ታላቁ ሴራ

Date:

በኔዘርላንድሱ ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሣይንስ ጥናት ኢንስቲትዩት  አንደኛው አዳራሽ ውስጥ ሊሂቃን ዲስኩር ለመታደም ተኮልኩለዋል፡፡

ለጨለማ ሩብ ጉዳይ የሚመስል እይታ ባለው አዳራሽ ውስጥ የጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረቢያው ፕሮጀክተር ለእነሱ እንደ ብርሀን  ፍንጣቂ የሚታዩ ፊደላትን ፤ ለሌላው  እነሱ ዘለዓለም በጫማ መርገጫቸው ስር እንዲውል ለሚፈልጉት ያልተገራ የሴራ መሻትን ይዟል ።

በቀጭን ሰውነት ላይ ገብስማ ጠጉር  የወረሳቸው  የምጣኔ ኃብት ሳይንስ ሊሂቅ ፕሮፌሰር ሀዋርድ ኒኮላስ ደግሞ አትሮኖሱ ላይ ተሰይመዋል።

የጥናት ጽሑፋቸው “የአፍሪካ እድገት ለምን ወደኋላ” -Underdevelopment in Africa የሚል ነበር።

ፌዝ ቢጤ እንደመግቢያ ጣል  አድርገው ለታዳሚያቸው ፈገግታ ያጫሩት ፕሮፌሰሩ  ለጥቀው ያወሩት ነገር የልብ ትርታን ቀጥ የሚያደርግ ሆኖ አረፈ።

“የሰለጠነው ዓለም እንዳለፈለት እንዲቀጥል ከተፈለገ አፍሪካ ድሀ ሆና መቅረት ይኖርባታል::”  አሉ -“we must keep Africa poor.”

ሀዋርድ ሲቀጥሉ “አፍሪካ የሰለጠነው ዓለም የእድገት መሰረት:: የጥሬ እቃም ሆነ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት  ከአፍሪካ ነው::” አሉ።

እናም  “ምዕራቡ ዓለም በተደላደለ ኑሮው እንዲዘልቅ ከፈለገ አፍሪካ ከዚህ የጥሬ እቃ አቅራቢነት የዘለለ ሚና ሊኖራት አይገባም::” አሉ።

ቀጠሉና…. “የትኛውም የኢኮኖሚ መዋቅር፣ ማናቸውም አይነት ሉላዊ ተቋማት እና የትምህርት ስርዓቱ ጭምር የተነደፈው ሆን ብለን  አፍሪካ ባለችበት እንድታዘግም ለማድረግ ነው!”  አሉ ፕሬፌሰሩ ያለሀፍረት።

እናማ ለግማሽ ሰዓት ሽርፍሪፊ ሰከንድ የጎደለው የፕሮፌሰሩ ዲስኩር ጥቅል ጭብጡ መግቢያው ላይ ተደመደመ።

ይህ እስቤ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ከተሰኘው የበርሊን ኮንፍረንስ አሊያም ጉባኤ የቀጠለ ግን ደግሞ የከፋው የደባ መሻት ሴራ ነው።

ሴራው እምቢ ቅኝ ግዛት ያሉትን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፓትሪስ ሉሙምባን  በልቷል፣  የቡርኪናፋሶውን ተራማጅ ቶማስ ሳንካራን ቀጥፏል፤ የቶጎው ስልጡን ሲልቫነስ ኦሊምዮን ቀብሯል፤  ለአንድ የአፍሪካ መገበያያ ገንዘብ የታገለው የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊን  አስከፊ በሆነ መንገድ ጥሎ ሀገሪቷንም በብዙ ዋጋ አስከፍሏል።

አፍሪካን ደሀ አንደሆነች ማስቀረት የተሰኘው ስልት ከጸረ ቅኝ ግዛት ትግል እና ከነጻነት በኋላ መልኩንም ሆነ  መተግበሪያ ስልቱን እየቀያየረ ቀጥሏል።

ኬንያዊው የሕግ ባለሙያ እና አንቂው ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ ይሄ ሴራ መሬት የነካበትን መንገድ እና አፍሪካ የከፈለችውን ዋጋ እያሰቡ ባገኙት መድረክ ሁሉ በብስጭት ይናገራሉ፡፡ በተለይ የአፍሪካ የትምህርት ሥርዓን ያለፈበትን ሲያስቡ ከመቆጨት አልፈው ያማቸዋል፡፡

ሉሙምባ ‘አፍሪካ ሆን ተብሎ የሰው ሀብት ልማት ላይ እንዳትሰራ ተደርጓል’ ባይ ናቸው።

ይህም ማንነቱን ያወቀ፣ የተማረና የመረመረ ብሎም ችግር ፈቺ ትውልድ ለመፍጠር የሚደርግ የትኛውንም ጥረት  ለማደናቀፍ አስችሏል ።

ይህን ሴራ ተሻግሮ ኮሌጅ የበጠሰ ባለምጡቅ አዕምሮ ተማሪ ሲከሰትም በውጭ የትምህርት እድል ሰበብ ከአህጉሩ ይነቅሉታል። የአእምሮ ፍለስት ወይም Brain drain የሚል የዳቦ ስምም ይሰጡታል።

እንደ አፍሪካ ሊደርሽፕ ገፀድር መረጃ በየአመቱ 70 ሺህ የተማሩ እና ስልጡን ክህሎት ያላቸው የአፍሪካ ልጆች በምዕራቡ አለም ይነጠቃሉ።

አፍሪካ ዋጋ ከፍላ ያበቃችው ሙያተኛ እውቀቱን፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና ጉልበቱን ያደገውን አገር ይበልጥ ሲያለማበት ያልፋል።

በሌላ በኩል ቱኒዚያዊው ጉምቱ የምጣኑ ኃብት ፕሮፌሰር ፋዴል ካቡብ ደግም ‘ስነ ልቦናችንን ቀድመው ሰልበውታል’ ባይ ናቸው።

‘የሀብት ማማ ሆነን ሳላ ደግመው ደጋግመው ደሀ ናችሁ አሉን እናም ይሄን እሳቤ ለመፋቅ ዋጋ ከፈልን’ ይላሉ።

እስከ 78 ከመቶ የምድሪቷ የኮባልት ማዕድን በአንድ ሀገር በዲ አር ሲ ኮንጎ ብቻ ይገኛል፤  ሆናም ሀገሩ አንዴ በወረረሽኝ ሌላ ጊዜ በጦርነት ይታመሳል።

የጀት ሞተር፣ተንቀሳቃሽ ስልኮቻ፣ ኮምፒዩተሮች ፣የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ ባትሪዎች እና ሌሎች ግዙፍ ግኝቶች ያለ ኮባልት ቅሪላ እንደሆኑ ልብ ይሉታል፡፡

90 ከመቶ የምድራችን ፕላቲኒየም የአፍሪካ ማህጸን ውስጥ ነው፤ ሆኖም ለማወቅ ብሎም ለማልማት ዘመን ወስዶብናል፡፡ የግብርና እና የቱሪዝም ሀብታችንማ መች ተዝቆ ያልቃል ይላሉ ምሁሩ፡፡

የቱኒዚያው ምሁር ሲቀጥሉ አፍሪካ ላይ እጅግ የተዛባ ገጽታ መፍጠር ደግሞ የታላቁ ሴራ ታላቁ ግብ እንደነበር ያሰምሩበታል።

ግዙፍ ነን ብለው በማሰብ የማያክሉትን የውሸት የካርታ ሥዕል በመስራት ለራሳቸው ይሰጣሉ፤የአፍሪካን ደግሞ ትንሽዬ በማስመሰል ያኮሰምናሉ፡፡ ዓለምንም በዚሁ አስተሳሰብ ለማሰር በገጸድሮች፣ በሕትመት፣ በሚዲያ እና በሥርዓተ ትምህርት ጭምር ውስጥ በሴራ ያካትታሉ፡፡

ይህ እጅግ የተጠና እና በተደራጀ መንገድ የተተገበረ የአፍሪካን ገጽታ የማንሸዋረር እቅድ ነው፡፡

ሆሊውድ አፍሪካን መቼት ያደረገ ቀረፃ ካለው ለታሪኩ አስፈላጊ ባይሆንም እንኳን በመለወጥ ላይ ያለውን ሳይሆን ጢሻውን ይመርጣል፡፡ ይህ በምዕራቡ የፊልም እና የመገናኛ ብዙኃን  አሰራር ያልተጻፈ ሕግ ነው፡፡

ፍጹም የሚላስ የሚቀመስ የሌለባት፣ ጽዳት ህልም የሆነባት፣ ባህል ፣ወግ ፣ልማድ  ብሎ ነገር  ከቅንጦት የሚቆጠርበት  በጠብ መንጃ የምትወያይ፣ ፍትሕ አልባ  አህጉር  አድርጎ ማሳየት  የሴራው  ቁንጮ ነጥብ ነበር።

በዚህ በእኛ ዘመን ግን አጥንት የሰረሰረ እና የዘለቀ ስር የወጋ  ሴራን የሚገላልጥ ሰው ተገኝቷል፤ ለዛውም ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ወጣት።

አሜሪካዊው ዳረን ዋትኪንስ “Speed dose Africa” በሚል መጠሪያ በ20 የአፍሪካ ሀገራት የጀመረው የቀጥታ ስርጭት ጉብኝት የምዕራቡን ዓለም ስልታዊ አህጉሩን የማጠልሸት ሴራ ያከሽፍ ጀምሯል።

የዳረን የኢትዮጵያ ጉብኝት ብቻውን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆኗልና  እስኪ ትንሽ እንቃኘው።

ፋታ የማይሰጠው   የወጣቱ ጉዞ የዓድዋ መታሰቢያ ሲደርስ ታሪክን እንደ አዲስ ለመዘከር በቅቷል። በባዶ እግራቸው ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው የነጭ የቆዳ ቀለም የበላይነትን በሰውነት እኩልነት የተኩትን የዓድዋ አርበኞች ገድል እንደ ቅድመ አያቶቹ ሁሉ በባዶ እግሩ ጎብኝቷልና።

ኢትዮጵያ  ቅኝ ያልተገዛች ብቻ ሳይሆን የባርነትን ቀንበር የሰበረች፣ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል፣ የትግል ስንቅ እና የድል አርማ መሆኗን  ወጣቱ  አይቷል፤ አሳይቷል።

የሰው ዘር መነሻው  ይህችው  ድንቅ ምድር፣ በምዕራቡ ሳይሆን በራሷ የጊዜ ቀመር ቀን የምታሰላ፣ ጊዜ የምትፈትል ዘመን የምትቀምር፣ የተፈጥሮ፣ የባህል እና የታሪክ ሀብታም፣ ውበትን በብዝኃነት የታደለች፣ ምድረ ቀደምት፣ ብሎም አስራ ሶስት ወራትን የምታዋልድ ብቸኟዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ዓለም ከስፒድ  እኩል በዓይኑ አይቷል።

እድሜ ለስፒድ፤ ድፍን ዓለም ቀኑን የሚጀምርበት ቡና ምንጩ  ከጥቁር አንበሶች ምድር  መሆኑን  ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማም ተገኘቷል፡፡

ታሪክ ቢባል  በደርዝ ፣  ምግብ ቢሉ በዓይነት፣ ጽዳት ካሉም ከአጸድ ያለፈ መንገድ የዘለቀ፣ ለአደባባይ የበቃ፣ ለስፖርት የተረፈ የከተማ ውበት ተቃኝቷል ፤ ቴክኖሎጂ ከተጠራ ነገን የተለመ … ብቻ  በመድረክ ስሙ በአይ ሾው ሲፒድ ዓይን ዓለም ለአራት ሰአት ከሀምሳ ሁለት ደቂቃ ከሰላሳ ሦስት ሰከንድ  የኢትዮጵያን እውነት ፣ መልክና አሁናዊ አውድ ለመኮምኮም ቻለ ።

እውነታው እዚህ ላይ ነው፤ ተቆርጦ በተቀጠለ፣ እንደወደዱት ባጠናቀሩት ዜና  እና ዘጋቢ ፊልም መልክ አልባ የነበረችው አፍሪካ  በወጣቱ ስፒድ በ48 ሚሊዮን የዩቲየብ ተከታዮች ዘንድ በቀጥታ ስርጭት ሴራው ሲበራይ ተስተዋለ፡፡

ስፒድ ባህል ሳይበረዝ፣ ታሪክ ሳይበወዝ ፣ ገጽታ ሳይንሸዋረር ያያል ያሳያል፣ ይዳሳይ ያስዳሳል፣  ይስቃል… ያነባል… ይገረማል ፡፡

መችም በትዕይንቱ ሴራቸው ታጭዶ ዶጋ አመድ የሆነባቸው እውነታው በወጣቱ በመገላለጡ ሀፍረታቸውን መሸፈኛ ሳያጡ አልቀሩም፡፡

በሌላ በኩል የእሱን የቀጥታ ስርጭት የታደሙ እና የተቀረጸውንም ቆይተው ያዩ የአፍሪካ መሰረት ያላቸው የድንቅነሽ ልጆች በሙሉ ዓይናቸው እንባ እያቀረረ….ባዩት ነገር እተገረሙ….የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው ኢትዮጵያ….አፍሪካ…..እያሉ በባለፈው ታሪክ እየተቆጩ፣ የወደፊት የልጆቿ ተስፋ ደግሞ እየታያቸው በስሜት እንደ ስፒድ ሆነዋል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት እና በተለይም ከአዲስ አበባ በተንቀሳቃሽ ምስል የተጋሩት እና ያዩት እውነታ ሁሉ ሕልም እየመሰላቸው ምናለ ባልነቃሁ ብለዋል፤ ልባቸው ጮቤ ረግጦ በሀሴት ፈንድቀዋል፡፡

እናም አፍሪካን በድህረ ቅኝ ግዛት እሳቤ “We must keep Africa poor” ሲሉ ርዕይ የተለሙ ፣ ስልት የነደፉ፣ ተቋም የፈጠሩ፣ ሚዲያ ያደረጁ፣ ፖሊሲ የተቀበሉ ምዕራባውያን በ21 አመቱ አይ ስፒድ ሾው የቀጥታ ትዕይንት  ድባቅ ተመትተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በደቡብ አፈሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጎላና ሌሎችም የአፍሪካ ድንቅ  ሀገራት ስፒድ ይህን አሳክቷል፡፡

ከ10 ሚሊዮን በላይ ተመልካች ካገኝው የአይ  ሾው ስፒድ  የኢትዮጵያ የቀጥታ ስርጭት በኋላም ዓለም በብዙ ስለ ኢትዮጵያ  ብሎም ስለ አፍሪካ  አውርቷል፤ ጽፏል ፣ በእንባ ጭምር  ባየው ነገር መነካት መገረሙን በተንቀሳቃሽ ቪዲዮ ሰርቷል፤  አጋርቷል ወዘተ … ግን አንድ መሰረታዊ ጥያቄ አንስቷል፤  ዓለም  ለምን ይሄን  እውነት ደበቀን ? የሚለውን።

ደራሲ በረከት በላይነህ በአንድ  የመነባንብ  ትዕይንት ላይ” እረፉ” በሚል ሀሳብ ጉዳዩን በግጥም ያዋዛው ይመስላል፡፡

      እረፉ…..

ማን እንደጠለፈኝ ማን እንደሠበረኝ፤

ጠያቂ አጣሁ እንጂ መልስማ ነበረኝ:: 

አሁን ዝነኛው አፍሪካ አሜሪካዊው አይ ሾው ስፒድ ይህን ቅኔ ይፈታው የያዘ ይመስላል።

በአስማረ ቸኮል

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ጃዋር የአመጽ ጥሪውን የሰረዘው ለአስቸኳይ ስራ ግብጽ ተልኮ በመሆኑ ታወቀ፤ የግብጽ ኤጀንት እንደሆነ መረጃዎች እየወጡበት ነው

አዲስ ሪፖርተር - ባለፈው ማክሰኞ በኢትዮጵያ ሕዝብ አመጽ እንዲያቀጣጥል...

የሶማሌ ዲሞክራቲክ ካውንስል “ኢትዮጵያ እየተጠቃች ነው” በሚል የጀርመን ድምጽን እንደሚከስ አስታወቀ

አዲስ ሪፖርተር - የጀርመን ድምጽ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን ሰዎችና...

“ፍቅር እስከ መቃብር”  የአብዮታዊው መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ ስንብት 

በማር ወለላ በተመሰለ ፍቅር ተጀምሮ በመቃብር የተቋጨው የኢራን እስራኤል...

የትርክት ጦርነት፤ ብሔራዊ ጥቅም ከሃይማኖታዊና ርዕዮተ – ዓለማዊ ወገንተኝነት በላይ የሆነ የሀገር ህልውና መሰረት!

ግብፅ በውስጥ ፖለቲካዋ የሙስሊም ወንድማማቾችን (Muslim Brotherhood) በሽብርተኝነት ፈርጃ፣...