አዲስ ሪፖርተር – “እኛና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ሁለት ድርጅት ነን” ይላሉ አቶ ለሚ የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ የኦፌኮ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጉርሜሳ አያኖ ደግሞ “ትርምስ አጀንዳችን አይደለም። ከቶውንም አናስበውም” ይላሉ። የእናት ፓርቲና የሶዴፓ የተለያዩ ኃላፊዎች ከትርምስ ፖለቲካ ትርፍ አለ ብለው የማያምኑ የሰላም ትግል ተጓዞች እንደሆኑ ያስረዳሉ።
ይህ የተለያዩ ፓርቲዎች አቋም የተሰማው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጃዋር መሐመድ በኢትዮጵያ ከሚነቀሳቀሱ ህጋዊ ፓሪዎች ጋር በመላው አገሪቱ ህዝባዊ ቁጣና አመጽ ለማቀጣጠል ስምምነት መደረሱን ማስታወቁን ተከትሎ ነው።
“አሁን ዐቢይ የሚመራው የሽግግር መንግሥት ነው … ማንም ያለ ምርጫ በሽግግር መንግሥት ስም ሥልጣን በአቋራጭ መሞከር አይችልም” ብሎ ለውጡን የተቀላቀለው ጃዋር፣ አፍታም ሳይቆይ “ሁለት መንግስት አለ አንዱ አብይ ሁለተኛው እኔ ነኝ” በማለት ወደ ጡንቻ መለካካት ተዛወረ፤
በጃዋር ስር የተደራጁ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ጀምሮ እስከ ዝዋይ፣ መቂ፣ ሻሸመኔና አርሲ ንጹሃንን ጨፈጨፈፉ። ንብረታቸውን አወደሙ። ዓላማውና ጥሪው አመጽ በመሆኑ ባልተዘጋ ፋይል ከማረሚያ የወጣው ጃዋር፣ አሁንም ትንፋሽ ስቦ ሌላ አመጽ እየጠራ ነው። ይሳካል፣ አይሳካም? ሰሚ ጆሮ አለ ወይስ የለም? የሚለው ወደፊትይ የሚታይ ቢሆንም ራሳቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች አድርገው የሚጠሩት አቶ ያሬድ ኃይለ ማሪያም በቅርቡ በአብሮነት የግብረኃይል ምስረታ ምርጫ ላይ ” ይህን መንግስት ለመጣል ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እንሰራለን” እንዳሉት ሌሎችን እያነካካ ነው። በአዲስ አበባ ያሉት ፓርቲዎች የቀረበላቸው የትርምስ ግብዣ ስለመኖሩ የሰጡት መልስ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘውም ከዚሁ አንጻር ነው።
ጃዋር ትርምስ ለመፈጠር ሁሉንም እንዳሳመነ የተናገረው አዲስ የጋራ መንግስት ለመመስረት እየተመካከራቸው ላሉት የትህነግ አንጋፋ ሰዎች ነው። በእስር ቤት ተጀምሮ የነበረውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ መንግስትን በትጥቅና በሕዝብ አመጽ ለማስወገድ የተያዘው ዕቅድ ይፋ የሆነው በአቶ ልደቱ አያሌው በሰላማዊ ትግል ስም በተመሰረተው አብሮነት በኩል መሆኑ አይዘነጋም።
ከአብሮነትም ሆነ አብሮነት ከቀፈቀፈው አመጽ ከሚያደራጀው ግብረኃይል ራሱን ያገለለው ጃዋር፣ ራሱን ከሁለቱም የሻዕቢያ አደረጃጀቶች ያገለለው በመሃልና በውጭ ከኦሮሞ ተወላጆች በደረሰበት ተቃውሞ እንደሆነ አዲስ ሪፖርተር ማስነበቧ አይዘነጋም።
“የጋላን መንግስት እንነቅላለን። የአባቶቻችንን ርስት እናስመልሳለን” በሚል በዋሽንግቶን በግልጽ ባነር ተለጥፎ በተካሄደ የገቢ መሰባሰቢያ ላይ በተላለፉ መልዕክቶች እንደ ማህበረሰብ የኦሮሞ ሕዝብ ክፉኛ መቆጣቱ አይዘነጋም። ይህንኑም ተከትሎ ይህን ዘርና የበላይነት ላይ ተንተርሶ የተደራጀን ቡድን በመቀላልቀል ኦሮሞ ላይ የሚዘምቱ የኦሮሞ ተወላጆች እጅግ የተወገዙ በመሆናቸው ጃዋር ራሱን ከአብሮነት እንዲያገል አድርጎታል።
ይህ ከሆነ በኋላ ጃዋ ሆነ ብሎ ባልተገኘበት የግብረኃይሉ ስብሰባ ላይ አቶ ልደቱ አያሌው “ተስማምቷል” በሚል ማብራሪያ አቅርበው ስራ አስፈጻሚ ተደርጎ ቢመረጥም፣ በጥድፊያ ከዚሁ የአመጽ አድማ አደራጅ ግብረኃይል ራሱን ማግለሉን አዲስ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት ማስታውቋ አይዘነጋም።
በገሃድ “ከነዚህ ሰዎች ጋር መስራት አይቻልም” በሚል ጃዋር ራሱን ቢያገልም፣ ከግብጽና ኤርትራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው የትህነግ ባለቤቶች ከሚባሉት አዛውንት ኃይሎች ጋር በጥምረት እየሰራ እንደሆነ አዲስ ሪፖርተር አረጋግጣለች። በዚሁ አግባብ አሁን ሊጀመር ዳር ዳር እያለ ያለውን ጦርነት በአመጽ ለማገዝ ጃዋር የተሰጠውን የቤት ስራ አስመልክቶ ሪፖርት ሲያቀርብ፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ ፓርቲዎች፣ የፓርቲ አመራሮችና አደረጃጀቶች ጋር አመጽ ለማቀጣጠል ከስምምነት መድረሱን አስታውቋል። ጃዋር ይህን ኃላፊነት ሲይዝ በዋናነት “ኦሮሞ አላምጽም አለ” በሚል በተያዘ አቋም ሳቢያ በከፍተኛ በጀት ነው።
ይህንኑ አደገኛ አካሄድ አስመልክቶ አዲስ ሪፖርተር የኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ሶዴፓና እናት ፓርቲ አመራሮችን በማነጋገር አስተያየታቸውን አካታለች። ጃዋር መሐመድን በተደጋጋሚ ለማግኘት ያደረገነው ሙከራ አልተሳካም።
አመጽ ለማደራጀትና መንግስትን ለመናጥ ሻዕቢያ ባደራጀው ግብረኃይል ውስጥ ዋናው አራጊና ፈጣሪ፣ በጀት አደራጅ አቶ ነዓምን ዘለቀ መሆናቸው በግልጽ እየታወቀ፣ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ሕግ መሰረት በሰላማዊ ትግል ለመታገል ወደውና ፈቅደው መመዝገባቸው ስለሚታወቅ እንዴት በዚህ መሰሉ አግባብ ሊሳተፉ ተስማሙ? መንግስትስ ይህን አውቆ ወደ እርምጃ ቢሄድ በምን ሊወቀስ ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት አነጋግረናቸዋል።
ጃዋር ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆነበት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጉርሜሳ አያኖ የሰሙትን አያምኑም። የተጠቀሰውን አመጽ አደራጅ ድርጅት በሚዲያ እንደሚያዩት አመልክተዉ አንዳችም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል። ሊገናኙ የሚችሉበት አግባብም እንደሌላ አመልክተዋል።
አቶ ጉርሜሳ ስለተነሳው በደቦ አምጽ ማነሳሳት ጉዳይ ሲመልሱ ያነሱት መተዳደሪያ ደንባቸውንና በምርጫ ቦርድ ህግ መሰረት በሰላማዊ ትግል ለመታገገል ውል የገቡ መሆናቸውን ነው። ድርጅታቸው ሲቋቋም ጀምሮ “ትግልን ማዘመን” የሚል መርህ እንዳለው አመልክተው፣ በዚህም ጠብመንጃ የያዘ ሁሉ ወደ ጠርጴዛ ውይይት እንዲመጣ ከመጣር ውጪ ትርምስ ከቶውንም የድርጅታቸው እምነት እንዳልሆነ፣ ተቀባይነትም እንደሌለው አስረድተዋል። በግል አቶ ጃዋር ለሚያራምዱት አቋም ድርጅቱ የሰጣቸው ማንዴት ስለሌለ እሳቸው ሊጠየቁበት እንደሚችሉ ቀደም ሲል ሌላ የፓርቲው አመራር በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ተጠይቀው መመለሳቸው አይዘነጋም።
አቶ ጌትነት ወርቁ የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። አብሮነት ጥቅምት ወር አካባቢ በበይነ መረብ የቀጥታ ስብሰባ ሲያካሄድ የፓርቲያቸው ሊቀመንበር ተሳታፊ ሆነው ንግግር ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ከፋኖ፣ከትህነግ፣ ከኦጋዴን ነጻ አውጪ፣ ከኦነግ ሸኔ ወዘተ የተወከሉ ንግግር ማድረጋቸውንም ይጠቅሳሉ። ዓላማው ሁሉም መሳሪያ አስቀምጠው ከአፈ ሙዝ በታች ባሉ አማራጮች ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ እንደነበር ካስታወሱ በሁዋላ፣ ከምርጫው በፊት በኢትዮጵያ አመጽና ትርምስ ለማስነሳት የተዘጋጁ ቡድኖች እንዳላገኟቸው አስታወቀዋል።
“ህገመንግስታችን በሚደግፈው የሰላማዊ ትግል እንሳተፋለን እንደግፋለን” የሚሉት አቶ ጌትነት፣ የቀረበላቸውን ጥያቄ አስመልክቶ በግልም ይሁን በድርጅት ደረጃ የቀረበ ጥሪ አለመኖሩን በድጋሚ አስታውቀዋል። አክለውም ምን እየሰሩም እንደሆነ እንደማያውቁ ገልጸዋል። አቶ ጌትነት ከቀረበላቸው ጥያቄ በተጨማሪ በስፋት ያጋሩንን ሃሳብ በሌላ ጊዜ አናቀርባለን።
በአብሮነት አማካይነት በተቋቋመው ሕዝባዊ ቁጣ አቀጣጣይ ግብረሃይል ውስጥ፣ በስራ አስፈጻሚነት ከተመረጡት አምስት ሰዎች መካከል አንዱ አቶ ጃዋር ቢሆኑም “ከፊት ለፊት ይልቅ ከኋላ” በሚል ስራ አስፈጻሚውን እንዳልተቀላቀሉ አዲስ ሪፖርተር የስብሰባውን ቅጂ በማስደገፍ ዜና አጋርታ እንደነበር ይታወሳል።
በዚሁ ወቅት ሃያ አንድ የሚሆነውን የአብሮነት ቦርድ ያነታረከው ኦብነግ፣ ኦነግ ሸኔ፣ ሻዕቢያና ትህነግን አስመልክቶ የተያዘው የተለያዩ አቋሞች ነበሩ።
የሶማሌ ክልልን ለመገንጠን የሁለት ወረዳ ተወላጆች ይዞ ሃርጌሳ የሚመላለሱ ስድስት ሰዎችን እንደ ድርጅት ቆጥሮ እውቅና መስጠት እንደ ኢትዮጵያዊ አሳፋሪ ነው ያሉ ተሰብሳቢ ነበሩ። ከሻዕቢያ ጋር የሚደረገውና ከግብጽ ጋር እየተከናወነ ያለው ግንኙነት ከብሄራዊ ጥቅም አንጻር ሊሰላ ይገባል ያሉ “አካሄዱ አገር አልባ ሊያደርገን ይችላል። መንግስትን በመጥላት ስም ታሪካዊ ስህተት እንዳንሰራ” በማለት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
አቶ ነዓምን “ይህ ጥያቄ አሁን ሊነሳ አይገባም። ስለ ኤርትራ ማውራት አግባብ አይደለም” በማለት ምላሽ ሲሰጡ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “ከአቶ ነዓምን ጋር እስማማለሁ” ሲሉ የሚያስረዳ የኦዲዮ ቅጂ በአዲስ ሪፖርተር የዩቲዩብ ገጽና ድረገጽ ላይ መታተሙ አይዘነጋም።
የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ “የምን አመጽ” ሲሉ ነው የጠየቁት። ኦነግና ኦፌኮ ሁለት ድርጅቶች መሆናቸውን አመልክተው፣ ግንኙነታቸውም በዚያው አግባብ መሆኑን አስታውቀዋል።
ስለተቋቋመው ግብረኃይልም ሆነ ጃዋር ስለሚለው ጉዳይ ምንም የሚያውቁት እንደሌለ አስታውቀዋል። አክለውም “በግል ደረጃ ከጃዋር ጋር የምንነጋገረውም ሆነ የምንሰራው ስራ የለም” በለዋል።
አቶ ለሚ ጥያቄውን ለመስማትና ለማስተናገድ መገረም ቀድሟቸዋል። እየተገረሙ “ደግሜ ላስረዳ፣ በግለሰብ ደረጃ የምነነጋገረው ነገር የለም። እኛ ድርጅት ነን፣ ከኦፌኮ ጋር በድርጅት ደረጃ አብረን እንሰራለን” ብለዋል።
ዶክተር ራሔል ባፌ ልክ ሌሎች እንዳሉት መነሻቸው የተቋቋሙበት ደንብና ሕገመንግስቱ ነው። “ሰላማዊ ፓርቲ ነን፤ በአመጽ ሂደት ውስጥ አንገባም” ያሉት ዶክተር ራሔል፣ እነ አቶ ልደቱ አመጽ ለመቀሰቀስ ሳይሆን በምርጫ ህዝብ እንዲወስን የሚሰሩ ናቸው ሲሉ ምስክር ሆነዋል።
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በአብሮነት ቦርድ ውስጥ የትጥቅ ትግሉን ከሻዕቢያ አመራር በመውሰድ የሚቀሰቅሱ፣ የሚያከናውኑ እንዲሁም የጦርነት ዜናዎችና የጦርነት መረጃ ናቸው የሚሉዋቸውን በፈጠራ ጭምር ባሏቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በውክልና በሚያስተዳድሯቸው ሚዲያዎች፣ እንዲሁም አክቲቪስቶች አማካይነት ሳምንቱን ሙሉ፣ ያለ አንዳች ዕረፍት የሚሰሩ መሆናቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችቻቸውና ቃለ ምልልሶቻቸው ይመስከራሉ። በተለይም የአመጹ መሐንዲስ ከሚባል፤ኡት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር የሚያስተላልፉት መረጃ ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።
በዚሁ ስብስብ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔልም ተካተዋል። ፕሮፌሰሩ በሶማሌ አቅጣጫ ያለውን ወጣ ገባ የሚል እንቅስቃሴ ቱርክ ድረስ በመመላለስ የሚያሳልጡና፣ ይህንኑ ኃላፊነት ከግብጽ የተረከቡ መሆኑን አብረዋቸው ከሚሰባሰቡት መካከል የተመሰከረባቸው ናቸው። ሌሎችም ሱዳን ያለውን የትህነግ ኃይል ለመርዳት በሚል ሎጂስቲክ የምኪያመላልሱ አባላት ያለበት አብሮነት እንዴት “የሰላማዊ ትግል አራማጆች? ሊባሉ ይችላሉ?” ለሚለው ጥያቄ አቶ ልደቱ ተጠይቀው ዝምታን መርጠዋል።
“ሶዴፓ ጦርነት አብቅቶ ሕዝብ የመረጠው ፓርቲ በምርጫ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ይሰራል። ብልጽግና አሁን በያዘው አግባብ፣ ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ፓርቲያቸው አይፈቅድም” ያሉት ዶክተር ራሔል፣ ይህም ተግባራዊ የሚሆነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው ብለዋል። ዶክተር ራሔል አብሮነት ስብሰባ ላይ ከተገኙ መካከል መሆናቸው አይዘነጋም።
ዶክተር ራሔል፣ “ዛሬም ነገም የአመጽ አካል አንሆንም፣ ልንሆንም አንችልም” በማለት በ192 ምርጫ ወቅት የሆነውን አስጨናቂ ገጠመኝ አስታውሰዋል። በውቀቱ እናት ከነልጆቿ መገደሏን፣ በርካቶች አካል ጉዳተኛ እንደሆኑ ጠቁመው ያን መሰል ታሪክ እንዲደገም አንሻም ብለዋል። አክለውም ከሃዘኑ ግዝፈት የተነሳ የ1993 የስራ ዘመን ፓርላማ ሲጀመር በህሊና ጸሎት መጀመሩት አመልክተዋል።
“አልጸጸትም” በማለት በአማርኛና በኦሮምኛ መጽሐፍ የጻፈው ጃዋር መሐመድ፣ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጋር የዘመኑ ትምህርት ሲጀመር አመጽ ለማቀጣጠል ከስምምነት መደረሱን ጠቅሶ ለተናገረው፣ የማህበሩ ፐሬዚዳንት ” በመምህራን ኑሮና ህይወት ላይ ከመንግስት ጋር ተግባብተን እየሰራን ነው። ጃዋርንም አግኝተነው አናውቅም። ቅጥፈት ነው” በማለት ለአዲስ ሪፖርተር ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ጃዋርን ሪፖርቱን ያቀረበው ግብጽ፣ ሱዳን፣ ሻዕቢያ፣ ወልቃይትን አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቷል የሚባለው የዘመነ ካሴ ፋኖና ትህነግ በጋራ ጦርነት ለመክፈት ከጫፍ በደረሱበት ወቅት ሕዝባዊ ቁጣና አመጽ በፍጥነት መቀጣጠል አለበት በሚል ከዋናዎቹ ስፖንሰሮችና የስፖንሰሮቹ ወዳጆች ጋር ባደረገው ውይይት እንደሆነ ታውቋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






