አዲስ ሪፖረተር – የአሜሪካ መንግስት ከሰሞኑ ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ይሰጥ የነበረውን ጊዜያዊ የህግ ከለላ (TPS) የማቋረጡ ውሳኔ ታላቅ ፖለቲካዊ እንደምታ እንዳለው ተገለጸ። ውሳኔው አሜሪካ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ማደጉንና፣ በኢትዮጵያ ጠብ መንጃ ያነሱ ኃይሎችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ወደፊት የሚሰሙ አዳዲስ ጉዳዮች ስለመኖራቸው አመላካች እንደሆነ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች እየገለጹ ነው። ክስ እንደሚያዋጣ የሚመክሩም አሉ።
ውሳኔ ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች በአሉታዊና በአዎንታዊ የሚሰጡትን አስተያየቶች ተከትሎ አዲስ ሪፖርተር ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተለያዩ ወገኖችንና ባለሙያ አነጋግሯል። የዲፕሎማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጸጋዘአብ እንደሚሉት ውሳኔው የኢትዮጵያ መንግስትና የአሜሪካን መንግስት አሁናዊ የግንኙነት ደረጃቸው ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
የአሜሪካንን መንግስት ውሳኔ መነሻ በማድረግ ባለሙያ ለአዲስ ሪፖርተር እንዳስታወቁት የ TPS መቋረጥ የአሜሪካ አስተዳደር አሁን በኢትዮጵያ እየተደረጉ ባሉ የሰላም ጥረቶች እና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ያለው ዕምነት መጨመሩን የሚያሳይና ለዚህም ዕውቅና መስጠቱን አመላካች ነው።
ይህ ውሳኔ ይፋ ከመሆኑ በፊት የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ኢትዮጵያ ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና የጦር ኃይሎሽ ኤታማዦር ሹሙን ማናገራቸውን የሚገልጹና የፖለቲካ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያደረጉትን የስልክ ውይይት በማንሳት “ፊትለፊት ከማይሰሙት ሚስጥራዊ ውይይቶች በተጨማሪ ይህ ሁሉ ከሆነ በሁዋላ አሜሪካ ‘ኢትዮጵያ ብትሄዱ ምንም አትሆኑም። በስልሳ ቀን አገሬን ልቀቁና ውጡ’ ስትል አሜሪካ ማወጇ በቀላል አማርኛ እርጥብ እናቃጥል የሚያስብል ግንኙነት አልይ ነን። ይህን ዕወቁ የሚል መልዕክት ነው” ብለዋል።
“ስሜን ተወው” ሲሉ ብዙ መናገር እንደማይፈልጉ ያስታወቁት መምህሩ እንዳሉት አሁን ላይ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ቀይ ባህርና አፍሪቃ ቀንድ ላይ ያተኮረ ነው። አሜሪካ ቀይ ባህርና ምስራቅ አፍሪቃን አስመልክቶ ያላትን ጥቅም ለማስተበቅ ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ደጋግማ ይፋ ማድረጓን አመልክተው፣ “አሜሪካን ጥቅሟን አስልታ ስትቀርብ፣ ኢትዮጵያም አሜሪካ ማድረግ የሚገባትን ጉዳዮች አንስታ መደራደሯ እሙን ነው። ነገሩ በዚህ የሚቆም አይምስለኝም። ቀታይ የሚሰሙ ውሳኔዎች ስለሚኖሩ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊወስዱ የሚገባቸው ወገኖች እንዳሉ ይሰማኛል” ብለዋል።
አቶ ጸጋ አብ በበኳላቸው የአሜሪካ መንግስት ይህንን ውሳኔ የወሰነው በግምገማ ወቅት በኢትዮጵያ ግጭት እየተካሄደ ቢሆንም፣ ተመላሽ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ባለመሆኑ ነው። ከዚህም በላይ አሁን ላይ በአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ላይ ያላቸውን አዎንታዊ አመለካከት በግልጽ ለማንጸባረቅ ነው።
ስማቸውን መጥቀስ የማይፈልጉ የኦፌኮ አመራር “ ውሳኔው ለተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በተለይም አሜሪካ ላሉ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ዋናው ጉዳይ ኝ አገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ መደላድል አስፍቶ ሁሉም ሳይሸማቀቅ በአገሩ በነጻነት ባሻው አሳብ በቸዋነት ፖለቲካውን እንዲያራምድ ማመቻቸቱ ላይ ነው” ብለዋል። ስምምነቱን ኮንነውታል።
የዲፕሎማሲ ባለሙያው አሜሪካ የትግራይ ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱን እና በኦሮሚያ ክልል የተደረጉ የሰላም ስምምነቶችን ማጣቀሷ በሀገሪቱ ያለውን የጸጥታ ችግር አስጊ እንዳልሆነ አድርጎ መመልከቷን እንደሚያጎላውም ባለሙያው አመልክተዋል።
በጊዜያዊ የህግ ከለላ ስር ተጠቃሚ የነበሩ 5001 ኢትዮጵያውያን እና 263 አመልካቾች ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ በመጠበቅ የኢትዮጵያ መንግስት በአቀባበልና በመልሶ ማቋቋም ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ከወዲሁ መስራት ይገባዋል ብለዋል። ከምንም በላይ ከተመልሾች መካከል በፖለቲካ የሚሳተፉትን ማስተማመኛ መስጠት ዋና ጉዳይ እንደሆነ \ተቁመዋል።
ተመላሾችን አስመልክቶ መንግስት ምን ማድረግ እንዳለበት ከወዲሁ ያመላከቱት ባለሙያው፣ መንግስት ከግንዛቤ ውስጥ ቢያስገባው ሲሉ የተወሰኑ ነጥቦችን ዘርዝረዋል።
ልዩ የአቀባበል ማዕከላት ማቋቋም። ተመላሾች መጀመሪያ ላይ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እና መረጃ በአንድ ቦታ የሚያገኙበትን ማዕከላት ማዘጋጀት። እንዲሁም የሥራ ዕድል መፍ\ተር እና ማኅበራዊ መስተጋብራቸው እንዲፋጠንና በፍጥነት ከማህበረሰባቸው ጋር እንዲዋሃዱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት፤ ለዚሁም ይረዳ ዘንዳ የሙያ ስልጠና ፣ የንግድ መደገፊያ እና የሥራ ምደባ ዕድሎችን አቅም በፈቀደ ማመቻቸት አስፈላጊ እንደሆነ ባለሙያው ሃሳብ አቅርበዋል።
የሰብዓዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ከረጅም ጊዜ መለያየት እና ከአዲስ ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊመጣ ለሚችለው ጭንቀትና ችግር የስነ ልቦና ምክር እና ድጋፍ ማቅረብ፣ የመኖሪያ ፈቃድ እና ሰነድ ማስተካከያ አስፈላጊ የሆኑ የመታወቂያ ሰነዶችን እና የመኖሪያ ፈቃዶችን በፍጥነት እንዲያገኙ ማገዝ ተመላሾችን በስነ ልቦና ደረጃ ሊያበረታታ እንደሚችል አመልክተዋል።
ለቢቢሲ ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት አስተያየት የሰጡ የሕግ ባለሙያ ሙሉዓለም ጌታቸው እንደሚሉት፤ በ60 ቀናት አሜሪካን እንዲለቅቁ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ጉዳያቸውን ከጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ ውጭ ወደሆኑ የጥገኝነት መጠየቂያ አሠራሮች ማዞር እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ይህም ከከለላ ወደ ጥገኝነት ስታተስ መዛወር ማለት ነው።
ይህ ሲሆን የሚቀርቡ የስደተኛ ማመልከቻ ማስደገፊያ ማስረጃዎች ትክክለኛ መሆን አለባቸው። ሐሰተኛ ከሆነ የአሜሪካን መንግሥት ማታለል ወንጀል በመሆኑ ለወደፊት ሊገኝ የሚችል የስደተኞች ከለላን እንደሚያሳጣቸው ያሰምሩበታል። ጥገኝነት መጠየቅ ያልፈለጉ ግን ከየካቲት 12/2026 በፊት ከአሜሪካ መውጣት አለባቸው።
በበጎ ፈቃዳቸው ከአሜሪካ ለመውጣት (voluntary departure) የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቻቸውን በተመለከተ ለአሜሪካ መንግሥት መረጃ ቢሰጡም፤ “ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፈቃደኛነት የመውጣት ስምምነት ስለሌለ ራሳቸው ትኬት ቆርጠው መሄድ አለባቸው” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ባለሙያው አመልክተዋል። ይህን ጉዳይ እሳቸው ከማለታቸው በቀር በይፋ በወጣው መግለጫ ላይ የሰፈረ ነገር የለም።
በራስ ፈቃድ አሜሪካን ለመልቀቅ ለሚወስኑ አንድ ሺህ ዶላር ይሰጣል የሚለው አካሄድ “ለኢትዮጵያውያን የሚሠራ አልመሰለኝም” ያሉት የህግ ባለሙያ ለኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ከለላው የተሰጠው በትግራይ ጦርነት ወቅት እንደሆነ አስታውሰዋል። አክለውም “አሁንም በሌሎች ቦታዎች ጦርነቶች አሉ” በማለት መከራከር እንደሚቻል አመልክተዋል። የአሜሪካ መንግስት በመግለጫው ወደ ኢትዮጵያ ብትመስለሱ የሚደርስባችሁ አደጋ ወይም ምንም ህየሚያሰጋ ጉዳይ የለም ማለቱ አይዘነጋም። የህግ ባለሙያው አስተያየት ሲሰጡ በመግለጫው ላይ በቀጥታ ከተቀመጠው ጋር አላነጻጸሩም።
“ኢትዮጵያውያን ሊኖራቸውን የሚችለው አንደኛው የሕግ አማራጭ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የከፋ ሆኗል፤ በ60 ቀናት ውጡ መባሉ ትክክል አይደለም ብለው በፍርድ ቤት መክሰስ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የህግ ባለሙያ አሁን በከፍተኛ ስጋት ላይ ላሉት ኢትዮጵያዊያን የነጻ ሙያዊ አገልግሎት ስለመስጠታቸው ያሉት ነገር የለም። በአሜሪካ የጥብቅና አገልግሎት ውድ እንደሆነ ይታወቃል።
“ወደ ክስ ቢሄዱ [ከአሜሪካ መውጣቱን] ለጥቂት ወራት ሊያራዝመው ይችላል” ሲሉ የእፎይታ አማራጭ ምክር የሰጡት የሕግ ባለሙያው።”ሌላኛው አማራጭ መንግሥት አንድ ሺህ ዶላር እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም ተግባራዊ አልሆነም” በሚለው መክሰስ አዋጪ እንደሆነ ያመላክታሉ።
“መንግሥት አታሎናል፤ አንድ ሺ ዶላር አልሰጠንም ብለው ፍርድ ቤት ሊወስዱት ይችላሉ” ሲሉ ለቢቢሲ የገለጹት የህግ ባለሙያ ሶሪያ እና ቬንዙዌላ ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ወስደው፣ “የዜንዙዌላ ከለላ መነሳቱ ትክክል አይደለም” በሚል በታች ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውሳኔውን የማስተላለፍ ሥልጣን አለው ሲል ብይን እንደሰጠ ተናግረዋል። የህግ ባለሙያው ይህን ሲሉ ለመተንፈሻ ያህል አማራጭ አድርገው ያቀረቡት የክስ አማራጭ እንደማያስኬድ ለመተቆም ይሁን ለሌላ ቢቢሲ አላብራራም።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






