ጦርነቱ እንደ ጅማሬው ባይሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች እንደቀጠለ ባለበት፣ በተለይም በጠለምት ጦረነቱ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተዛውሮ የአገር መከላከያ ያማጻዳት ስራ እየሰራ መሆኑን ባስታወቀበት በአሁኑ ወቅት ትህነግ የሰላም ውይይት እንደሚቀበል ማስታወቁ ተሰማ። ከፋኖ፣ ሻዕቢያና ከሱዳን ካሉ ታጣቂዎቹ ጋር በቅንጅት ጦርነት የከፈተው ትህነግ በምን መነሻ የሰላም ውይይት ፍላጎቱን የሚያሳይ ደብዳቤ ሊጽፍ እንደቻለ ለበርካቶች ግራ ሆኗል።
“የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያለውን አክብሮት ይገልጻል” ይላል በዶክተር ደብረጽዮን ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ። “ክቡርነትዎ” ሲል ለተጠራቸው መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የተላከው ደብዳቤ፣ ድርጅቱ በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ስለሰጠው መግለጫ አመስኟል። መግለጫውንም በበጎ እንደሚያየው አስታውቋል።

ደብዳቤው “ትህነግ የሰላም እና የውይይት ጥሪውን የሚቀበል ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚያደርገውን መርህ-ተኮር ተሳትፎ ያደንቃል” ካለ በሁዋላ፣ “ትህነግ በትግራይ እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት መካከል ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ብቸኛው እና ዘላቂው መንገድ ውይይት መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል። ይህም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ቃል እና መንፈስ ሙሉ በሙሉ በተከተለ መልኩ መሆን እንዳለበት ያምናል” ሲል አሳቡን ያስታውቃል።
በዚህ ረገድ፣ ትህነግ በአፍሪካ ህብረት በሚመቻቹ ማንኛቸውም የውይይት መድረኮች ላይ ገንቢ በሆነ መልኩ ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን (High-Level Panel) አማካኝነት የሚደረጉ የሰላም፣ የመተማመን ግንባታ እና የእርቅ ስራዎችን እንደሚያካትት አመልክቷል።
ወቅታዊ፣ ተከታታይነት ያለው እና ንቁ ተሳትፎ ለውይይቱ ስኬት እንዲሁም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ጀምሮ የተገኙ ውጤቶችን ጠብቆ ለማቆየት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ትህነግ በደባዳቤው አመልክቷል። የታደሰ እና የተጠናከረ የአፍሪካ ህብረት ተሳትፎ በአሁኑ ወቅት ያለውን መቀዛቀዝ (impasse) ለመሻገር የሚያስችል ግፊት ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳለውም አመልክቷል።
ደብዳቤው ትህነግ ለሰላም እና ለመረጋጋት ጽኑና ቁርጠኝነት አቋም እንዳለው አመልክቷል። አክሎም |ትህነግ በእውነተኛ፣ አካታች እና ውጤት ተኮር በሆነ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ እንዲጠናከር እንጠብቃለን” ብሏል።
በውጭ አገር የሚገኙ የሻእቢያ፣ የትህነግና የፋኖ ደጋፊ ሚዲያዎች የተጀመረው ጦርነት በአጭር ቀናት መንግስትን መገልበጥ እንደሚያስችል በስፋት እየተናገሩ ባለበት ወቅት፣ የተጀመረውንም ጦርነት ትህነግ በበላይነት እያስኬደው እንደሆነ እየዘገቡ ባለበት ሁኔታ ትህነግ ለውይይት ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ መሆኑን ጠቅሶ ደብዳቤ መጻፉን አስመልክቶ ምን እንደሚሉ ከወዲሁ የታወቀ ነገር የለም። የሻዕቢያ ደጋፊ ሚዲያዎች ትግራይ የመገንጠል ጥያቈ እንድታነሳ በመተየቀ አጀንዳውን ለማዞር እየመኦከሩ እንደሆነ ታይቷል።
ትህነግ ከተስማማና በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ወደ ትግበራ የሚገባ ከሆነ አብረውት ለመስራት ቃለ ያሰሩት የፋኖ ታጣቂዎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ እያነጋገረ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






