የትህነግን “ትግስቴ አለቀ” ማስጠንቀቂያ፣ “የትህነግ ረሃብን ፈጥሮ ማልቀስ ለጦርነት መለኮሻ አዋጅ” ተቃዋሚዎች

Date:

ትህነግ ሁሌም ጦርነት መለኮስ ሲያስብ እና ዓለም ዓቀፍ ትኩረት ሲፈልግ ሰው ሰራሽ ረሃብ ይፈጥራል – በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች

  • አዲስ ሪፖርተር – ትህነግ ህጻጽ የሰፈሩ ተፈናቃዮችን በረሃብ መጎዳታቸውን የሚያሳይ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ “ሳምንታዊ መልዕክት” በሚል ባወጣው መግለጫ፣ “ትዕግሴት አልቋል” ቃታ ሊስብ መቋመጡን ይፋ አድርጓል።የፌደራል መንግሥቱን የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደጣሰ ጥቅሶ ከዚህ በሁዋላ እንደማይታገስ ያስታወቀው ትህነግ፣ “የትግራይ ህዝብን በተለያዩ መንገዶች የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ቀጥሏል” በማለት ወንጅሏል። ትህነግን የሚቃወሙ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው “ከተረጂ ጉሮሮ ነጥቅህ የምትውስድ፣ ለትግራይ የሚላከውን በሙሉ ሰራዊት የምትቀልብና የምትሸጥ፣ ራስህ ረሃብን ሰርተህ ራስህ መልሰህ የምታለቅስ የትግራይ መቅሰፍት” ሲሉ ይከሱታል።

በተጠቀሰው ቦታ በርሃብ በርካታ ዜጎች መሞታቸውን የሚናገረው ትህነግ፣ ዓለም እንደዘነጋውን አስታውቋል። ፓርቲዎቹ እንደሚሉት ደግሞ ትህነግ አሁን ላይ ራሱ ፈጥሮ እያስጮከ ያለው ረሃብ ለትግራይ ሕዝብ ከመቆርቆር ሳይሆን የረሃቡ አጀንዳ የዓለምን ትኩረት እንዲስብና ያጣውን ድጋፍ ለማሰባሰቢያ ነው።

“የትግራይ ህዝብ ትህነግ እስካልተገላገለ ድረስ  የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ሁኖ ይቀራል” የሚል ተመሳሳይ አቋም የያዙትን ሶስት ፓርቲዎች አዲስ ሪፖርተር አነጋግራለች። የትህነግ የተለያዩ ባለስልጣናትን ለማካተት በእጅ ስላካቸው ሙከራ ቢደረግም አልተሳካም። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመሩት ቡድን አዲስ አበባ በመምጣት ኤምባሲዎችን፣ የተለያዩ የፌደራል ተቋማት ባለስልጣናትን ያነጋገሩ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስይትር አብይ ታደሰ ወረደን ማነጋገራቸው አይዘነጋም። ይህ ከሆነ በሁዋላ ትህነግ “ትዕግስቴ አልቋል” ሲል እጁ ቃታ ላይ እንደሆነ ማስታውቁ አነጋጋሪ ሆኗል።

የትግራይ ክልል በጦርነትና በሰላም መሃል ባለ ግራ መጋባት ውስጥ እያለ የክልሉን ሕዝብ ወካዮች ነን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትህነግ በሕዝቡ ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እና ስቃይ በተመለከተ ቆመው ተናገሩ። 

በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሳልሳይ ወያኔ ባይቶና እና ስምረት የተባሉ ፓርቲዎች እንደሚሉት ከሆነ ትህነግ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ለመሳብ እና የጦርነት ነበልባልን ለመቀስቀስ ሲያስብ ሁሌም ሰው ሰራሽ ረሃብ ይፈጥራል። ፓርቲዎቹ በግልጽ እንደገለጹት የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት እስካልተገላገለ ድረስ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ሆኖ ይቀራል ብለዋል። 

ሳልሳይ ወያኔ ምን አለ 

የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሃነ አፅባህ ለአዲስ ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ትህነግን የትግራይ ክልል ሰቆቃ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን በግልጽ አስቀምጠዋል። 

አቶ ብርሃነ እንዳሉት ትህነግ ታሪካዊ አመጣጡ ከደም ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ አሁንም  የተጠቀመበት መንገድ ሁሌም በሕዝብ ደም የመቆመር ስልት ነው። የዛሬ ሶስት ዓመት ትህነግ በተመሳሳይ መልኩ በክልሉ ከባድ ረሃብ መከሰቱን በመግለጽ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የውጭ ኃይሎች ጫና እንዲያሳድሩ ካደረገ በኋላ ጦርነት መቀስቀሱንም አንስተዋል። 

ይህ ድርጊት የትህነግን ተፈጥሮ ያሳያል ያሉት አቶ ብርሃነ፣ “ትህነግ በታሪክ ሂደት የትግራይን ሕዝብ የራሱን ስልጣን ማስጠበቂያ ወታደራዊ ጋሻ አድርጎ ሲጠቀምበት ኖሯል። በ1980ዎቹ የመጨረሻና ከዚያም በኋላ ትህነግ ያካሄዳቸው በርካታ ውጊያዎች የትግራይን ወጣት ትውልድ ገብሮ ነው” በማለት የፓርቲውን ግፍ በዝርዝር አብራርተዋል። 

አሁንም ቢሆን “የጦር መሳሪያ ለመግዛት” በሚል ሰበብ ከተፈናቃዮች እና በችግር ላይ ካሉ ዜጎች ገንዘብ እንደሚቀበል አቶ ብርሃነ ጠቁመዋል። ይህና ሌሎች መሰል ተግባሮቹ  ከሕዝብ ሥቃይ በላይ ለቡድኑ የስልጣን ጥም ቅድሚያ እንደሚሰጥ የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል። 

ከትግራይ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ረሃብ ገባበት ህጻጽ ብቻ ሳይሆን ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ትህነግ በግድ መዋጮ ይሰበስባል። በአንድ ሰው የሚሰጠውን 15 ኪሎ ስንዴ ለትህነግ ማጠናከሪያና ለሰራዊቱ ቀለብ በሚል 5ኪሎ እየቀነሰ ይወስዳል። “አንሰጥም” የሚሉ ካሉ ከስንዴ እርዳታ ፕሮግራም ያስወጣቸዋል። መመለስ ከፈለጉና እርዳታ ማግኘት ከፈለጉ በአደባባይ ግለ ሂስ ያደርጋሉ፣ ይቅርታ ይጠይቃሉ። በዚህም ምልኩ ከተረጂዎች ጉሮሮ የሚነጥቅ ድርጅት ነው “ረሃብ ገባ” ብሎ ይሚጮኸው፤ ፓርቲዎቹ ቃል በቃል ጉዳዩን ባይዘረዝሩም “ረሃብን ራሱ ፈጥሮ ራሱ የጦርነት መለኮሻና የዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሚያደርገው” ሲሉ ድርጅቱ ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ሊወርድ እንደሚገባ የሚጠቁሙት።

“ትህነግ የትግራይን ሕዝብ በእንባና በሰቆቃ ጠልፎ፣ ያጣውን ተቀባይነት ለመመለስና ለፖለቲካው ዓላማ ማዋል ማቆም አለበት” በማለት ጦርነት አማራጭ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ ብርሃነ፣ የትግራይ ሕዝቡ ከትህነግ ተላቆ በሰላም ለመኖር የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንደሚገባው አስታውቀዋል። 

ከታሪክ ማህደር መዝገብ በመነሳት ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ለስልጣን ጥሙ ሲል ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞ ያሰቃየበት ግፍ እጅግ አሳዛኝ እና የሰውን ልብ የሚነካ መሆኑን አስታውሰዋል። ኃላፊው እንዳነሱት ትህነግ ዓለም አቀፍ ትኩረት ለመሳብና ጦርነት ለመቀስቀስ ሲፈልግ ሁሉ ሰው ሰራሽ ረሃብ የመፍጠር ልምድ አለው። ይህ አሳፋሪ ድርጊት በበርካታ ጊዜያት ተደጋግሟል። 

የ1984ቱ ታላቅ ረሃብ የትግራይን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፍተኛ ሰቆቃ የጣለበት ወቅት ነበር ብለውናል። በወቅቱ ትህነግ በክልሉ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በመቆጣጠር ረሃብተኛውን ሕዝብ ከመርዳት ይልቅ ለጦርነት ዓላማው ሲጠቀምበት ኖሯል ከረሃብ አደጋ ለመዳን የመጣውን ስንቅ ለራሱ ታጋዮችና ወታደራዊ ፍላጎቶች አውሎታል ይህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች በረሃብ እንዲያልቁ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ጠቁመዋል። 

ትህነግ በረሃብ የተጎዳውን ሕዝብ ከአካባቢው በማፈናቀል ወደ ሱዳን እንዲሰደድ በማድረግ ረሃቡን እንደ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ መደራደሪያ ካርድ ተጠቅሞበታል። የተሰደዱትም ዜጎች በረሀብና በችግር ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገዋል። ትህነግ የረሃብ ሰለባዎችን የዓለምን ትኩረት ለመሳቢያ መሳሪያነት ነው የተጠቀመው ሲጠቀም ኖሯል። አሁንም እየተጠቀመ ነው።

ከ1983 ዓ.ም. በኋላም ቢሆን ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ለትግራይ ሕዝብ የሚደርሰውን ሰብዓዊና የምግብ እርዳታ የሚቆጣጠርበት እና ለፖለቲካው ዓላማ የሚጠቀምበት አሰራር ዘርግቶ እንደነበረ ነግረውናል። በሴፍቲ ኔት የሚረዳ ሕዝብ አድርጎ ያኖረውን ሕዝብ እንዳሻው ለመዳት ዕርዳታን ማስፈራሪያ አድርጎ ነው የኖረው። 

የትህነግ ካድሬዎች እርዳታ የሚሰጠው የቡድኑን የፖለቲካ አቋም ለሚደግፉ እና ለታማኝ አባላት ብቻ እንዲሆን በማድረግ ረሃብን እንደ የመግዣ መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል። ድሃውና ተጎጂው ሕዝብ እርዳታ የማግኘት መብቱን ለመጠቀም ለትህነግ መንበርከክ አለበት። ይህም በረሃብ ላይ የተጀመረ የፖለቲካ ግፍ ነው ዛሬ ድርስ የቀጠለው።  

በተለይ በቅርብ ጊዜ በተከሰተው ግጭት ትህነግ ወደ ክልሉ የሚገባውን ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብዓዊ እርዳታ በግልጽ ሲዘርፍና ለጦር ኃይሉ ሲያዘዋውር ቆይቷል። ይህ እርምጃ እርዳታው በእርግጥ ለተራበው ሕዝብ እንዳይደርስ አድርጓል ይህም ሕዝብን ለከፋ ችግር እና ለሰው ሰራሽ ረሃብ የዳረገ አሳዛኝ ተግባሩ እንደነበረ አብራርተዋል። 

በአሁኑ ወቅት በጦርነት ሳቢያ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ ተፈናቅሎ በከባድ የረሃብና የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛል። 

ትህነግ አሁንም ቢሆን የረሃብን ቀውስ ለፖለቲካና ለወታደራዊ ፍላጎቱ ይጠቀምበታል። ከተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ለጦር መሳሪያ መግዣ በሚል ሰበብ ገንዘብ በግዴታ መሰብሰቡ ከፍተኛ ግፍ ነው። ረሃብተኛው ሕዝብ ከራሱ ስቃይ በተጨማሪ ለቡድኑ የጦርነት ወጪ እንዲያዋጣ ማስገደድ ትህነግ የሰብዓዊነትን መስመር የረገጠበትን ርቀት ያሳያል ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል። 

ትህነግ የረሃብን ጉዳይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድርበት የሚጠቀምበት አጀንዳ አድርጎታል። ይህ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ስቃይ ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል እንጂ በእውነት ችግሩን ለመፍታት እንዳልፈለገ በግልፅ ማሳየቱን ጠቁመዋል። 

ትህነግ በረሃብ ሰበብ የፈጸመው ግፍ የትግራይን ሕዝብ እንባ እና ሰቆቃ ለዘመናት ያራዘመ ነው። ይህ ቡድን ሕዝብን ከመጠበቅ ይልቅ ረሃብን እንደ ስልታዊ መሳሪያ በመጠቀም የራሱን የሥልጣን ፍላጎት አስቀድሟል። የትግራይ ሕዝብ በትህነግ ሲደርስበት የኖረውና እየደረሰበት ያለው ግፍ የታሪክ ቁስል ሆኖ ይመዘገባል። 

ባይቶና ምን አለ 

የባይቶና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ክብሮም በርሄ  በበኩላቸው ፤ በትህነግ ድርጊት የተነሳ የትግራይ ሕዝብ የደረሰበትን ሰቆቃ ተዘርዝሮ አያልቅም ባይ ናቸው። 

የትህነግ ዋና ዓላማ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያዝንለትና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲፈጥርበት ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። ረሃብና ሰብዓዊ ቀውስ ለትህነግ የፖለቲካ መሳሪያ እንጂ የሕዝብ ስቃይ አለመሆኑን በተጨባጭ ያሳያል ብለዋል። 

ባለፉት ዓመታት ትህነግ ስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ ሁሉ የትግራይን ወጣት ለጦር ግንባር አስገድዶ በማሰለፍ በርካቶችን እንዲያልቁ አድርጓል። ይህም የትህነግ ታሪካዊ የጭካኔ አካል ነው። ይህ ቡድን የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የክልሉን ሕዝብ በተለይም አቅመ ደካሞችን እና ሴቶችን ለከፋ ድርጊት አሳልፎ ሰጥቷል ብለዋል። 

የትግራይ ሕዝብ ስሙ የፖለቲካ መደራደሪያ መሆን አለበት ወይ የሚለው ጥያቄ በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንደ እሳት የሚፋጅ ነው አሁንም ቢሆን በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሰፈረው የከፋ ችግር እንደ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ እየተጠቀመበት መሆኑ ትህነግ የሰብዓዊነትን መስመር የረገጠበትን ጥልቀት ያሳያል ብለዋል። 

የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በኋላ በትህነግ መዳፍ ስር ሆኖ የጦርነት ቁማር መጫወቻ ሆኖ መቅረት የለበትም ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

ስምረት ፓርቲ ምን አለ?

ዲሞክራሲያዊ ትግራይ ስምረት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ ገብረኢየሱስ ፤ ትህነግ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ሳይሆን የሰቆቃ ፈጣሪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ሁሌም የሚንቀሳቀስ የአብዮት ነዳጅ አድርጎ ነው የሚቆጥረው። የሕዝቡ እንባ እና መከራ ለትህነግ የፖለቲካ ትርፍ ምንጭ ነው። ይህ ቡድን ኃይልን እና ፍርሃትን ተጠቅሞ ሕዝብን ለጥቅሙ አስገዝቶ ኖሯል ብለዋል። 

በታሪክም ቢሆን ትህነግ የትግራይን ወጣት ለእልቂት ሲመራ መቆየቱን እያጣቀሱ አስረድተዋል አሁን እየተፈጠረ ያለው ሰው ሰራሽ ረሃብ የትህነግ ስትራቴጂ አካል መሆኑን በመግለጽ ዓላማው ጦርነትን መልሶ መቀስቀስ መሆኑን ተናግረዋል። 

የትህነግ አመራሮች በቅንጦት እየኖሩ የትግራይ ሕዝብ ለርሃብ መጋለጡ ትልቅ የፍትህ መጓደል ነው ሲሉ አስምረውበታል። 

ከዚህ በላይ ደግሞ ለተፈናቃዮች የተላከውን ሰብዓዊ እርዳታ ለራሱ ዓላማ ሲጠቀምበትና ከተፈናቃዮች ለጦር መሳሪያ መግዣ ገንዘብ ሲሰበስብ መቆየቱን በዝርዝር አስረድተዋል። 

የትግራይ ሕዝብ የሰብዓዊ መብቱ ተከብሮ የራሱን የፖለቲካ ምርጫ በነጻነት መወሰን የሚችለው ከሕወሓት የብረት ቀንበር ሲላቀቅ ብቻ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ደምድመዋል። 

ፓርቲዎቹ በጋራ ባስተላለፉት መልእክት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የትህነግን እውነተኛ ባህሪ እንዲረዳና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያሳድረውን የፖለቲካ ጫና እንዲያቆም ጥሪ አስተላልፈዋል የትግራይ ሕዝብ ከዚህ የፖለቲካ ቁማር እስካልተላቀቀ ድረስ ሰቆቃው መቀጠሉ አይቀሬ ነው ብለዋል ፓርቲዎቹ። 

የእነዚህ ፓርቲዎች ድምጽ የትግራይ ሕዝብ የደረሰበትን መከራ እና የትህነግን ግፍ የሚገልጽ አሳዛኝ እውነታ ነው።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የአዲስ አበባ ሕዝብ የእናት ሀገር ጥሪ ተሳትፎና ኮሎኔል መንግሥቱ

የእናት አገር ጥሪ ከተደረገ በኋላ መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ...

ቢሾፍቱ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ፤ ኢትዮጵያን ወደ መፃኤ ዘመን የሚያሻግር የሎጂስቲክስ አብዮት

ኢትዮጵያ ከቢሾፍቱ ሰማይ ስር የኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ካርታዋን እንደገና ለመሳል...

“ጥርስ የሌለው ውሻ” የሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም መፃኢ እጣፈንታ

አዲስ ሪፖርተር - ፕሬዛዳንት ትራምፕ አሜሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት...

በዘመነ ትራምፕ ጫና ውስጥ የወደቀችው ሶማሊያ እና ለሶማሌ ላንድ ተስፋን ያለመለመው አዋጅ

አዲስ ሪፓርተር - ከሶማሌላንድ የሉዓላዊነት ጥያቄ እና ከእስራኤል እውቅና...