አዲስ ሪፓርተር – በአሜሪካ የፖሊሲ ቀረጻ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካላቸው ተቋማት አንዱ የሆነው የአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ ኢንስቲትዩት (AEI)፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኤርትራ ላይ የአገዛዝ ለውጥ እንዲያመጡ የሚጠይቅ ግልጽ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳብ ይፋ አደረገ። ዜናው አሜሪካ በአፍሪቃ ቀንድ ከእስራኤል ጋር ከጀመረችው አዲስ ፖሊሲና ተገባራዊ እርምጃ አንጻር የቀረበው የፖሊሲ ሃሳብ ኢሳያስ ላይ ነገሮች እየከረሩ መሄዳቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል።
ተንታኙ ሚካኤል ሩቢን ባቀረቡት በዚህ ጽሑፍ፣ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው “አዲስ ጦርነት አልጀምርም” የሚል አቋም ቢኖራቸውም፣ አሁን ግን በአሜሪካ ተቃናቃኞች ላይ የሚወስዱት እርምጃ የተቀየረ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ላይ የተወሰደው እርምጃ ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂም እንደ ማስጠንቀቂያ ሊያገለግል እንደሚገባ ተመልክቷል።
ለዚህ ጥሪ እንደ ዋነኛ ምክንያት የቀረበው በኤርትራ እስር ቤት ለ13 ዓመታት የታሰረችው የአሜሪካ ዜግነት ያላት ሲሃም አሊ ጉዳይ ነው። ሲሃም በታሰረችበት ወቅት የ15 ዓመት ታዳጊ እንደነበረች ያስታወሰው ጽሑፉ፣ አባቷ (የቀድሞው የኮምንኬሽን ሚኒስትር ዓሊ አብዱ) አገዛዙን ጥለው ወደ ውጭ በመሄዳቸው ምክንያት ብቻ ያለምንም ክስ መቀጣቷን ይገልጻል። ትራምፕ ታጋቾችን በማስለቀቅ ረገድ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው ለሲሃም ፍትሕ እንዲሰጡና የኤርትራው መሪ ሥልጣናቸውን በሰላም ካልለቀቁ እንደ ኒኮላስ ማዱሮ “ከሀገር የመባረር” ዕጣ ፈንታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ ጸሐፊው ወትውተዋል።
ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችንም የዳሰሰው ይህ መጣጥፍ፣ ኤርትራን “የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ” በማለት ይገልጻታል። የአገዛዙ ያልተገደበ ብሔራዊ ውትድርና፣ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ላይ የሚጣለው የ2 በመቶ ግብር፣ እና አሜሪካውያን ኤርትራውያን ላይ የሚፈጸመው ማስፈራሪያ ለአሜሪካ ጥቅም ስጋት መሆኑ ተጠቅሷል። በተጨማሪም ኤርትራ ከቻይና፣ ከኢራን እና ከሁቲ አማፂያን ጋር ያላት የጠበቀ ትብብር እንዲሁም በትግራይ ጦርነት ወቅት የነበራት ጄኖሳይድን ያካተተ ተሳትፎ በአካባቢው ጸጥታ ላይ የፈጠረው ስጋት የአገዛዝ ለውጥን አስፈላጊ እንደሚያደርገው ሩቢን በዝርዝር አስረድተዋል።
ይህ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳብ በተለይ በቀይ ባሕር አካባቢ አሜሪካ ያላትን ስትራቴጂካዊ የበላይነት ለማስጠበቅ ኤርትራን እንደ “አደገኛ እንቅፋት” የመመልከት አዝማሚያ በዋሽንግተን የፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ እየጎላ መምጣቱን ያሳያል። የትራምፕ አስተዳደር በሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በታጋቾች መታሰር ስም የቀጥታ ጣልቃ ገብነት እርምጃዎችን እንዲወስድ የቀኝ ዘመም ኃይሎች የሚሰጡት ምክር፣ የአገዛዝ ለውጥ ማምጣት በቀጠናው ላይ ያለውን ስር የሰደደ አለመረጋጋት ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ይከራከራሉ።
እንደ ሩቢን ገለጻ፣ የኢሳይያስ አፈወርቂን አገዛዝ ማስወገድ በአካባቢው ላይ የሚታየውን የቻይና እና የኢራን ተፅዕኖ ከመቀነስ ባለፈ፣ ቀይ ባሕርን ከሽብር ስጋት ነፃ በማድረግ የዓለም ንግድ ፍሰት በሰላም እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በተጨማሪም፣ ይህ የቀጥታ ጣልቃ ገብነት እርምጃ የአገዛዙን መውደቅ ተከትሎ የሚመጣው አዲስ ሥርዓት በኢትዮጵያና በኤርትራ ዳያስፖራዎች ዘንድ ተቀባይነትን እንደሚያገኝና ይህም ለአሜሪካ ቀጠናዊ ወዳጅነትን እንደሚያጠናክር እየተገለጸ ይገኛል። የአገዛዝ ለውጡ በኤርትራ ውስጥ ለዓመታት የሰፈነውን የግዳጅ ውትድርና እና የሰብአዊ መብት ረገጣ በማቆም፣ አገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም የምትኖርበትን ዕድል እንደሚከፍትና ይህም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የጸጥታ ስጋት በዘላቂነት እንደሚያስወግድ የፖሊሲ አፍላቂዎቹ በሰፊው ይተነትናሉ።
በዚህ የፓሊሲ ሃሳብ ዙሪያ ለአዲስ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፤ እንደ AEI ያሉ የአሜሪካ የፖሊሲ ሐሳብ አፍላቂ ተቋማት እንዲህ ዓይነት አስተያየት ከሰጡ፣ የኤርትራ መንግሥት ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ የቆመ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል። በመሆኑም በዋሽንግተን የፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ኤርትራ እንደ ቀጠናዊ ስጋት መታየቷ፣ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አገዛዝ የኒኮላስ ማዱሮ ዓይነት ዕጣ ፈንታ ሊደርሰው እንደሚችልና ይህም ለአካባቢው ሰላምና ደኅንነት ሲባል የሚወሰድ አስፈላጊ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አስገንዝበዋል። አክለውም ከልምድ እንደሚታየው እንዲህ ያለ ጉዳይ እንዲሁ ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ እንደማይታተም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ዶናልድ ትራም ለጻፉት የድርድር ግብዣ ደብዳቤ ካስወመጠቻቸው ነጥቦች መካከል ግብጽ፣ የአፍሪቃ ቀንድን ብሎም ኢትዮጵያን ለማተራመስ ሌት ከቀን የሚሰራውን “አሸባሪ መንግስት” ለመንቀል ተባባሪ መሆን እንደሚገባትና ይህን እንድትቀበል ጠይቃለጭች። ይህ ድርድሩ ላይ የሚቀርብ አንዱ ጉዳይ ብቻውን ለአሜሪካ ጥቅም መከበር አሜሪካ ልትወስደው የሚገባ እርምጃ መሆኑ መገጣጠም ሊባል እንደማይችልም ተመልክቷል። አንዳንዶች ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በቅርቡ ከሁለት ሰዐት በላይ ስድብና ቁጣ አዘል ትችት የሰነዘሩት ይህንን አካሄድ ቀድመው ስለሚያውቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






