሩቁን ብንተወው በኤርትራ በኩል ወያኔን እና አማራ ክልል ውስጥ በተከፋፈል አጀንዳና አደረጃጀት የጠበንጃ ትግል እንዲጀምሩ የተደረጉትን የፋኖ ኃይሎች በመጠቀም ኢትዮጵያን የማተራመስ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ከርማለች። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ባሉ ምድራዊ እውነቶች ዕቅዱ የተሳካ ኣልሆነም። እንዳሰቡትም ሊሄድላቸው አልቻለም። እንደውም ዕቅዳቸው የከሸፈ ሆኗል ማለት ይቻላል። ይህ ክሽፈት ግብፅ ወደ ሁለተኛው አማራጭ አቅድ (plan B) እንድታፈላልግ አድርጓታል። ይኸውም ኢትዮጵያ ለሱደን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በቢንሻንጉል ክልል ውስጥ የስልጠና ካምፕ በማዘጋጀት፣ የሎጂስቲክስና የመሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች የሚል የሀሳት ትርክት በመፍጠር በአልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሰራዊት በምስራቅ ሱዳን ድንበር በቢንሻንጉል በኩል ጦር ግንባር በመክፈት የህዳሴ ግደቡን ለመቆጣጠር ዒላማ ያደረገ ነው። በመሆኑም በዚህ ጽሁፍ የግብፅ በኤርትራ በኩል ትህነግን ተጠቅማ ኢትዮጵያን የማተራመስ ጥረቷ ለምን ሊከሽፍ ቻለ ? አሁን በሁለተኛ አማራጭነት የያዙት እቅድ ምንያህል አዋጭ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መዳሰስ ነው።
ቅዠት ሆኖ የቀረው ፅምዶ
ግብፅ በኤርትራ በኩል ወያኔን እና አማራ ክልል ውስጥ የጠበንጃ ትግል ውስጥ ያሉትን የፋኖ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማተራመስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ለዚህም ዕቅድ ስኬት ኤርትራና ትህነግ ፅምዶ የተሰኘ ጥምረት እንዲፈጥሩ አድርጋለች። ሁለቱንም ተላላኪዎች “ቼ በለው” እያለችና ፍርፋሪ በሚጣልላቸው ልክስክስ ሚዲያዎች ሴራ እያስመረተች የጀመረችው ቅንጅት ወይም እቅድ እንዳሰቡት ሊሄድላቸው አልቻለም። ይህንኑ የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየወጡባቸው ይገኛል።
ትህነግ እንኳን የኢሳያስን አጀንዳ ተቀብሎ ወታደራዊ አመራር ለመስጠት ቀርቶ የውስጥ አንድነቱን አጥቶ እንደ አሜባ እየተከፋፈለና እየተበጣጠሰ ይገኛል። ሕዝቡ ” ዞር በሉ” ብሏል ሰራዊቱም “የምትሰጠኝን ስጠኝና ወደ ሰላማዊ ኖሮ ልመለስ” በሚል ተቃውሞ ውስጥ ነው።
አንደኛው የሕወሃት ክንፍ አክሱም ፅዮን ማርያም ሲከበር በኤርትራ ወታደሮች የተጨፈጨፉትን ንጹሃን የትግራይ ልጆች የሚዘክር የሻማ ማብራት ስነ ሥርዓት አድርጎ ተቃውሞውን አሳይቷል። ይህ ድርጊት የኢሳያሳ በአሽከርነት በመሰረተ ፅምዶ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶበታል። ትህነግ ከኢሳያስ እጅ መውጣቱን ማብሰሪያ ምልክታዊ ኩነት ተደርጎ ተወስዷል። በሌላ በኩል “ሙክት ከቀጠቀጠው” እንዲሉ በተላላኪነትና ባንድነት ጥርሳቸውን የነቀሉ ወንጀለኞች በትግራይ ንጹሃን ደም ዳግም ሊነግዱ ሞክረው የጨው አምድ ሆነዋል።
ከራሳቸው ጓዳ እንደተሰማው ሰሞኑን ሲካሄድ የነበረው የትህነግ ሰብሰባ ያለ አንዳች መቋጫ አመራሩ ተከፋፍሎ ተጠናቅቋል። በዓለም ገብረዋህድ የሚመራው አንደኛው ቡድን ድርጅታችን ትህነግ ሰለተዳከመች ለውጥ ያሰፈልጋል የሚል አቛም የያዘ ሲሆን ሌላኛው በድብረፅዮን የሚመራው ቡድን ደግሞ ድርጅታችን ትህነግ ተጠናክራለች መልካም በሚባል ደረጃ ላይ ትገኛለች የሚል ሰፊ ልዩነቱን አንፀባርቋል።
ሻዕቢያ ይደግፈኛል ብሎ የሚውተረተረው የምግበይ ሃይሌ ቡድን በአክሱም ፅዮን በዓል ዕለት በተፈፀመው የሻማ ማብራት ስነሥርዓት ከሻዕቢያ ጋር የፈፀመውን የፅምዶ ግንባር በትኖበታል። ሃራ መሬት ላይ ያለው የሰላም ሃይል እንደተጠበቀ ሆኖ የትግራይ ሕዝብ በጠቅላላው ጦርነት ይብቃን ብሎ ምሎ ተገዝቷል። እንኳን የጥይት ጦርነት “የቲማቲም ድብድም ማየት አንፈልግም” ሲል አደባባይ ተናግሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ “የፌደራል መንግስት የድጎማ በጀቱ ለልማት እንጂ እራሱን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት እያለ ለሚጠራ ጦርነት ጎሳሚ ቡድን ደመወዝና ስንቅ መዋል የለበትም” በሚል የፋይናንስ ማዕቀብ ማድረጉ ትክክለኛ እርምጃ በመሆኑ ውጤት እያስገኘ ይገኛል። የሰራዊቱ አባላት “ትጥቅ እንፍታ፣ ተሃድሶ ወስደን ወደ መደበኛ ሕይወት እንድንገባ የተጀመረው DDR program ይቀጥል” የሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የፌደራል መንግስት ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ መቐለ ከተማ ውስጥ የፍሳሽ ማስወገጃ በ2.24 ቢሊዩን ብር በጀት ለመገንባት የፌደራል ውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር የሆኑት ኢሃብታሙ ኢተፋ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን የግንባታ መሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። ይህ ተግባር የትግራይ ሕዝብን አዕምሮና ልቦና በማሸነፍ የመንግስትን የሰላም ግንባታና ጥረቱን ይበልጥ እንደሚደግፈው ይታመናል። ሌላኛው ተስፋ የተደረገበት ፋኖን የመጠቀም እቅድ እንዲሁ ከፊሉ ከመንግስት ጋር በመደራደር ወደ ሰላም መንገድ ማምራቱና የተረፈውም ዛሬ ነገ እያለ ለውሳኔ እየተናጠ ነው።
በጠቅላላው መሬት ላይ ያለው ሃቅ የሚያሳየው ግብፅ በኤርትራ በኩል ትህነግን ተጠቅማ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የምታደርገው ጥረት ከንቱ እንደቀረና እንደከሸፈ ነው። የግብፅ የሰሞኑ ቀቢፀ ተስፋ የሆነ ጦርነት አይቀሬ ዛቻና ፉከራ ከዚህ ተስፋ መቁረጥ የመነጨ እንደሆነ መረዳት አይከብድም። ገና ብዙ ይላሉ፣ ከመንግስት አቋም፣ ከሕዝብ ስሜትና በተግባር እየሆነ ካለው እንቅስቃሴ አንጻር የግብጽ በየአቅጣጫው መንፈራገጥ የሚጠብቅና ቀደም ሲል ጀምሮ የሚታወቅ ነው። ወደ ቤኒሻንጉል የተወረወረችውም በዚሁ ስሌት ነው።
የግብፅ ሁለተኛ አማራጭ ፡ የቢንሻንጉል ጦር ግንባር
የግብፅ መንግስት ከተስፋ መቁረጥ ስሜት በመነጨ በሁለተኛ አማራጭነት (Plan B) የያዘውን መጫወቻ ካርድ ሊመዝ ችሏል። በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ በኩል ግብፅ የውሃ ደህንነት ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የጦርነት አማራጭን መጠቀም ዝግ አለማድረጋቸውን በአልጀዚራ በኩል በገለፁት መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ በሶስት ግንባር ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት አድርገዋል። ከነዚህ መካከል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ግንባር ዋነኛው ነው።
ይህ ግንባር ዋና ዒላማው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ነው። ለዚህም እንደ ማስመሰያ ምክንያት (pretext) የቀረበው “ኢትዮጵያ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንዲገነቡ ፈቅዳለች” የሚል ነው። የአልቡርሃን ክስም የተቀዳው ከዚህ ከግብጽ ዕቅድ ሁለት ነው።
“የኢትዮጵያ መንግስት በሄሜቲ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በመደገፍ በኢትዮጵያ እና በሱዳን አዋሳኝ በሆነ በቤኒሻንጉል ክልል የሚገኘው አልሃማር የተባለ የድንበር ቦታ ላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ገንብታለች” የሚል ነው። “የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ከአስር ሺህ ወታደሮች በላይ ማሰልጠን እንደሚችል በተገለፀው ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሎጂስቲክ ድጋፍ፣ የአየር ትራንስፖርት እና የአየር ማረፊያ ዝግጅት፣ የወታደራዊ ስልጠና ማኑዋል፣ አሰልጣኞች እና የሰው ኃይል መድቧል” በሚል አልቡርሃን ከሷል።
በመሆኑም ይህን የስልጠና ቦታ አጥቅቶ ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ የሕዳሴው ግድብን ኢላማ ያደረገ ጦር ግንባር አልቡርሃን በሱዳን ምስራቃዊ አቅጣጫ በቤንሻንጉል በኩል አዲስ ወታደራዊ ግንባር ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጿል። ይህ ከመሰማቱ ሳምንት በፊት አቶ አንዳርጋቸው የሚባሉት የባንዳዎች ቁንጮ “ይህ መንግስት ይህን ዓመት ከጨረሰ ታምር ነው” በማለት ፍርፋሪ ከሚለቅሙቱ ወሬ ለቃሚዎች ጋር ምኞት ሲቆላና ጭራውን ሲረጭ እንደነር ይታወሳል።
የግንባሩ ወታደራዊ አንድምታ
ይህ የሕዳሴው ግድብን ዒላማ አድርጎ በቢንሻንጉል ጉሙዝ ድንበር በኩል የተከፈተው የጦር ግንባር ከወታደራዊ ጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ከዚህ አንፃር ሶስት ቢሆኖችን (scenario’s) ማስቀመጥ እንችላለን። የመጀመሪያው ቢሆን ግብፅ እና ሱዳን ሆን ብለው ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ አቅራቢያ ለውጭ ሃይል ወታደራዊ ማሰልጠኛ በማቋቋም የግድቡን አስተዳደር ስጋት ላይ ጥላለች በማለት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ እንድትወገዝ በማድረግ የግድቡን አስተዳደር በተመለከተ በሚደረግ ድርድር የተሻለ የመደራደር አቅም (Positions of Strength) እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።
በመሰረቱ የኢትዮጵያ መንግስት ካላበደ በስተቀረ ዓለም አቀፍ የትኩረት መስክ በሆኑው ህዳሴው ግድብ አቅራቢያ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ይገነባል ተብሎ አይጠበቅም ። የግብጽን ስልትና አሰላለፍ እያጠና መክቶ ወደ አጥቂነት የተዛወረ፣ አባይንም ገድቦ ያሳየ መንግስት ይህቺን ስሌት ይስታል ብለው የሚንጫጩ የያኔው ትውልድ ሽንቶች ይህን ቅዠት እያነሱ ሲያዜሙ በጨዋነታቸው ከመሳቅ የዘለለ ምንም አስተያየት አይሰጥም። በመሆኑም ይህን የሃሰተ ክስ ኢትዮጵያ በተጨባጭ በተመሰሳይ ሚድያ በማስተባበል ተቀባይነት እንዳይኖረው ልታደርግ ትችላለች። ለዚህም ይህን የሃሰት ዘገባ ለሰራው አልጀዚራ ኔት የኢትዮጵያ መንግስት ማስተባበያ ሰጥቷል።
ሁለተኛው ቢሆን ደግሞ ሱዳንና ግብፅ የቢንሻንጉል፣ በአፋር እና በወልቃይት ድንበር በኩል የጦር ግንባር የፈጠሩ በማስመሰል ኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የከበባ የሕልውና ስጋት የተደቀነባት እንደሆነ እንድታስብ በማድረግ ወታደራዊ ወጪዋን በከፍተኛ ደረጃ በማናር ሌሎች በአባይ ተፋሰስ ላይ የምትሰራቸውን የልማት ስራዎች እንድታቋርጥ በማድረግ ብሄራዊ ጥቅማቸውን ማስከበር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋ ከፍተኛ (excessive militarization) ከሆነ በሌሎች ሃገሮች ዘንድ እንደ ጸብ አጫሪ ሃይል ትፈረጅና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና የቱሪስት ፍሰት እንዲቀንስ ያደርጋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ቢሆን ግምት ውስጥ በማስገባት የአልጀዚራን ዘገባ እንደ ትክክለኛ የማይስተባበል መረጃ በመውሰድ ወታደራዊ ውሳኔዎችን ከመወሰኑ በፊት በሱዳን በኩል ያለውን ዝግጅት የተለያዩ የወታደራዊ መረጃ ምንጮችን መሰረት አድርጎ መረጃ በማሰባሰብ፣ በመተንተንና የጠራ መረጃ በመጠቀም ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት። ይህን የሃሰት ድርጊታቸውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችንና መድረኮችን በመጠቀም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ እንዲወገዙ ማድረግ አለበት። አንዳንድ ሚዲያዎችና ማህበራዊ አውዶች ላይ ለአገር ያሰቡ የሚመስላቸው እንደ ቢቢሲ ያሉትን መርዛማ ጽሁፎች የሚያጋሩትን ሳይቀር እንዴት ዘመቻውን መከላከል እንዳለባቸው ስልተና ቢጤ ቢሰጣቸው በሚል የዚህ ሪፖርት አቅራቢ እግረ መንገዱን ይጠቁማል። ወደፊት በስፋት የሚያየው ጉዳይ እንደሆነም ይገልጻል።
ሶስተኛው ቢሆን ግብፅና ሱዳን ወታደራዊ ጥምረት በመፍጠር ቢንሻንጉል በኩል ግንባር በመክፈት የህዳሴ ግድቡን በከባድ መሳሪያ በመምታት ማፍረስ ሳይሆን ግድቡን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር ጥረት ማድረግ ነው። ይህ የህዳሴ ግድብን ዒላማ ያደረገ ጦርነት ግብጽ እና ሱዳን በራሳቸው ላይ የጥፋት ውሃ እንዳዘዙ ይቆጠራል። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመጣስ ሕልውና ስጋት የፈጠረውን የግብፅና የሱዳን ጥምር ሃይል ለመከላከል ኢትዮጵያ ማናቸውን ሃይል የመጠቀም ሉዓላዊ መብት አላት። ከዚህም መካከል በስድስት መቶ ጫማ ከፍታ ላይ የሚገኘው የሕዳሴ ግድቡ በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰበት የፈርዖን ጦር የእስራኤልን ሕዝብን ሲያሳድድ እግዚአብሔር ቀይ ባህር በጦሩ ላይ እንደጎረፈና እንዳጠፋቸው (ዘጸአት 14:26-28) ሁሉ የሕዳሴው ግድብ ውሃ ግብፅንና ሱዳንን ከምድረ-ገፅ እንደሚያጠፋቸው ግልፅ ማስጠንቀቂያ ከመስጥት ጀምሮ አስፈላጊውን ወታደራዊ እምርጃ ኢትዮጵያ ለመውሰድ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት እንደላት በማስፈራራት እና ይህንንም ለመፈፀም ቁርጠኛ መሆኑዋን በተግባር ማሳየት ትችላለች። በመሆኑም ሱዳንና ግብጽ ሕዳሴውን ግድብ ለመያዝ የሚያደርጉት ወታደራዊ ጥረት ከጥቅሙ ይልቅ የሕልውና ስጋት ይዞባቸው እንደሚመጣ ሰለሚያውቁ ወታደራዊ የሃይል አማራጭን የመጠቀም ፍላጎት አይኖራቸውም።
እንደ መውጫ፡ የመጨረሻው ምዕራፍ
ግብፅ በእጇ ላይ ያላትን ማናቸውንም አማራጮች ለማስፈፀም ብሄራዊ የተፅዕኖ መሳሪያዎቿን ተጠቅማ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ እያደረገች ያላቸው ጥረት ውጤታ እየሆነ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ስለዚህ ያላት ብቸኛ አማራጭ ከአራት ኪሎ ጋር በሰላማዊ ድርድር የአባይ ወሃ አስተዳደርን በተመለከተ ሁሉም ወገን አሸናፊ የሆነበት ስምምነት መፍጠር ነው። ይህ አግባብ ብቻ ትክክለኛ አማራጭ እንደሆነ ይፋ የሚሆነው አሁን ላይ አልሲሲ ወደ ቤኒሻንጉል ተንጋሎ እያየ ያለው ቅዠት በቅርቡ እንደ ጉም ሲተንበት ነው።
በዚህ ሁሉ ውጥረት መካከል ኢትዮጵያ ሃገራዊ የውስጥ አንድነቷን እና ሰላሟን በማጠናከር ልትከተለው የሚገባው ስልት ማስረጃን መሠረት ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዋነኛው ነው። ግብጽንና አሽከሮቿን ያበሳጨው የሰሞኑ የነ ማስረሻ ሰጤ ኃይል ወደ ሰላም መምጣትና እነሱን ተክትሎ የተቀሩቱ መከተላቸው ነው። የኦነግ ሸኔ ኃይል መግባቱ እንዳለ ሆኖ።
የግብፅን ‘የህልውና ስጋት’ ትርክት ለመመከት፣ ኢትዮጵያ በግድቡ ቴክኒካዊ ገፅታዎች ላይ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን በሚያሳምን መልኩ ግልፅ መሆን አለባት። ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉዳት ከመፍጠር ይልቅ በጎርፍ መከላከል እና በተረጋጋ የውሃ ፍሰት አስተዳደር የጋራ ተጠቃሚነትን እንዴት እንደሚያስገኝ በሳይንሳዊ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለማቋረጥ ማሳየት ወሳኝ ነው። በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ በንቃት በዓለም አቀፍ ባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ በመገኘት፣ በውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ ያላትን ሉዓላዊ መብት ከዓለም አቀፍ የውሃ ህግ መርሆዎች ጋር በማጣጣም በማብራራት ማሳወቅ ይኖርባታል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ ወጥ፣ የተረጋጋ እና ለጋራ ልማት የተዘጋጀ መሆኑን በማሳየት፣ የግብፅና የሱዳን የጦርነት ቅስቀሳ ላይ ትኩረት ያደረጉ ማናቸውንም ንግግሮች በትዕግስት መቋቋም አለበት።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






