የአፍሪካ ህብረት የእስራኤልን የሶማሊላንድ እውቅና በጽኑ አወገዘ፤ “ቢቃወምም አቅም የለውም”

Date:

አዲስ ሪፓርተር – በቅርቡ በትረ ስልጣኑን የተረከቡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ይፋዊ እውቅና በማስመልከት ጠንካራ መግለጫ አውጥተዋል። መገለጫው የሚጠበቅ ቢሆንም አፍሪካ ሕብረት አቋሙን የሚተገብርበት አቅም እንደሌለው አዲስ ሪፖርተር ያናገራቸው ዲፕሎማት አመልክተዋል።

የጅቡቲ ተወላጅ የሆኑት ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው፣ ህብረቱ ለማንኛውም ዓይነት የሶማሊላንድ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና ያለውን ፍጹም ተቃውሞ የገለጹ ሲሆን፣ ሶማሊላንድ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የማይነጣጠል የግዛት አካል መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ይህ የእስራኤል ውሳኔ የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥልና በዲፕሎማሲያዊው መድረክ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ህብረቱ አስታውቋል።

ሊቀመንበሩ መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዋናነት የአፍሪካ ህብረት የአገራትን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የማክበር ጽኑ አቋም እንዳለው አሳስበዋል። በተለይም እ.ኤ.አ በ1964 በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) የተወሰነውንና የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ የነበራቸውን ድንበር የመጠበቅ መርህን ህብረቱ በጥብቅ እንደሚከተል ገልጸዋል። በመሆኑም ሶማሊላንድን እንደ ገለልተኛ ሀገር እውቅና ለመስጠት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የአፍሪካ ህብረትን መመስረቻ ስምምነት  (Constitutive Act) የሚጥስና የአህጉሪቱን የሕግ ማዕቀፍ የሚጋፋ መሆኑን በመግለጫው በዝርዝር አስፍረዋል።

በተጨማሪም ማንኛውም የሶማሊያን አንድነት እና የግዛት ሉዓላዊነት የሚንድ እርምጃ በመላው አፍሪካ ለሚነሱ ሌሎች የመገንጠል ጥያቄዎች እንደ “አደገኛ ልምድ” ሊያገለግል እንደሚችል ሊቀመንበሩ አስጠንቅቀዋል። እንዲህ ያለው አካሄድ በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በመላው አህጉሪቱ ለሚገኙና የመገንጠል ስጋት ያለባቸው አገራት ትልቅ የደህንነት ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአፍሪካ ህብረት መርሆዎች ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ይህ እርምጃ በቀጠናው ላይ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችልም አክለዋል።

በመጨረሻም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ለሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት ያለውን የማይናወጥ ድጋፍ አረጋግጧል። የሶማሊያ ባለስልጣናት ሰላምን ለማስፈን፣ የመንግስት ተቋማትን ለማጠናከር እና ሁሉን አቀፍ አስተዳደርን ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ህብረቱ ከጎናቸው ሆኖ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

አዲስ ሪፓርተር በሕብረቱ መግለጫ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቃቸው ዲፕሎማት ሕብረቱ የሀገራትን የግዛት አንድነት የመጠበቅ ታሪካዊና ሕጋዊ ግዴታ ስላለበት እንዲህ ያለውን የተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ የሚጠበቅና ተገቢ ነው። በተግባር ግን አፍሪካ ሕዝብረት እንደ እስራኤል ያሉ ኃያላን ሀገራት የሚወስኑትን ሉዓላዊ ውሳኔ ለመቀልበስ የሚያስችል አስገዳጅ የሕግ መዋቅርም ሆነ የፖለቲካ ጡንቻ የለውም ብለዋል።

ይህ የሚያሳየው የአፍሪካ ሕብረት ተፅዕኖ በሞራልና በፖለቲካዊ መግለጫዎች ላይ የተገደበ መሆኑንና አባል ሀገራት ወይም የውጭ ኃይሎች የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም መሠረት አድርገው የሚወስዱትን እርምጃ ለማስቆም አቅም እንደሚያንሰው ነው።

ዲፕሎማቱ እንዳብራሩት፣ የአፍሪካ ሕብረት መዋቅራዊ ሥርዓት በአባል ሀገራት ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ አንድ ሉዓላዊ ሀገር (ለምሳሌ እስራኤል) ከሌላ አካል (ለምሳሌ ሶማሊላንድ) ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት ቢወስን ሕብረቱ ሊጠቀምበት የሚችል ምንም ዓይነት ማዕቀብ ወይም የቅጣት እርምጃ የለም። ሕብረቱ በመግለጫው “አደገኛ ልምድ” ይፈጥራል በማለት ስጋቱን ቢገልጽም፣ ዓለም አቀፋዊው ሥርዓት ግን በተጨባጭ ኃይልና በስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም እስራኤል በቀጠናው ያላትን ወታደራዊና የደህንነት ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ስትል የወሰደችው እርምጃ፣ ከሕብረቱ መግለጫ በላይ ሚዛን እንደሚደፋና የሶማሊላንድን የዓለም አቀፍ እውቅና ጉዞ ሕብረቱ ሊያቆመው የማይችል አዲስ ምዕራፍ ውስጥ እንደከተተው ዲፕሎማቱ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሕብረቱ በውስጥ አባል ሀገራቱ መካከል ያለው መከፋፈል ሌላው የአቅም ማነስ ምንጭ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ምንም እንኳን የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ጠንካራ መግለጫ ቢያወጡም፣ በአባል ሀገራቱ መካከል (ለምሳሌ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል) ያለው የተለያየ አቋም ሕብረቱ ወጥና አስገዳጅ ውሳኔ እንዳያሳልፍ እግርና እጁን ያስረዋል። ዲፕሎማቱ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ሕብረት መርሆቹን ከመግለጽ ባለፈ አዲሱን የጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታ ተቀብሎ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከማሳሰብ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም። ይህም ሶማሊላንድ በሂደት የምታገኘው እውቅና በሕብረቱ የተቃውሞ መግለጫ ብቻ የሚቆም ሳይሆን፣ በታላላቅ ኃይሎች ፍላጎትና በቀጠናው ነባራዊ ሁኔታ የሚወሰን መሆኑን ያረጋግጣል።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የአዲስ አበባ ሕዝብ የእናት ሀገር ጥሪ ተሳትፎና ኮሎኔል መንግሥቱ

የእናት አገር ጥሪ ከተደረገ በኋላ መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ...

ቢሾፍቱ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ፤ ኢትዮጵያን ወደ መፃኤ ዘመን የሚያሻግር የሎጂስቲክስ አብዮት

ኢትዮጵያ ከቢሾፍቱ ሰማይ ስር የኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ካርታዋን እንደገና ለመሳል...

“ጥርስ የሌለው ውሻ” የሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም መፃኢ እጣፈንታ

አዲስ ሪፖርተር - ፕሬዛዳንት ትራምፕ አሜሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት...

በዘመነ ትራምፕ ጫና ውስጥ የወደቀችው ሶማሊያ እና ለሶማሌ ላንድ ተስፋን ያለመለመው አዋጅ

አዲስ ሪፓርተር - ከሶማሌላንድ የሉዓላዊነት ጥያቄ እና ከእስራኤል እውቅና...