አዲስ ሪፖርተር የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተከታታይ አዲስ አበባ መገኘት የተለያዩ ፍላጎት ባላቸው ወገኖች የተለያየ አስተያየት እየተሰነዘረበት ነው። በቅርቡ ከኤርትራ ጋር ጥምረት የፈጠሩት ትህነግና ፋኖ የባለስልጣናቱን መመላለስ አልወደዱትም።
ከሳምንት በፊት ኤርትራ የነበሩት የሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አልኬሬጂ ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውን ተከትሎ ነው ይህ አስተአየት የተሰማው። ሚኒስትሩ ዛሬ በማለዳ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
የሳዑዲ አረቢያው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሳምንት በፊት በአሥመራ ተገኝተው ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በቀይ ባሕር እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።
በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መውያየታቸው ይፋ ተደርጎ ነበር። ስለ ንግግሩ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጥም ለውጡን ተክትሎ ኢትዮጵያና ኤርትራን ያሸማገለችውና በርካታ ውል አፈራርማ የነበረችው ሳዑዲ አረቢያ ከመሆኗ አንጻር ሁለቱን አገራት የማሸማገል ስራ እየተሰራ መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ከርመዋል።
ዛሬ አዲስ አበባ የተገኙት ዋሊድ አልኬሬጂ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአቻቸው ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር ስለ ቀጠናው ስትራቴጂክ ጉዳዮች እንደመከሩና የሁለቱን ሃገራት አጋርነት የሚያጠናክር ስምምነቶች እንደተፈራረሙ ተገልጿል። ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምስራቅ መካከል ያለው የጂኦ-ፖለቲካዊ ትኩሳት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ትርጉም የሚሰጠው ሆኗል።
ይህ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዘመናት የቆየውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ‘የጋራ ትብብር’ የሚያሸጋግር ሲሆን፣ በተለይም በቀጣናዊ ደኅንነትና ሰላም ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ይበልጥ ያጠናክራል። ሳዑዲ አረቢያ ለኢትዮጵያ ያላት ፋይዳ ከዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ባለፈ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ላይ የተመሰረተ ጥልቅ ትስስር ነው።
ሪያድ ለኢትዮጵያ ዋነኛ የሰው ኃይል መዳረሻ ከመሆኗም ባለፈ፣ ከስደት ተመላሾች የሚላከው የውጭ ምንዛሬ (Remittance) ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። በተጨማሪም የሳዑዲ ገበያ ለኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ቀዳሚ መዳረሻ በመሆኑና እንደ ሸህ አላሙዲን ያሉ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ሚና፣ ሳዑዲን በኢትዮጵያ የውስጥ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም (Leverage) እንድትጨብጥ አድርጓታል። በመሆኑም ይህን መሰል ግንኙነት እንደ “መሳሪያ” (Weaponized) የመጠቀም አቅም ስላላት፣ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ጋር የምታደርገው ማንኛውም ግንኙነት እጅግ በሰከነና በጥንቃቄ የታጀበ መሆን እንደሚገባው የሚመክሩ አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት አሜሪካና እስራኤል በቀይ ባህር ላይ ያላቸውን ልዩ ፍላጎት ተክትሎ ሳዑዲ አረቢያ ማፈንገጥ ስለማትችል ኢትዮጵያና ኤርትራን የማሸማገል ኃላፊነት እንደወሰደች የሚጠቁሙ “ኢትዮጵያ ተጣቃሚ የምትሆንበት አግባብ አለ” እያሉ ነው። አዲስ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እየተደረጉ ያሉት ተከታታይ ውይይቶች ውጤት አጓጊ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉብኝት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት አካል ተደርጎ ይወሰዳል። በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ እየታዩ ያሉ የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል መግባባት ላይ መደረሱ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከንግድ አጋርነት ወደ ስትራቴጂካዊ የደኅንነት አጋርነት ከፍ ያደርገዋል። ይህ ስምምነት በተለይ በቀይ ባሕር ቀጣና ላይ የሚታየውን አለመረጋጋት ለመቅረፍና የሁለቱን ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
ስምምነቱ በቀጠናው ጂኦፓለቲካ ያለው አንድምታ
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚታየው የጎራ መለየት ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በአንድ በኩል ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ እና ቱርክ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE)፣ እስራኤል እና ሶማሊላንድ የየራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ የኃያላን ሀገራት የፉክክር መድረክ ውስጥ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስፍራ ላይ ትገኛለች። እያንዳንዱ ጎራ ኢትዮጵያን ወደራሱ ጎራ ለመሳብ የተለያዩ “ማባበያዎችን” (Carrots) የሚያቀርቡ ሲሆን፣ አንዳንዴም ፍላጎታቸውን በግዴታ ለመጫን የሚሞክሩበት ሁኔታ ይስተዋላል።
ሳዑዲ አረቢያ ከግብፅ ጋር ያላት ጥብቅ ግንኙነት ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስጋት ሊሆን ቢችልም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከኤምሬትስ ጋር ያላት የክልላዊ የበላይነት ፉክክር ለኢትዮጵያ አዲስ በር ሊከፍት ይችላል። ሪያድ ኢትዮጵያን በጸጥታው ዘርፍ እንደ ወሳኝ አጋር መመልከቷ፣ ግብፅ በሱዳንና በዓባይ ጉዳይ ላይ የምታደርገውን ጫና ለመመከት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የመደራደሪያ አቅም ይሰጣታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ የጥቅም መጋጨት ውስጥ የትኛውንም ወገን ሳታስቀይም፣ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ “ሚዛናዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ” መከተል እንደሚኖርባት የሚጠቁሙ አጋጣሚው ለኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ እየገለጹ ነው።
የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት የሚያሳየው፣ ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ በቀጠናው ስኬታማ መሆን እንደማትችል መገንዘቧን ነው። ኢትዮጵያም ይህንን ፍላጎት ተጠቅማ በኢኮኖሚ፣ በጸጥታና በዜጎች መብት ጥበቃ ዙሪያ ጠንካራ ስምምነቶችን ለመቅረጽ ትልቅ ዕድል አግኝታለች። የሳዑዲንና የኤምሬትስን ፍላጎት በብልሃት ማጣጣም፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም በላይ፣ ሊሰነዘሩ የሚችሉ የውክልና ጦርነቶችንና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ይረዳታል።
ለኢትዮጲያ ብሄራዊ ጥቅም ያለው ፋይዳ
በዶ/ር ጌዲዮን እና በዋሊድ አልኬሬጂ መካከል የተደረገው ውይይት በዋናነት “በጋራ የጸጥታ ግንባር” ላይ ያተኮረ መሆኑ፣ የቀጣናውን የኃይል ሚዛን የሚቀይር ነው። ሳዑዲ አረቢያ በቀይ ባሕር ላይ ያላትን የበላይነት ለማስጠበቅ በየብስ ላይ ጠንካራ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅም ካላት ኢትዮጵያ ጋር መስማማቷ ግድ ይላታል። ይህ ትብብር በተለይም እንደ ሽብርተኝነት፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የባህር ላይ ስጋቶችን ለመከላከል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። ኢትዮጵያም በምላሹ ከሳዑዲ የምታገኘውን የደኅንነት መረጃና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለውስጣዊ ሰላሟ ልትጠቀምበት ትችላለች።
ይሁን እንጂ ይህ ግንኙነት በ”ገቢር ነበብ” (Realpolitik) መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ሳዑዲ አረቢያ ሃይማኖታዊ ስፍራዎችን የምታስተዳድር ሀገር በመሆኗ ያላት መንፈሳዊ ተፅዕኖ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር ተዳምሮ ትልቅ የፖለቲካ ካፒታል ይሰጣታል። ይህ ካፒታል ለበጎ ግንኙነት መሠረት ሊሆን እንደሚችለው ሁሉ፣ በብልሃት ካልተያዘ ግን ለውጭ ጣልቃ ገብነት በር ሊከፍት ይችላል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የሳዑዲን “ለስላሳ ኃይል” (Soft Power) ከሀገሪቱ ሉዓላዊነት ጋር እንዳይጋጭ በጥንቃቄ መምራት እንደሚጠበቅባቸው የቀጠናው የጂኦፓለቲካ ተንታኞች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያና የሳዑዲ አረቢያ አዲሱ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በቀጠናው ሰላም ለማምጣት ትልቅ አቅም አለው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከግብፅና ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ውጥረት ለማርገብ የሳዑዲን የዲፕሎማሲያዊ ድልድይነት ልትጠቀምበት ትችላለች። ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር በታላላቅ ሀገራት ፉክክር መካከል በብልሃት የመደራደር አቅሟን ያሳየችበት ሲሆን፣ በቀጣይም ይህን የጋራ ግንባር ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚና የወታደራዊ ትብብር መቀየር የቤት ስራዋ ይሆናል።
አንዳንድ የአገር ውስጥ የፖለቲካ አካሄድ የሚከታተሉ እንደሚሉት፣ የሱዳን ፈጣን ኃይሎች በሳዑዲና ግብጽ የሚደገፈውን የጄኔራል አልቡርሃን ኃይል ላይ ተከታታይ ድል መጎናጸፋቸው፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የአልቡርሃን ኃይሎች አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ የፈጠረው ጭንቀት ሳዑዲን አሳስቧል። ኢትዮጵያ ይህን አጋጣሚ እንደ መልካም አጋጣሚ ይዞ ሊመጣ ይችላል።
የሱዳን ፈጣን ኃይሎች ድል በግብጽ የምትመራውን ኤርትራን ከማሳሰቡ ጋር ተያይዞ፣ በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆነችው ሳዑዲ ይህንን አጀንዳ ጠርጴዛ ላይ እንደምታስቀምጥ ግምታቸውን የሚሰጡ፣ በሱዳን የሚቋቋም ሰላማዊ መንግስት እንዲኖር ኢትዮጵያ ትልቁን ሚና ስለምትጫወት፣ እዚሁ ጠረጴዛ ላይ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን በማስቀመጥ አጋጣሚውን ልትጠቀም እንደምትችል የሚገልጹት እነዚሁ ወገኖች፣ አንዳንድ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የሱዳን ፈጣን ኃይሎች ድል ከጄኔራል አልቡርሃን በላይ ያስቆጣቸው ከዚሁ አጀንዳ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም በማስላታቸው እንደሆነ ያመለክታሉ። እነዚህ ወገኖች “ሻዕቢያን ማመን ቀብሮ ነው” በሚል ባልፈው ሳምንት ከትህነግ ደጋፊዎች ዘንዳ የተሰማውን አዲስ መረጃ ከዚህ ዜናም ጋር ያገናኙታል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






