አዲስ ሪፖርተር ትግራይ – የጦርነት ወሬ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አንደበት መሰማቱን በመጠቀሰ በተለያዩ አውዶች መረጃዎች እየተሰራጩ ነው። ይህ መረጃ የወጣው ጄኔራሉ የህጻጽን ወቅታዊ ሁኔታና የአዲስ አበባ ቆይታቸውን አስመልክቶ በትግራይ ቴሌቪዥን የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ነው። ይህ የሰሙ ሌላ ጄኔራል “እመነኝ ትህነግ ጦርነት አይጀምረም” ብለዋል፤ የሁለቱ መኮንኖች ወግ!
እርግጥ ከትግራይ ጦርነት ይለኮሳል? የሚለውን ጉዳይ፣ ጦርነት የሚፈልጉና በጦርነቱ ሊያተርፉ የሚፈልጉ አካላት ምኞት ወይስ ሌላ በሚሉት ጉዳዮች ዙርሪያ የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ የቀደሙና የአሁኑን መረጃዎች አሰባስቦ ልኳል። ዝግጅት ክፍሉ አግባብነት ያላቸውን መረጃዎች አካቶ ሪፖርት አዘጋጅቷል።
“እመነኝ” ይላሉ ለዛሬ ስማቸው የማይነሳው የጦር መኮንኑ፣ “እመነኝ የመጨረሻው ቀን ሲመጣ ስሜን ጠብቄ ነው በክብር የምሞተው” ይላሉ። “ምን ማለትዎ ነው?” ሲል የዛሬው የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ ይጠይቃል። “ተማርኬ ወይም እጄን ሰጥቼ አልዋረደም” ሲሉ ከዓመት በፊት የተናገሩት እኚህ ጄኔራል በወርቅ ንግድ ከጠገቡት መካከል አንዱ ናቸው። እናም እሳቸው “የመጨረሻ” ያሉት ጊዜ ሲመጣ ሊፈጽሙ ያሰቡት ገድል ይህ ነው። እስከዛው ግን ወርቅ እያረሱ ነው።
ተባባሪያችን ይህን ያነሳው አሁን ላይ “ሰላም” ብለው አዲስ አበባ የተቀመጡ ሌላ የጦር መኮንን “እመነኝ ትህነግ ጦርነት አይከፍትም” ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ “ወደ ጦርነት ልንገባ እንችላለን” ሲሉ ትናንት ማምሻውን በትግራይ ቴሌቪዥን ለትግራይ ሕዝብ ከተናገሩት ጋር ለማያያዝ ነው። “እጅ አልሰጥም” ያሉት ጄኔራል የተካተቱት ግን የትግራይን ሕዝብ ለሚያስቡ ሁሉ ማጣቀሻ እንዲሆን ነው።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር መሪ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል ያመላከቱት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ነው። እነሱም ከ1983 በኋላ ወደ ትግራይ ተካተው “ምዕራብ ትግራይ” የተባሉት የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ሁመራ አካባቢዎች ወደ ትግራይ ካልተካተቱና፣ እንዲሁም ተፈናቃዮች በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ ቀዬያቸው ካልተመለሱ ነው።
የጄኔራሉና ልዑካቸው አዲስ አበባ ቆይታ
ታደሰ ወረደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው የመጡት የክልሉ ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እንዲያናገሩ ፈቃድ አላገኙም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተነጋገሩት እሳቸው ብቻ ናቸው። ለትግራይ ሕዝብ በትግርኛ ቋንቋ የአዲስ አበባ ቆይታቸውን አስመልክቶ ሲናገሩ በአብዛኛው የመከሩባቸው ጉዳዮች በስኬትና በመግባባት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በርካታ ጉዳዮች ላይ የፌደራል መንግስት የትግራይን ጊዚያዊ አስተዳደር መውቀሱንና ማስጠንቀቁን፣ ከምንም በላይ ከክልሎች ህገመንግስታዊ ገደብና መብት ዘለው ከሻዕቢያ ጋር የሚያደርጉትን ስርዓት የለቀቀ ግንኙነት፣ ፋኖን ጨምሮ ከተጣቂ ኃይሎች ጋር እያከናወኑ ያሉትን መረን የወጣ አካሄድ እንዲያቆሙ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን፣እንደ ማንኛውም ክልል ስርዓት እንዲያከብሩ የተሰጠውን መመሪያና እሳቸውም የተስማሙበትን በዝርዝር ባይገልጹም፣ ገደብ የጣለበት በጀት፣ የደሞዝ ገንዘብና የታገዱ የድርጅቱ የንግድ ተቋማት አካውንቶች እንዲከፈቱ ከስምምነት መደረሱን በበጎ መልኩ ተናግረዋል
ስለ ምርጫ
ምርጫ በትግራይ ይካሄዳል አይካሄድም በሚለው አግባብ ከምርጫ ቦርድ ጋር ውይይት መደረጉን ታደሰ ወረደ አስታውቀዋል። በዚህም ከቦርዱ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰው፣ ቦርዱ ከመንግስት ጋር በጸጥታ ጉዳዮችና ምርጫ ለማካሄድ ያሉት አስቻይ ሁኔታዎች ስለመኖራቸውና አለመኖራቸው መረጃ ከወደዱና የራሳቸውን ዳሰሳ ከሰሩ በሁዋላ እንደሚያሳውቋቸው ግልጽ አድረገዋል።
“… ጦርነት አይነሳም ማለት አይደለም”
ተፈናቃዮችን አስመልክቶ፣ በተለይም የህጻጽን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ታደሰ ወረደ ሲናገሩ ያተኮሩት ስለ ዘላቂ መፍትሄ ነው። የተመጠነና እንደ መሪ በጥንቃቄ በገለጹት የተፈናቃዮች ጉዳይ በሕፃፅን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ 146 የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።
የፊደራሉ አደጋና ስጋት መከላከል የሰጠውንና እያሰጠ ያለውን ድጋፍ በዝርዝር ጠቅሰው ማነሱንና እጥረት መፈጠሩን፣ እንዲሁም ጉድለት መታየቱን ያላስረዱት የትግራይ መሪ፣ ተፈናቃዮች ካልተመለሱ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል አመላክተዋል።
ጦርነት እንዳይነሳ አበክረው እየሰሩ መሆኑን፣ ሁሉንም ጉዳይ በውይይት ለመጨረስ እንደሚተጉ አየተናገሩት ታደሰ ወረደ “ይህ ማለት ግን ጦርነት ሙሉ በሙሉ ይቀራል ማለት አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል። ምህንያታቸው ደግሞ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ወደ ትግራይ ተካቶ “ምዕራብ ትግራይ” የተባለው አካባቢ ወደ ትግራ ካልተመለሰና ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ካልተደረገ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ ታደሰ ወረደ ያሰቀመጡት እንደ ቅድመ ሁኔታ ነው።
ትግራይ ውስጥ ርሃን ስለመፈጠሩና ትግራይ ውስጥ ተፈጠረ የተባለው የምግብ እጥረት የተለያዩ መረጃዎች ቢቀርቡበትም ጄኔራሉ “ለረሀቡ ዘላቂ መፍትሔ ተፈናቃዮችን መመለስ ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን ጦርነትን ማስቀረት አይቻልም” ብለዋል። አክለውም በበጀት ዓመቱ የግድ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው መመለስ እንዳለባቸው አመልክተዋል። እስካሁን ተፈናቃዮች ለምን ሊመለሱ እንዳልቻሉ ባይገልጹም፣ “ካልተመለሱ ግን ጦርነት መፍትሔ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
የፌደራል መንግስት የተጠቀሱት አወዛጋቢ ቦታዎች ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ሲደረግ ጀምሮ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ይህንን ጥያቄ ተከትሎ ሰፊ ችግር፣ በደል፣ ግፍ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያና ወዘተ እንደተፈጸመ ከሁሉም ወገን የሚነሳበት በመሆኑ አካባቢዎቹን የአገር መከላከያ እየተቆጣጠረ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው ይመለሱና ሲረጋጋ ሕዝብ ይወስን የሚል አቋም እንዳለው በተደጋጋሚ በተለያዩ መደረኮች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ለዚህም አስተዳደሩን ጨምሮ ሙሉ መዋቅሩ እንዴት እንደሚዋቀር ዝርዝር መቅረቡም ሲገለጽ ቆይቷል።
አሁን አካባቢዎቹን የሚያስተዳድሩትም ሆኑ ራሱ የአማራ ክልልም ከትግራይ ክልል ታጣቂዎች ተመልሰው እንዲመጡ አይፈቅዱም። በተለይ ዞኑ በወንጀል የሚፈለጉ፣ ቀደም ሲል በሕዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙ በመሆናቸው በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸው መሆኑን ነው የሚናገረው። ከዚህም በላይ የተከዜ ዘብ ብሎ ሰፊ ሰራዊት በማደራጀት ድንገት እንኳን ጦርነት ቢነሳ ለመከላከል ብቁ ዝግጅት ማድረጉን እያስታወቀ ነው።
ገለልተኛ አካላት እንደሚሉት ከሆነ የፊደራል መንግስት ያቀረበውን ዕቅድ በመቀበል የሚጨመሩና የሚቀነሱ አሰራሮችና ደንቦችን በማከል ተፈናቃዮች በአስቸኳይ ወደ መንደራቸው እንዲመለሱና በቀጣይ ህገመንግስታዊ መፍትሄ መፈለጉ ላይ ያተኩራሉ። በተለይም ብሄርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገውን ከፋፋይ ህገመንግስት ማስወገድ ክርክሩን ለመቅረፍ ዋንኛ ጉዳይ ነው።
“በትግራይ ጦርነት አይነሳም እመነኝ”
ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ከፍተኛ የጦር መኮንን ጦርነት እንደማይነሳ እርገጠኛ ናቸው። “እመነኝ ጦርነት አይነሳም” ያሉት መኮንኑ፣ ትህነግ አሁን ላይ ጦርነት እንዲጀመር የሚፈቅድለት አመቺ ሁኔታ የለውም።
መኮንኑ እንደሚሉት ኢህነግ ቀደም ሲል ባደረጋቸው ጦርነቶች ሁሉ ሕዝብ ከጎኑ ነበር። አሁን ላይ ግን ያንን ያላቅ ሎጂስቲክ ከስሯል። እሳቸውን ጨምሮ የትሀነግን አጀንዳ የሚገዙ የትግራይ ተወላጆች እንደቀድሞ አይኖሩም። ይህ እውነታ በእነሱም ዘንድ ስላለ ዘለው ወደ ጦርነት ይገባሉ ተብሎ አይታሰብም። በአጭሩ ሕዝብ ከጎናቸው እንዳልሆነ ያውቃሉ።
“በሌላ በኩል ሕዝቡ በጦርነት ተማሯል። አሁን ላይ ትግራይ ውስጥ እንኳን ጦርነት ተራ ጸብ የሰለቸው፣ ሰላም የናፈቀው፣ ከካምፕ ወጥቶ በሰላም በቤቱ መኖር የሚፈልግ ሕዝብ ነው ያለው። ይህንን እውነት እነ ደብረጽዮን ይረዱታል” የሚሉት መኮንኑ ስለ ሰራዊቱም ያነሳሉ።
እሳቸው ባላቸው መረጃና በቅርብ እንደሚከታተሉት ከሆነ በትግራይ ጦርነት ቢለኮስ መዋጋት የሚፈልግ፣ ስነ ልቦናው ለጦርነት ዝግጁ የሆነ፣ ለሚቀሰቀሰው ጦርነት ዓላማ የሚገዛ የሰራዊት አባላት የሉም። “እውነቱን ነገረኝ ካልክ ሰራዊቱ በመልሶ ማቋቋም የተሰጠውን ወስዶ ጎጆ ቀልሶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ የሚፈልግ ነው” የሚሉት መኮንኑ፣ የትህነግ የተወሰኑ ቡድኖች ሰራዊቱን የሚፈልጉት ለማስፈራሪያ እንጂ ለትግራይ ምንም ሊፈይዱ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
እርግጥ የጦር አመራሮች ከጅምሩ ሲደራጁ በአምቻ ጋብቻ እንዲሆን ሆን ተብሎ መደረጉን የሚያወሱት መኮንኑ ከፍተኛ አዛዦች የስብሃትን ቤተሰቦች በትዳር ሆን ተብሎ እንዲቆራኙ መደረጉን ይናገራሉ። አክለውም እነዚህ መኮንኖች በጽናት ሊቆዩ ይችሉ ካልሆነ ሌላው ካሁን በሁዋላ ለአንድ ቡድን የሚሞትበት ምንም ጉዳይ እንደሌለው ሕዝብ በግልጽ “ካሁን በኋላ አልሞትም” ሲል መደመጡን ይጠቅሳሉ።
“እዛም እዚህም ሕዝብን የማይጠቅም አጀንዳ ውስጥ እየተነከረ ያለው ትህነግ ከሻዕቢያ ጋር የጀመረው ጽምዶም ከሽፎበታል” ያሉት መኮንኑ “ትናንት ጽምዶ ጽምዶ እያሉ ሲጮሁ የነበሩ የኤርትራ አክቲቪስቶች ዛሬ ስድብ ጀምረዋል። እንኳን ተራባችሁ እያሉ እየተዛበቱ ነው” ሲሉ በቁጭት የትህነግ መሪዎች የትግራይን ሕዝብ መሳለቂያ እያደረጉት መሆኑን አመልክተዋል። እሳቸው ባይገልጹትም “ሻዕቢያን የቀረብነው ለስትራቴጂ ነው። ሻዕቢያ አይታመንም” የሚለው የድምጽ መረጃ ከወጣ በሁዋላ ነገሮች መቀያየራቸውን የሁለቱን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ በተደጋጋሚ መናገራቸው አይዘነጋም።
መኮንኑ እንደሚሉት የትግራይ ሁኔታ በዚ አይቀጥልም። ወደ አንድ ማብቂያ እያመራ በመሆኑ ሕዝቡን መልሶ ለማነሳሳትና የነፈገውን ድጋፍ ለማነሳሳት አሁን ላይ የሚደረጉ ጥረቶችና ቅስቀሳዎች ብዙም የሚሳካ አይሆንም። ነገሮች ወደ ማብቂያቸው አይሄዱም።
“የመጨረሻው ጊዜ ሲደርስ ተዋግቼ እሞታለሁ”
“እጄን አልሰጥም ወይም አልማረክም” የሚሉት አሁን ላይ በወርቅ ንግድ ውስጥ ስማቸው ከሚነሱት አንዱ መኮንን ናቸው። ከዓመት በፊት ለተባባሪያችን ቡና እየጠጡ ይህን ያሉት መኮንን፣ “የመጨረሻው ሲደርስ” ያሉትን ጊዜ ዘርዝረው ባያስረዱም “የክብር” ያሉትን ሞት እንደሚመርጡ አመልክተዋል። “የትግራይ ነገር በዚህ አይቀጥልም” ሲሉ ከዓመት በፊት የተናገሩት እኚሁ ጄኔራል ምን ቢሆን እሳቸውም ሆኑ የትግራይ ሕዝብ በሰላም ሊኖሩ እንደሚችሉ አላመላከቱም። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ምዕራብ ትግራይ ሲመለስ ትግራይ አገር እንድትሆን ምኞት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ራያና “ምዕራብ ትግራይ”
በፕሪቶርያ ስምምነት ውስጥ ቁልፍ ተደራዳሪ የነበሩት የቀድሞ የህወሃት አባል እና የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ African Report ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ስለ በፕሪቶርያው ስምምነት ወቅት ስለነበሩት ጉዳዮች እንዲሁም በቅርቡ በአልጀዚራ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።
አቶ ጌታቸው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ተዋጊዎች መካከል የተነሳውን የዘመናችንን አስከፊ ጦርነት እንደማስቆሙ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንደሆነ አንስተዋል። አቶ ጌታቸው ቀጥለውም “የፕሪቶሪያ ስምምነት ጦርነቱን አስቁሟል ነገር ግን ዘላቂ ሰላም አላስገኘም።” በማለት በምክንያት አስረድተዋል።
ስምምነቱ ስለተፈፀመበት ሁኔታ ያነሱት አቶ ጌታቸው በወቅቱ የትግራይ ተወካዮች ወደ ድርድሩ ሲቀርቡ በወቅቱ ውሳኔ ሰጪ አካል ከነበረው ከማዕከላዊ እዝ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱ እንዲቆም የተሰጠው ጥብቅ መመሪያ ይዞ እንደበር ተናግረዋል።
“እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 2 ቀን 2022 ስምምነቱ ሊፈረም በነበረበት ቀን ደብረጽዮን ሁኔታው ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በማሳሰብ እንዲህ ሲል መልእክት ላከልኝ ‘ሰላም፣ አዲግራት በጠላቶች እጅ ልትወድቅ ነው የተደረሰው ስምምነት ዛሬ መፈረም ከቻለ ያ ጥሩ ይሆናል። ካልሆነ ግን ዛሬ ማታ ትግላችንን እንዴት እንደምንቀጥል እና መፈጸም እንደምንጀምር ስልታዊ ውሳኔያችንን እንወስናለን።’ “ በማለት የቀድሞ የህውሃት ሊቀመበር ደብረፅዮን ለስምምነቱ መፈረም የነበራቸውን መጣደፍና እና ፍላጎት በግልጽ ጽፈዋል።
በድርድሩ ወቅት የምዕራብ ትግራይ እና ራያ የጊዜያዊ አስተዳደር ጥያቄ እንዲሁም የፌደራል መንግስት ወታደሮችን የማስለቀቁ ጥያቄ ችላ የተባለ ሳይሆን ሆን ተብሎ ከድርድሩ እንደወጣ ያነሱ ሲሆን “ምክኒያቱ ግልፅ ነው ስለዚህ ካወራን ድርድሩ ይፈርሳል።” ሲሉ ተናግረዋል። እናም የአከራካሪዎቹ ስፍራዎች ጉዳይ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ወደ ትግራይ እንዲመለሱ አስገዳጅ አልነበረም።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






