የእናት አገር ጥሪ ከተደረገ በኋላ መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለጥሪው የሰጠው ምላሽ በጣም አስገራሚ ነበር። አገራችን በሶማሊያ መወረሯን እንደሰማ ተበሳጨ፣ቁጭትም አደረበት። በዚህ የተነሳ ሕዝባዊ ሠራዊት ለማሰልጠን ዝግጅት መጀመሩን እንዳወቀ በሚጠየቀው መንገድ ሁሉ ለመርዳት ፈቃደኛ ሆኖ ተነሳ።
በቅድሚያ የዕድሮችን ድንኳኖች በሙሉ አስረከበ። ከግለሰቦችና ከድርጅቶች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሰብስቦ በስጦታ መልክ አበረከተ። በዚህ ብቻ ሳይወሰን በርከት ያሉ ሰዎችን ተራ አስገብቶ በየቀኑ ወደ ታጠቅ ጦር ሠፈር በመላክ ድንኳኖችን አስተከለ። የጉልበት ሠራተኛ የሚጠይቁ ሥራዎችን ማለትም ጉድጓድ መቆፈር፣ እንጨት መፍለጥ፣ ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ዕቃዎችን ማመላለስ፣ ከመኪና ማውረድ ወይም መጫን የመሳሰሉትን ሥራዎች ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎችን በፈቃደኝነት እያሰባሰበ ቦታው ድረስ በማጓጓዝ አድርሷል።እነዚህ ሥራዎች እንዲከናወኑ ያስተባበሩትና አመራር የሰጡት የቀበሌ ማህበራት ነበሩ።
ከሁሉ ይበልጥ የአዲስ አበባ ሴቶች የተጫወቱት ሚና በእጅጉ የሚያስገርም ነበር።ከከፍለ ሃገራት እየተመለመሉ ታጠቅ ጦር ሠፈር የመጡትን ምልምሎች እንደእናት
እየተቀበሉ አስተናግደዋል፣ መግበዋል፣ ተንከባክበዋል። ቋሚ ሠራተኛ በሌለበት ወቅት የአዲስ አበባ ሴቶች በየቀኑ ታጠቅ ጦር ሠፈር በመገኘት የሥራ ክፍፍል እያደረጉ
እህል ይለቅማሉ፣ ያስፈጫሉ፣ ሊጥ ያቦካሉ፣ ይጋግራሉ፣ ወጥ ይሠራሉ። ይህን ሥራ የሚያከናውኑት ተራ ገብተው ነው። በተራቸው ቀን በአንድ በተወሰነ ቦታ ይሰባሰባሉ።
ከዚያ በአውቶቡስ ተሳፍረው ወደ ታጠቅ ጦር ሠፈር ይሄዳሉ። ሙሉ ቀን ምግብ ሲያዘጋጁና ሠራዊቱን ሲመግቡ ውለው ማታ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። በማግስቱ ደግሞ ባለተራዎቹ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ይውላሉ። ይህን ተግባር የሚያከናውኑት እንደብሔራዊ ግዴታ ስለሆነ አንዳቸውም ቅር የመሰኘት ወይም የመከፋት ምልክት አያሳዩም። እንዲያውም በሥራ ላይ እያሉ ይፎክሩና ጉሮ ወሸባዬ በማለት ይዘምሩ ነበር።
ይህን የመሰለው የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ድርጊት ያበሳጨውና ዕኩይ ዓላማውን ለማስፈጸም እንደእንቅፋት አርጎ የተመለከተው #ኢሕአፓ በአገር ፍቅር ስሜት የተቃጠሉት ሴቶች ለእናት አገር ጥሪው ድጋፍ እንዳይሰጡ ለማድረግ የግድያ ሙከራና የማስፈራሪያ ዘመቻ ከፍቶባቸው ነበር። ይሁን እንጅ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ሴቶች መካከል በኢሕአፓ ድርጊት ደማቸው የተቆጣው
“ማን ይፈራል ሞት ማን ይፈራል! ለእናት ሃገር ሲባል” የሚለውን ሕዝባዊ ዜማ ፈጥረው ወደ ታጠቅ በሚያደርጉት ጉዞና በታጠቅ በሥራ ላይ በተሠማሩባቸው ጊዜያት ሁሉ በኅብረት ያዜሙት ነበር።
በአገራችን ላይ የተሰነዘረው ወረራ ሙሉ በሙሉ አስኪገታና ደህንነታችን እስኪረጋገጥ ድረስ ሠራዊት የማሰልጠን እንቅስቃሴ መቀጠል እንዳለበት በመታመኑ ምግብ የሚያበስሉና የሚመግቡ ቋሚ ሠራተኞች ሥራውን እስኪረከቡ ድረስ የአዲስ አበባ ሴቶች አገልግሎት ቀጥሎ ቆይቷል። የአዲስ አበባ ሕዝብ በሁሉም የሥራ መስክ በታጠቅ ጦር ሠፈር እየተገኘ ተሳትፎ አድርጓል።የተለየ ሙያ ያላቸው ጥሪውን ተቀብለው ነጻ አገልግሎት ሰጥተዋል። እዚህ ላይ በወቅቱ በአዲስ አበባ የፀጉር አስተካካይ የነበሩ ወገኖቻችን ያበረከቱትን ተግባር መጥቀስ ይቻላል።
ከሁሉም አገሪቱ ክፍሎች የመጡት ምልምሎች እንደ አካባቢያቸው ባህልና የአኗኗር ዘይቤ የተሠራው ፀጉራቸው ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጭ ሆኖ በመገኘቱ የአዲስ አበባ ፀጉር አስተካካዮች ታጠቅ ጦር ሠፈር ድረስ መጥተው የሕዝባዊ ሠራዊቱን ፀጉር እንዲያስተካክሉ በሠራተኛ ማህበር በኩል ጥሪ ተደረገላቸው። ለጥሪው
መልስ ለመስጠት አላመነቱም። ወዲያው አባሎቻቸውን ተራ አስገብተው በዘመቻ መልክ ለማስተካከል ወሰኑ። ጊዜ አላባከኑም ማስተካከያ መሣሪያቸውን ይዘው ታጠቅ ጦር ሠፈር በመገኘት ጊዜያዊ የፀጉር ማስተካከያ ቦታ አዘጋጅተው ማስተካከል ጀመሩ። የማስተካከሉ ሥራ ስልጠናው አስኪጠናቀቅ ድረስ ቀጥሏል። ፀጉር አስተካካዮች በሙያቸው ላገራቸው ያበረከቱት አኩሪ ተግባር የመንፈስ ደስታ ሰጥቷቸዋል።
በታጠቅ ጦር ሠፈር አዲስ በተተከለው ዘመናዊ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ለሠራዊቱ የሚበቃ ዳቦ ማምረት እስኪቻል ድረስ ሠራዊቱን ለመመገብ ከግል ዳቦ መጋገሪያ ቤቶች
በየቀኑ ዳቦ እየገዛን መውሰድ ነበረብን። በዚህ የተነሳ ዳቦ ጋጋሪዎች የአዲስ አበባ ሕዝብንና የታጠቅ ጦር ሠፈርን የዳቦ ፍላጎት ማሟላት ስላቃታቸው መንግሥት የሚፈልጉትን ያህል
የዳቦ ዱቄት በመስጠት ሌት ከቀን ዳቦ እንዲጋግሩ ተደረገ። በዚህ አኳኋን ጋጋሪዎቹ ብርቱ ጥረት አድርገው በወቅቱ የገጠመንን ችግር አስወገዱ።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የአውቶቡሶችና የተሽከርካሪ ባለቤቶች የእናት አገር ጥሪውን ተቀብለው ሕዝባዊ ሠራዊቱን በማጓጓዝ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽዖም በጣም አስመስጋኝ
ነበር። የእነሱ ትብብርና ፈቃደኝነት ባይታከልበት ኖሮ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝባዊ ሠራዊትን ከጠረፍም ሳይቀር አጓጉዘን አዲስ አበባ ማድረስ አይቻለንም ነበር። “አገር
ከሌለ እኛም ሀብት ሊኖረን አይችልም። ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የምንሰጠው ለአገራችን ጉዳይ ነው” ብለው ይሰበርብናል ወይም ይበላሽብናል የሚል ስጋት ሳያድርባቸው ያላቸውን ተሽከርካሪ በሙሉ ሠራዊቱን እንዲያጓጉዝ በፈቃደኝነት አሰማሩ። ከባለቤቶቹ ባልተናነሰ ሁኔታ ሹፌሮችም ሙሉ ፈቃደኛና ተባባሪ በመሆናቸው አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ወጥተውና ወርደው በመጓዝ ያለምንም እንከን ምልምሎችን ታጠቅ ጦር ሠፈር አድርሰዋል።
እኛና አብዮቱ ፤ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ፤ 376 እስከ 377
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






