የኢትዮጵያ መንግሥት የፍትህ ሚኒስቴር በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መዝገብ ቀርበው የነበሩ ክሶች ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንዲቋረጡ መወሰኑን ተከትሎ ከእስር የተፈቱት የቀድሞው የሜቴክ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ትግራይ ተገንጥላ ከኤርትራ ጋር መዋሃድ እንዳለባት መግለጻቸውን ተከትሎ ክፉኛ ተተቹ፤ ቅዠታቸውም “ድንቁርናና ዘመኑን ያላገናዘበ” በሚል የተቃወሙት ፖለቲከኛ ክብሮም ወልደፃዲቅ ናቸው።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀል ክስ ክርክር ሲካሄድበት የነበረው ክስ ተቋርጦላቸው ከአምስት ዓመት ዕስር በሁዋላ የተፈቱት ክንፈ ዳኘው ያቀረቡት “ከኢትዮጵያ ተገንጥለን ከኤርትራ ጋር መዋሃድ እንፈልጋለን” የሚለው አስተያየት፣ “በትግራይ ሕዝብ ደም እና መስዋዕትነት የተገኘውን የፖለቲካ ትርፍ የሚያጨልም፣ ከእውነታ የራቀ እና ክልላችንን ወደ ከፋ አዘቅት የሚከት የዘመኑን ተግዳሮቶች ያልተረዳ ኋላቀር አስተሳሰብ ነው” ሲሉ አዲስ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት ፖለቲከኛ ክብሮም ወልደፃዲቅ አስረድተዋል።
“ጀነራሉ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39 ጠቅሰው የትግራይን የሀገርነት ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ቢሆንም፣ ይህን ታሪካዊ ጥያቄ ከኤርትራ ጋር መዋሃድ ከሚል ዘበት አጀንዳ ጋር ማጣመር ግን የትግራይን ህልውና በሚገባ ከሚያውቅ ሰው የማይጠበቅ ትልቅ ስህተት ነው” ሲሉ ፖለቲከኛው ተናግረዋል።
ትግራይ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ከሁሉም በላይ የተዋጋችው በታሪክም ሆነ በቅርብ ጊዜ በተፈጸሙ ግፎች ሳቢያ የህልውና አደጋ ከደቀነባት ከኤርትራ መንግሥት ጥቃት ለመከላከል መሆኑን ያጎሉት ነው-ፖለቲከኛው ክብሮም፣ “በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን የጨፈጨፈን እና ታሪካዊ መሠረተ ልማታችንን ያወደመን ኃይል እንዋሃድ ብሎ መጣራት፣ በሕዝባችን ላይ የተፈጸመውን ግፍ እንደ መርሳት ነው የሚቆጠረው” ብለዋል። ይህ የፖለቲካ ዕውርነት እንጂ ለትግራይ ብሔራዊ ጥቅም የሚበጅ ስልት አይደለም በማለት ክንፈ ዳኘውን ተችዋል።
ትግራይ በመጀመሪያ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ሰላሟን ማጠናከር እና ተገቢውን የፖለቲካ መብቷን ማስከበር ነው ። ከኤርትራ ጋር የውህደት ጥሪ ማቅረብ ማለት፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት በመናድ ትግራይን ዳግም ወደ ጦርነት አውድማ መጣል እና ክልሉን በኤርትራ የውክልና ጦርነት እንደመክተት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። ትግራይ አሁንም ቢሆን የውክልና ጦር ሜዳ የመሆን ስጋት እንዳለባት ጀነራሉ ራሳቸው ቢገልጹም፣ ለዚህ አደጋ እንደ መፍትሔ ውህደትን መሆኑን መግለጻቸው፣ ችግሩን መፍታት ሳይሆን ይበልጥ ማባባስ ፍላጎት እንዳላቸው ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል። የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎች መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው፣ በሕዝብ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሀገርነት ጥያቄን ማስቀደም ነው ሲሉ ገልጸዋል። ከዚያ በኋላም ቢሆን፣ ከማንኛውም ጎረቤት ኃይል ጋር መዋሃድ ወይም መተባበር የሚለው ጥያቄ በሕዝብ ውሳኔ እና በጠንካራ የፖለቲካ ጥናት ላይ የተመሰረተ እንጂ፣ በአንድ ግለሰብ ፍላጎት የሚወሰን መሆን የለበትም ሲሉ አብራርተዋል።
ትግራይ በጠየቀችው ትንሽ መስዋዕትነት ሀገር የምትሆነው በምርጫ፣ በዲፕሎማሲ እና ጠንካራ የውስጥ አንድነትን በመገንባት እንጂ ዳግም ከጠላቶቿ ጋር “እንዋሃድ” በሚል ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ በመግባት እንዳልሆነ ፖለቲከኛው አመልክተዋል። “የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ቀደም የከፈለውን ዋጋ እንዳይረሳ እና እንደ ጀነራሉ ያሉ የክልሉን የቅርብ እና የሩቅ ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ አደገኛ የፖለቲካ ሀሳቦችን በአንክሮ እንዲያይ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲሉ አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ክብሮም ወልደፃዲቅ አስታውቀዋል።
የቀድሞው ጄነራል ሜቴክ ክንፈ ሲታሰሩ ግዢ የፈጸመባቸው ሆቴሎች እንዲሁም የተለያዩ መሳሪዎች ግዢዎች የተካሄዱት ከተቋሙ የግዢ መመሪያ እና ከሕጋዊ አሠራር ውጪ መሆኑ በክስ መዝገቡ ላይ ተጠቅሶ ነበር። በዚህ ዓይነት መልኩ ግዢ ተፈጽሞባቸዋል ከተባሉት መካከል አንዱ ግዙፍ የጭነት መርከብ ሲሆን እና ሌሎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ መሳሪያዎች መሆናቸው ተገልጾ ነበር።
ሜቴክ “ከሥልጣኑ አልፎ ተያያዥነት በሌለው የትራንስፖርት ዘርፍ ለማሰማራት በመወሰን፣ ያለ ኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ መርከብ በመግዛት፣ ያለጨረታ መርከቦቹ አንዲጠገኑ በማድረግ” ኪሳራ እንደደረሰ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አመልክቶ ነበር። ሜጀር ጄኔራል ክንፈ፤ በእነዚህ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. ሲሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ቆይቷል። የፕሪቶሪያውን የሰላም አማራጭ ተከትሎ ከተፈቱ በሁዋላ ወደ ትግራይ ያቀኑት ክንፈ ዳኘው “ጽንፈኛ” ከሚባለው የትህነግ ወገን እንደሚመደቡ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ዋና ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው መያዛቸው ተነገረ። ሃላፊው ከትግራይ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው ጀነራሉ የተያዙት ትናንት ማምሻ ሁመራ ከተማ ውስጥ ነው። የትግራይ ልዩ ፖሊስ ጀነራሉን ከያዘ በኋላ ለፌደራል መንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ማስረከቡን የወቅቱ የትግራይ አስተዳደር ማስታወቁ አይዘነጋም።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






