ኣዲስ ሪፖርተር – በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ሰባት ወራት በጋራ ገቢዎች፣ አስተዳደርና ትልልፍ ቀመር መሠረት 71 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር ለክልሎች ማስተላለፍ መቻሉን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ለክልልና ፌደራል ባለድርሻ አካላት በጋራ ገቢዎች አስተዳደር፣ አሰባሰብና ትልልፍ አፈፃጸም ላይ የተደረገ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርትን በማስመልከት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፥ በፌደራልና ክልል መንግስታት መካከል ያለውን የጋራ ገቢዎች አስተዳደርና ክፍፍል ሥርዓት ለማጠናከር ውጤታማ ስራ መሠራቱን ገልጸዋል። በቅርቡ ተግባራዊ በተደረገው አዲስ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር መሠረት ማሻሻያ በማድረግ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የገቢዎችና የማዕድን ሚኒስቴርም አዲሱን የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር በመከተል የገቢ ዝውውር ሥርዓቱን የሚያፋጥን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ልማት በመዘርጋት ለምክር ቤቱ ውሳኔ ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል። በተሻሻለው የአሰራር ሥርዓት ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የክልል መንግስታት ገቢ ዕድገት እያስመዘገበ መምጣቱን አስረድተዋል።
በዚህም የጋራ ገቢ ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የነበረው የክልሎች ድርሻ በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ወደ 91 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር ማደጉን ገልጸዋል። በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት 71 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር ለክልሎች ማስተላለፍ መቻሉን አብራርተዋል።
በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል በተፈጠረው ጠንካራ ቅንጅት የመጣውን ለውጥም የፌደራል ሥርዓቱንና የለውጡን ግብ የሚያሳካ ነው ብለዋል። የፌዴራልና የክልሎች የጋራ ገቢዎች አካል የሆነው የከፍተኛ ማዕድንና ፔትሮሊየም ልማት ሃብቶች የሚሰበሰበው የሮያሊቲ ገቢዎች ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል። የጋራ ገቢዎች አሰባሰብ፣ አስተዳደርና ትልልፍ በማሻሻል የህዝቡን የልማትና የተመጣጠነ ዕድገት ለማረጋገጥ የሁሉንም አይነት የገቢ አማራጮች ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የፌዴራልና የክልሎች የጋራ ገቢዎች አካል የሆነው ከከፍተኛ ማዕድንና ፔትሮሊየም ሀብቶች ልማት የሚሰበሰብ የሮያሊቲ ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻሻያ እያሳየ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ለክልሎች የሚተላለፉ የሮያሊቲ ገቢዎች አፈፃፀም በገለልተኛ አካል የፋይናንስ ኦዲት በማድረግ ግልጽነትና ተጠያቂነት መፍጠር የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።
በዚህም ከሁለት ዓመታት በፊት በገቢዎች ሚኒስቴርና በማዕድን ሚኒስቴር የጋራ ገቢዎች፣ አስተዳደርና ትልልፍ ላይ በፌደራል ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ኦዲት ቀርቦ የጋራ መግባባት በመፍጠር ሪፖርት መዘጋጀቱን አንስተዋል። በሁለቱ ተቋማት የሚተገበረው የጋራ ገቢዎች፣ አስተዳደርና ትልልፍ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ግኝት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ፥ አዲሱ የጋራ ገቢዎች፣ አስተዳደርና ትልልፍ ሥርዓት በመርህ ላይ የተመሠረተና ግልጸኝነትን የተላበሰ ነው ብለዋል። በትግብራውም የገቢዎችና የማዕድን ሚኒስቴር አፈፃጸምና የክልሎች ድርሻ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






