የፕሮፌሰሩ እይታ “ጠንቋይ የሰዉን እንጂ የራሱን አያዉቅም” አብይ አሕመድ ነጥብ አስጥለዋል

Date:

ሀገር የምትገነባው መንግስት ያድርግ በሚሉ ጥያቄዎች ሳይሆን እኔ ይሄን ሰርቻለሁ፣ መንግስት እንዲያግዘኝ እፈልጋለሁ በሚሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መሆን አለበት!! ካልሆነ ልክ እንደ ጠንቋዩ የሰዉ ሰዉ፣ የመንግስት የመንግስት፣ ልክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳለዉ ተስፈኛዉ ትዉልድ ሳይጠበቅ ከተፍ ብሎ ከወሬ እና ከሽኩቻ ያለፈ ተግባር የሌላቸዉን የአሁን ምሁራንን ከጨዋታ ዉጭ እንዳያወጣቸዉ የሚል የአዘኔታም ስሜት አለኝ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምሁራን ነን ባዮችን “ በዝረራ ነጥብ አስጥለዋል፣ያዉም በገዛ ሜዳቸዉ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)

ስማቸው እንዳይገለፅ ያልፈለጉ ፕሮፌሰር እንደጻፉት / ነጻ አስተያየት

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ገደማ ካልተሳሳትኩ Friday, January 2,2026 በቀድሞዉ የቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ለእኔ ደግሞ ከ College of Business and Economics በዛ ግርግር ሰሞን እና በከፊሉ የሀገራችን ክፍል በርካቶችን በነጠቀን የረሃብ ዘመን ወራት በ 1977 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቅኩበት፣ ለሁላችንም ብርቅ  የነበረዉ ትዉስታዉ ትዝታዉም እንደ ትላንት በምናብ የሚታወሰኝ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት በአል ላይ የተዘጋጀው መድረክ ስከታተል ነበር። የወጣትነት አፍላ ጉልበታችንን ሀገራዊ አብዮት እንቅስቃሴ፣ የከተማ ዉስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስም ጋር ድቅን ይልብኛል። አንድም በናፍቆት አንድም በቁጭት፤ በወቅቱ ሀገራችን ከሶሻሊስት ሀገራት ጋር በነበራት ጥብቅ ወዳጅነት የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል ወደ ሩሲያ ( የቀድሞ ሶቪዬት ህብረት ) እድል አግኝተን ከሄድን 32 ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነበርኩ። ከሄድንበት ሳንመለስ የወያኔ እና የሻዕቢያ ጦር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ መሃል ሀገር እየገሰገሰ የነበረበት ወቅት ስለነበር፤ ወደ ሀገር ለመመለስ አመቺ ሆኖ አልተሰማኝም ነበር። የተወሰኑ ጓደኞቼን አስተባብሬ ወደ አሜሪካ የምንሻገርበትን መንገድ ከትምህርታችን ጎን ለጎን ማፈላልግ ያዝን፤ በስተመጨረሻ ተሳክቶ በዛም በዚህም ብለን ከብዙ እንግልት በኃላ አሜሪካ ከገባሁ አሁን ወደ 35 አመት ገደማ ተቃርቤያለሁ። ላለፉት 24 አመታት Old Line State” and “Free State” በምትባለዉ Maryland (MD) እየኖረኩ እገኛለሁ። 


. . . . በትዝታ ነጎድኩ ወደ ዋና ቁም ነገሬ ልመለስ በአዲስ አበባ 75ኛ አመት ምስረታ በዓል ላይ  የሰማሁት የምሁራን ድምፅ፣ ጥያቄዎች እና የመንግስት(የጠቅላይ ሚኒስትሩን) ምላሾች ከሩቅ ላለን ታዛቢዎች ትዝብታችንን እንድንሰነዝር ያስገደደን ይመስለኛል።  በውጭ ሀገር የምንኖር ምሁራንም ሆነ ኢትዮጵያውያን ሀገራችን በለውጥ እና በነዉጥ፣ በእድል እና በፈተና፣ በተስፋ እና ትከዛ መጋጠሚያ ቦታ ላይ እንደቆመች ይሰማናል ብዬ አስባለሁ። በግሌ እንደዛ አይነት ግምገማ ነዉ ያለኝ። ሆኖም ይሄው የለውጥ ጉዞ በአንድ በኩል በመንግስት መዋቅራዊ መዘግየት፣ በሌላ በኩል ከትችት ባለፈ ሰራተኛ፣ ፈጣሪ፣ ለዋጭ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ አለመሆናችን ክፉኛ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው። እኔም እንደማንኛውም ሰው  የሀገሬን ነገር በናፍቆትና በስጋት እቃኛለሁ።እውነቱን ለመናገር፣ እኔ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ/ዶክተር/ መንግስት ትልቅ “ተቃዋሚ” ነበርኩ የተቃዉሞ መንፈሱ አሁንም የለዘበ ቢሆን እንጂ ጠፍቷል ብዬ አላምንም አልፎ አልፎ ብለጭ ይልብኛል። ብልጭ የምትለዉ ቃል ዐብይ አህመድ  እንደ ህፃን ብልጭልጭ ይወዳል “በብልጭልጭ ሀገሩቷን ሞላት ፤ ገንዘቡን አበባ በመትከል ጨረሰው  የሚለውን  የሁልጊዜም ሙግቴን ያስታውሰኛል። ጓደኞቼ ለምን ሚዲያ ላይ ወጥተክ አትሞግትም ቢሉኝም፣ ያለኝን ትችት እና ወቀሳ እነሱ ላይ ከማዝነብ እና አልፎ አልፎ ከምፅፋቸዉ ፅሁፎች ዉጭ  ወደ ሚዲያዉ ለመዉጣት ብዙም አልዳዳኝም፤ ምናልባት ዛሬ ላይ እዉነቶችን ሳጤናቸዉ በአደባባይ እንዳልዋረድ ፈጣሪ ትረፍ ሲለኝ ይሆናል።  

ወደ ዋና ጉዳዬ ልመልስ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ አመት ምስረታ በዓል ላይ የነበረዉን ትዝብቴን ጣል ላድርግ፤ የሀገር ህሊና እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ምሁራን ላይም አንዳንድ ነገሮችን ከትዝብቴ ልበል። ምሁር (ምሁራን ነን ባዮች”) እጅግ የሚያሳፍር የጥገኝነት ስነ-ልቦና (Dependency Mindset)  ውስጥ ወድቀዋል። ትልቁ የሀገሪቱ ህመም ያለውም የሀገሪቱ መብራት መሆን በሚገባቸው ምሁራን ዘንድ እንደሆነ በትዝብቴ ተመልክቻለሁ። Characteristics of a Dependency Mindset፡  Lack of Initiative , External Locus of Control , Low Self-Efficacy, Submissiveness እነዚህን መመዘኛዎች በማየት ሀሳቤን ትረዱታላችሁ ትዝብቴን፣ ትጋራላችሁ ብዬ አምናለሁ!

Lack of Initiative፡ በግብርናው፣ በዲፕሎማሲዉ፣ በትምህርት፣ በማህበረሰብ፣ በጤና በተለያዩ ዘርፎች የኔ ሚና ምንድነው? ሀገሬን ሊለውጥ የሚችል ከወረቀት ያለፈ ስራ እንዴት ላበርክት ? በድህነት እና በኋላ ቀርነት ለሚማቅቀዉ ወገኔ እንዴት ልድረስ? ችግር ሊፈታ የሚችል ስራ እንዴት ልስራ? የሚሉትን ነጥቦች አደባባይ አውጥቶ ከመጠያየቅ እና ሀገር ከምሁራን ብዙ በምጠብቅበት በዚህ ወቅት፣ የሀገር አዕምሮ ተብለው የሚጠሩ ምሁራን ዋናውን ችግር ትተው አንድም ውሀ የማያነሳ ነጥብ ላይ ማተኮራቸው በጣም ይገርመኛል። የምሁር ሚናው የሀገር ችግር መፍታት እና የመፍትሄ ሃሳብ መጠቆም መስሎኝ?

ለበርካታ አመታት በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚቀመጠዉ እና ተወዳዳሪ አልተገኘለትም በመባል የሚታማዉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አፈራቸዉ የሚባሉ ምሁራን ከአንድ የተራ የታክሲ ውስጥ ወሬ እና ሀሜት ያላለፈ ንግግር ሲናገሩ ማየት እጅግ አስደንጋጭ ነዉ።  ፕሮፌሰር አጎሽ አሸናፊየ ምሁራንን ንቁ ተሳትፎ ለመፍጠር መንግስት ምን ለማድረግ አቅዷል? ሲሉ ጠይቀዋል።  አይ የኛ ምሁራን መንግስትማ ስራዉን እየሰራ ነዉ፣ መንገድ ብትሉ በየአይነቱ፣ ህንፃ ቢባል አማርጣችሁ፣ መብራት ብትሉ ከፈረቃ ገላግሏችሁ፣ ምግብ ብትሉ በአለም ደረጃ ተሸልሞበት አሳያችሁኮ! ከመንግስት የምትጠይቁት ሌላ ምንድን ነው? ደምወዝ እየከፈለ በብዙ የአለም ሀገራት እያስተማራችሁ ምን ቀረው?  እስከምረዳው ምሁርነት ለጨለማ ብርሃን መሆን እንጂ፣ ብርሃን እስኪመጣ በጨለማ ውስጥ ተደብቆ መቆየት አይደለም።

ሌላዉ ድንቃድንቅ ወሬ ደግሞ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት? የሚል ግርምት የሚያጭር ጥያቄም ከዚሁ መድረክ ሲሰነዘር ሰማሁ….በPhD ደረጃ ታላላቅ አርቲክሎችን የጻፈ ምሁር ነኝ ከሚል፣ ይሄ ጥያቄ መነሳቱ ራሱ የውድቀት ምልክት ነው። ጭራሽ ምሁር ነን ብለዉ ተሰብስበዉ የምሁር ሚና ምን መሆን አለበት የሚለዉን ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይጠይቃሉ #ቅሌት ነዉ። በተገላቢጦሽ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚና ምን መሆን አለበት ብሎ እነሱን እንደመጠየቅ ነዉ።  ከአንድ ምሁር መነሳት የነበረበት የራሱን ሚና የሚገልጽ ሀሳብ መወርወር እንጂ ከሌላ ወገን ሚናዬ ምንድነው?  ብሎ ትዕዛዝ መቀበል መሆን አልነበረበትም። Submissiveness ያልኩትም ይሄን ነዉ። የሆነ ጊዜ ወረቱ ሳያልቅ በፊት አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ እንዲ ሲል ሲጠይቅ በብሄራዊ ቲያቲር ጢም ያለዉ ተመልካች በጭብጨባ እና በሳቅ ቤቱን ሲያደምቁት አልረሳዉም “ምነዉ የዘንድሮ ምሁራን ዕዉራን ሆኑ፣ ምነዉ የዘንድሮ ዶክተሮች ዶሮዎች ሆኑ” ሲል ነበር።

አቶ የቆያለም እንዳነሱት፣ መንግስት ስለዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ምን ያስባል? ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ እኛ እንደ ምሁር የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች በሀገር ዉስጥ ለመጠቀም እና የራሳችንን ፈጠራ ለማከል ማድረግ የሚጠበቅብን ጉዳዮች ብለዉ መዘርዘር ሲገባቸው፣ መንግስት ምን ያስባል ብለዉ እርፍ ። አለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የእኛ ምሁራን የዜሮ ድምር ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቀው የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ መጠቆም ተስኗቸዋል። ጥያቄው ግን መንግስት ላይ ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲው ላይም መሆን ነበረበት….ዩኒቨርሲቲዎች እስከዛሬ በዚህ ዘርፍ ምን ሰሩ? የትኛው የፈጠራ ስራ ነው ከመንግስት ቢሮክራሲ ወጥቶ ለህዝብ ጥቅም የዋለው? ዩኒቨርሲቲ ለሀገር የቤት ስራ የሚሰጥ፣ አቅጣጫ የሚያሳይ ተቋም እንደመሆኑ ብዙ ይጠበቃል፤  ዛሬ ላይ የምናየው ምሁር ትንታኔ ላይ የሚፈጥን፣ ተግባር ላይ የሚዘገይ፤ መፍትሄ የማይሰጥ፤ ከመንግስት እጅ የሚጠብቅ ሆኗል። ምሁራን መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች መንግስትን ማስገደድ የሚችል የሃሳብ የበላይነት ማምጣት የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጓዳ የደበቀው ጉድ እየወጣ፣ እየነጣ እና እየታየ ነዉ።  

ሀገር የምትገነባው በንድፈ ሀሳብ ክርክር ብቻ አይደለም። ሀገር የምትገነባው የፖለቲካውን ጫና ተቋቁሞ፣ ከጥቅም በላይ ሀገርን አስቀድሞ፣ በየዘርፉ ጠብ የሚል ስራ መስራት ሲቻል ነው። ምሁራኖቻችን ከመንግስት ምቹ ሁኔታን መጠበቅ አቁመው፣ ራሳቸው ለሀገሪቱ ምቹ ሁኔታ መሆን አለባቸው። ካልሆነ ግን፣ እንደለመድነው የምሁራን ውይይት እንደ ወግ አጥባቂዎች የሻይ ቡና ጨዋታ ሆኖ ይቀራል። አንድ ሀገር በአንድ መሪ ጠንካራ ስራ ብቻ አትገነባም፤ ይልቁንም የእያንዳንዱ ዜጋ፣ በተለይም የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች የዕለት ተዕለት ውጤት ድምር ናት። እናም የምሁራኖቻችን ጥያቄ ጠቅላዩ ስንዴ ላይ ውጤት አምጥተዋል ብሎ መመስከር ብቻ ሳይሆን፣ “እንደ እንስሳት ህክምና ባለሙያ በስጋና ወተት ምርት ላይ ጠቅላዩ ስንዴ ላይ ያመጡትን አይነት ለውጥ ለማምጣት እኔ ምን ሰራሁ? የሚለው ጥያቄ ቀዳሚ መሆን አለበት። ሀገር የምትገነባው መንግስት ያድርግ በሚሉ ጥያቄዎች ሳይሆን እኔ ይሄን ሰርቻለሁ፣ መንግስት እንዲያግዘኝ እፈልጋለሁ በሚሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መሆን አለበት!! ካልሆነ ልክ እንደ ጠንቋዩ የሰዉ ሰዉ፣ የመንግስት የመንግስት፣ ልክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳለዉ ተስፈኛዉ ትዉልድ ሳይጠበቅ ከተፍ ብሎ ከወሬ እና ከሽኩቻ ያለፈ ተግባር የሌላቸዉን የአሁን ምሁራንን ከጨዋታ ዉጭ እንዳያወጣቸዉ የሚል የአዘኔታም ስሜት አለኝ።

ኢትዮጵያ ከምሁራኖቿ ብዙ ትጠብቃለችና በምትፈልገን ልክ እንገኝላት!!

የግል ምልከታዬ ነው….. ክብረት ይስጥልኝ Jan , 07 , 2026

ዝግጅት ክፍሉ፣ ይህ አስተያየት የጸሀፊውና ይጸሐፊው ብቻ ነው። የሚወክለውም እሳቸውን ብቻ ነው። ምላሽ ወይም አስተያየት ካለ ዝግጅት ክፍሉ ያስተናግዳል።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

“አሳጋቾቹን ካህናት ስም ዝርዝር ይፋ እናደርጋለን”

አዲስ ሪፖርተር - የወረታ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ...

ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ነፃ የሃሳብ ሪፐብሊክ፣ የሁምቦልድት ፍልስፍና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሪፎርም እይታ

ቢልዱንግ እና የሃሳብ ትውልድ እሳቤዎች ሲቀናጁ ምሁራን የቆዩ የትርክት...

የኤርትራ አፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች ግንባር ፈጠሩ፤ “ስምምነቱ ለሻዕቢያ አስደንጋጭ መርዶ ነው” አቶ አብዲ ሼኽ መሐመድ

አዲስ ሪፓርተር - በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች...