ሮይተርስ በአዲስ አበባ ያሰማራቸው ሶስት ጋዜጠኞቹ የስራ ፈቃዳቸው እንዳልታደሰና የአፍሪክ ሕብረት ጉባኤን ለመከታተል የተሰጠ ፈቃዳቸውንም መነጠቃቸው ተሰምቷል። ይህንኑ መረጃ በግል የጽሁፍ መልዕክት እንደደረሰው ያመለከተው ንብረትነቱ የወይዘሮ ጸዳለ የሆነው አዲስ ስታንዳርድ ነው። ዜናው ይህ እስከታተመ ድረስ በመንግስት ማናቸውም የሚመለከታቸው አካላት ይፋ አልሆነም። አዲስ ሪፖርተር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ የግል ስልክ ላይ እና በድረገጹ የተቀመጡ፣ የማይነሱ፣ የማይሰሩ ስልኮች ላይ ማጣራት ለማድረግ ሞክራ አልተሳካለትም።
“ይህ እርምጃ የተወሰደው ሮይተርስ ኢትዮጵያ ለሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) የማሰልጠኛ ካምፕ መገንባቷን የሚገልጽ የምርመራ ዘገባ ካወጣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው” ሲል አዲስ ስታንዳርድ ግምቱን ሰጥቷል። ጋዜጣው አክሎም የሮይተርስ ቃል አቀባይ ዜናውን በጽሁፍ እንዳረጋገጠለት አስታውቋል።
የዜና ወኪሉ ውሳኔውን እየገመገመው መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ “ሮይተርስ የቶምሰን የሥነ-ምግባር መርሆችን በመከተል ስለ ኢትዮጵያ ገለልተኛ፣ አድልዎ የሌለበትና ተዓማኒነት ያለው ዘገባ ማቅረቡን ይቀጥላል” ማለታቸው ተሰምቷል።
ሮይተርስ ከቀናት በፊት የተለያዩ የዲፕሎማቲክ፣ የጸጥታ እና ይፋ ያላደረጋቸውን የመንግሥት ምንጮችን ጠቅሻለሁ በማለት “ኢትዮጵያ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የማሰልጠኛ ካምፕ አዘጋጅታለች” የሚል በራሱ በዘገባው መሰረት ያልተረጋገጠ መረጃ ማሰራጨቱ ይታወሳል።
ሮይተርስ ይህ ዘገባ ከመዘገቡ ውጭ ግብጽ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጣልቃ በመግባት ሱዳን እንዳሉ የሚታወቁ ታጣቂዎችን በማደራጀት፣ በገሃድ ማሰልጠኛ በመክፈትና ከባድ መሳርኪያ በማስታጠቅ ወደ ኢትዮጵያ ስታሳመራ “የምርመራ ዘገባ” ብሎ ያነሳውን የሰራውም ሪፖርት የለም።
ሮይተርስ በግብጽ የሚደገፈው የጄነራል አልቡርሃን ጦር ድፍን የብሉ ናይል አካባቢዎችን ማስረከቡን፣ የዳጋሎ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሁርዱፋን በእካቸው አሰገብተው ወደፊት እየገሰገሱ ባለበት ሰዓት መሆኑ የሪፖርቱን ተአማኒነት ሰብሮታል። አዲስ ሪፖርተር ይህንኑ አስመልክቶ ባደረገችው ማጣራት መረጃው የተሳሳተ እንደሆነ ማረጋገጧም ይታወሳል።
“ሮይተርስ በ15 ምንጮች እና በሳተላይት ምስል ትንታኔ ላይ ተመስርቶ ባቀረበው ዘገባ፣ ስፍራው በሱዳን እየተካሄደ ላለው የእርስ በርስ ጦርነት አዳዲስ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ምልምሎችን ለማሰልጠን ሳይውል እንዳልቀረ ጠቁሟል። የዜና ወኪሉ በካምፑ ውስጥ ስለሚገኙት ግለሰቦች ማንነትም ሆነ ምልመላው ስለተከናወነበት ሁኔታ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጿል” ሲል አዲስ ስታንዳርድ የሮይተርስ ሰራተኞች ፈቃድ አለመታደስና የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን እንዳይከታተሉ መከልከላቸውን ፍትህ የጎደለው እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራል።
አዲስ ሪፖርተር ሮይተርስ ዘገባውን ይፋ እንዳደርገ፣ የሚከተለርውን አትማ ነበር። በመጀመሪያ ዘገባው እራሱ የጠቀሳቸው መረጃዎች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መሆናቸውን ማየት ይቻላል። ዘገባው የሳተላይት ምስሎችን እንደ ዋነኛ ማስረጃ ቢያቀርብም፣ በምስሎቹ ላይ የቀረበው ትርጓሜ ግን ተዓማኒነት የጎደለው ነው። ለዚህም ትልቁ ማስረጃ ታዋቂው የመከላከያ መረጃ ተንታኝ Janes የሰጠው አስተያየት ነው፤ ሮይተርስ በዘገባው ላይ “Janes said it could not confirm the site was military based on their analysis of the imagery” በማለት የገለጸው ሀሳብ፣ የቀረበው ምስል ወታደራዊ እንቅስቃሴን እንደማያሳይ በተዘዋዋሪ ያረጋግጣል። ይህ ሆኖ ሳለ ሮይተርስ “ሚስጥራዊ የጦር ካምፕ” የሚል ስያሜ መስጠቱ ዘገባው አስቀድሞ ኢትዮጵያን ለመወንጀል ታቅዶ የተሰራ መሆኑን ያሳያል።
በሁለተኛ ደረጃ ዘገባው የተመሰረተባቸው ምንጮች ማንነት ጥርጣሬ የሚጭር ነው። ሮይተርስ በዘገባው ውስጥ “Eight sources, including a senior Ethiopian government official…” እና “The news agency spoke to 15 sources…” እያለ ቢገልጽም፣ አብዛኛዎቹ ምንጮች በስም ያልተጠቀሱ መሆናቸው መረጃው ተዓማኒነት እንዲያጣ ያደርገዋል። እንዲህ ያሉ ለደህንነት ሲባል ስማቸው አልተጠቀሰም የሚባሉ ምንጮች፣ ብዙውን ጊዜ ለፖለቲካዊ ፍጆታ የሚፈጠሩ ወይም በአንድ ወገን የሚሰጡ የተዛቡ መረጃዎች መሆናቸው የታወቀ ነው። ይህ መረጃውን በገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
በሦስተኛ ደረጃ፣ ዘገባው የአሶሳ አውሮፕላን ማረፊያን ከሱዳን ጦርነት ጋር ለማገናኘት የሄደበት ርቀት እጅግ አሳሳች ነው። ሮይተርስ “The analyst and the expert said the airport had become instrumental in supplying the RSF across the border in Sudan” በማለት ያሰፈረው ሀሳብ፣ ምንም ዓይነት ተጨባጭ የበረራ መረጃ (Flight tracking) ወይም ተያያዥ ማስረጃ የሌለው ግምት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ የራሷን ድንበርና እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ስትራቴጂካዊ ተቋማትን ለመጠበቅ የአየር ኃይል አቅሟን የማጠናከር ሉዓላዊ መብት ያላት ቢሆንም፣ ይህንን ከጎረቤት ሀገር አማጺያን ጋር ለማገናኘት መሞከር የተለመደ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው።
በአራተኛ ደረጃ፣ በዘገባው ውስጥ የተጠቀሱት የጭነት መኪናዎች መረጃ እጅግ ደካማ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ነው። ሮይተርስ “The news agency could not independently verify what the trucks carried…” በማለት በግልጽ የተቀመጠው ሀሳብ፣ በጭነት መኪናዎቹ ውስጥ ሰራዊት ስለመኖሩ ወይም ስላልመኖሩ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ እንደሌለው ያሳያል። መኪናዎቹ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሞዴል መመሳሰላቸው ብቻ፣ ለሌላ ሀገር ታጣቂዎች ስልጠና እየዋሉ ነው ለማለት የሚያስችል በቂ መነሻ ሊሆን አይችልም። ይህ የሚያሳየው ዘገባው በግምት ላይ የተገነባ መሆኑን ነው።
በአምስተኛ ደረጃ፣ የዘገባው አዘጋጆች ያሉበት ቦታና የዘገባው ጊዜ የግብፅን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው። ሮይተርስ በመጨረሻው ክፍል ላይ “Additional reporting by Alexander Dziadosz, Nafisa Eltahir and Ahmed Shalaby in Cairo” በማለት የዘገባው አንድ አካል የሆኑ ጋዜጠኞች መቀመጫቸው ካይሮ መሆኑን ገልጿል። ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላትን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን በቀጠናው ውስጥ እንደ ስጋት አድርጎ የማቅረብ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ይታወቃል። ዘገባው በዚህ መልኩ መቀናበሩ፣ የግብፅን የዲፕሎማሲ አጀንዳ ለማስፈጸም የታለመ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
በስድስተኛ ደረጃ፣ ዘገባው በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) መካከል ያለውን የልማት ትብብር ለክፉ ዓላማ ለማዋል ሞክሯል። ዘገባው “UAE financed the camp’s construction and provided military trainers…” የሚለውን ክስ ቢሰነዝርም፣ ሮይተርስ እራሱ “The news agency could not independently verify UAE involvement in the project or the purpose of the camp” በማለት ሀሰተኝነቱን በራሱ ቃል አረጋግጧል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግልጽ የኢኮኖሚ ትብብር እንደ “ሚስጥራዊ ወታደራዊ ጥምረት” ተደርጎ መቅረቡ፣ በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ነው። ሙሉውን ዘገባ እዚህን ሊንኮች ተጭነው ያንብቡ
A Critical Examination of Reuters’ Geopolitically Motivated Allegations
የሮይተርስ የሀሰት ዘገባ ሴራ – በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ልክፍት በማስረጃ ሲጋለጥ
Exposing the Reuters Disinformation Campaign: A Strategic Attack on Ethiopia’s Sovereignty
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






