አዲስ ሪፓርተር – በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች ማለትም የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (RSADO) እና የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ (EANC) የኤርትራን አምባ ገነን መንግስት በጋራ ለመታገል ተስማሙ። የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዲ ሼኽ መሐመድ “26 ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር በትግል ኖረናል የወደፊቱን ሲደርስ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ ለአዲስ ሪፖርተር ተናግረዋል። ስምምነቱ ለሻዕቢያ አስደንጋጭ እንደሆነ አመልክተዋል።
ድርጅቶቹ ባጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በኤርትራ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና የአፋር ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ እንዲከበር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቁ። ድርጅቶቹ ይህንን መግለጫ ያወጡት በቅርቡ በተካሄደው የ”ሆርን ቪዥን 1″ (Horn Vision 1) የጎንዮሽ ስብሰባ ላይ በቀጠናዊ ጉዳዮች እና በኤርትራ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ከመከሩ በኋላ ነው።

የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (RSADO) ዋና ጽሐፊ በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ የተደረገው ይህ የጋራ ስምምነት አምባገነኑንና በቀይ ባህር አፋሮች ላይ ጄኖሳይድ፣ ስደትና፣ እንግልት ለሚፈጽመው የሻዕቢያ አገዛዝ የውደቀቱ መርዶ ነው።
ድርጅቶቹ በመግለጫቸው የራስን ዕድል በራስ መወሰን በዓለም አቀፍ ሕግ የተደገፈ የማይገሰስ ፖለቲካዊና ሕጋዊ መብት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል። ትግላቸውም ለበርካታ አስርተ ዓመታት የቆየውን መገለልና አምባገነናዊ አገዛዝ በማቆም፤ ነፃነት፣ እኩልነት እና ሰብአዊ ክብር የተረጋገጠባትን ፍትሃዊት ኤርትራን ለመገንባት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የራስን በራስ ዕድል የመወሰን ትግል ሲሉ ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ምን ማለት እንደሆነ ለተጠየቁት “ጥሩ ጉርብትና” ያሉት አብዲ ሼኽ መሐመድ፣ “26 ዓመታትን ከኢትዮጵያ ጋር በትግል ኖረናል። የወደፊቱን ሲደርስ ይፋ እናደርገዋለን” ብለዋል።
በኤርትራ ለሚታየው ጭቆና እና ለቀጠናው አለመረጋጋት ዋነኛው ተጠያቂ ገዢው የሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ (ህግደፍ) መሆኑን በመግለጫቸው የጠቀሱት ድርጅቶቹ፣ ይህን አምባገነናዊ ሥርዓት በጋራ ለመታገልና ለማስወገድ መስማማታቸውን ገልጸዋል። በጭቆና ላይ የሚደረግ ተቃውሞ በአለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት ያለው መሆኑን በመጥቀስ፣ ሁሉም የአፋር ኃይሎች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩና ማህበረሰቡም ለቀይ ባሕር አፋር ህዝብ ፍትሃዊ ጥያቄ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ከኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ ጋር የተደረገው ስምምነት ቢዘገይም እጅግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያስታወቁት አብዲ ሼኽ፣ “ቀደም ሲል እንደ አንድ ማህበረሰብ ግፍ እየተፈጸመብን፣ አብረን መታገል ሲገባን በተናጠል በመታገል ለአምባገንኑ የኢሳያስ መንግስት ጉልበት ሆነን ነበር። ይህ ትልቅ ስምምነት ነው። ወደፊት በርካታ ጉዳዮች ይፋ ይሆናሉ” ብለዋል። ሌሎችም ወደ ትብብሩ እንደሚመጡ አመልክተዋል።
የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ ቀደም ሲል በሰላማዊ ትግል እንደሚያምንና በአብዛኛው በውጭ አገር ባሉ አመራሮቹ የዲፕሎማሲ ትግል ሲመራ ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የሻዕቢያን የከፋ ግፍና ጄኖሳይድ ለማስወገድ ፊቱን ወደ ትጥቅ ትግል እንደሚያዞር ማስታወቅ ጀምሮ ነበር።
አዲስ ሪፓርተር የዚህ መግለጫ ቀጠናዊ አንድምታ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጥያቄ ያቀረበችላቸው የአዲስ አበባ ዩንቨሰርሰቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህር እንደገለፁት፣ “የሁለቱ ድርጅቶች ጥምረት ከውስጥ ከኤርትራ ውስጣዊ ፖለቲካ ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ አለው” ብለዋል።
የአፋር ሕዝብ በስትራቴጂካዊው የቀይ ባሕር መስመር፣ በተለይም በዓለም ዓቀፍ የንግድ መስመርና በወደብ አካባቢዎች የሚኖር በመሆኑ፣ የእነዚህ ድርጅቶች መቀናጀት በኤርትራ የባሕር ጠረፍ ላይ ያለውን የኃይል ሚዛን ሊቀይረው ይችላል። ድርጅቶቹ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን አጥብቀው ማንሳታቸው፣ በኤርትራ የወደፊት የባሕር በር አስተዳደር እና በቀጠናዊ የጸጥታ ትብብር ላይ አዲስ አቅጣጫ ሊጠቁም የሚችል ክስተት ተደርጎ እንደሚታይ ገልፀዋል።
በተጨማሪም፣ ይህ ስምምነት በስኬት ከተጠናቀቀ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ አገራትን ግንኙነት ሊያወሳስብ ወይም አዲስ መልክ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ድርጅቶቹ መግለጫውን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ማውጣታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራ ተቃዋሚዎች የሚሰጠውን ድጋፍ ወይም የቀጠናዊ ተጽዕኖ ፍላጎቱን ሊያሳይ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። በተለይም ኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር ለመድረስ ካላት ጉልህ ፍላጎት አንጻር፣ ከቀይ ባሕር አፋር ድርጅቶች ጋር የሚኖር የፖለቲካ መናበብ በቀጠናው አዲስ ስትራቴጂካዊ ትብብርን ሊወልድ ይችላል ብለዋል።

በአጠቃላይ፣ የሁለቱ ድርጅቶች የጋራ አቋም በኤርትራ ያለውን የአምባገነን ሥርዓት ለመቃወም ብቻ ሳይሆን፣ በቀይ ባሕር ዙሪያ ለሚካሄደው ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ የኃይል ፍልሚያ አዲስ ተለዋዋጭ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህ ጥምረት የአፋርን ሕዝብ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ከማስተጋባቱም በላይ፣ በኤርትራ እና በጎረቤት አገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አዲስ መልክ ሊፈጥር እንደሚችል ይጠበቃል፡
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






