የትርክት ጦርነት፤ ብሔራዊ ጥቅም ከሃይማኖታዊና ርዕዮተ – ዓለማዊ ወገንተኝነት በላይ የሆነ የሀገር ህልውና መሰረት!

Date:

ግብፅ በውስጥ ፖለቲካዋ የሙስሊም ወንድማማቾችን (Muslim Brotherhood) በሽብርተኝነት ፈርጃ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው የነበሩትን መሐመድ ሙርሲንና አባላቶቻቸውን እስከ መግደልና ማሰር የደረሰ እርምጃ የወሰደችው የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነትና የሉዓላዊነት ስጋት በማስቀደሟ ነው። ይህ እርምጃ በሃይማኖታዊ መነጽር ለሚመለከቱት አስደንጋጭ ቢሆንም፣ ለግብፅ መንግስት ግን የውስጥ ሰላምን የማስከበርና የህልውና ጉዳይ ነበር። ….. በተመሳሳይ፣ በጋዛና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ግብፅ የጋዛ ተፈናቃዮችን ወደ ግዛቷ ለማስገባት ፍቃደኛ አለመሆኗ ሌላው የብሔራዊ ጥቅም ማሳያ ነው። ምንም እንኳን የጋዛ ሕዝብና ግብፅ በሃይማኖትና በቋንቋ ቢገናኙም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን መቀበል ሊያስከትል የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና፣ የደህንነት ስጋትና የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍራት ካይሮ ድንበሯን ዘግታለች። ይህም “ሃይማኖታዊ ወንድማማችነት” ከድንበር ደህንነትና ከብሔራዊ ጥቅም በታች መሆኑን ያረጋገጠ ክስተት ነው።


አለባቸው ጉብሳ- ነፃ አስተያየት

ሰሞኑን አንዳንድ ሙስሊም ወንድሞቻችን የእስራኤ ፕሬዝዳንት ወደ የኢትዮጵያ መጥተው ገብኝት ከማድረጋቸው በፊት፣ በጉብኝቱ ወቅትና ከጉብኝቱ በኋላ እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ስለሆነ ልትወገዝ ይገባል በማለት የታቀደና የተቀናጀ የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻ ሲያካሂዱ ነበር። እስራኤል ሃገር ተጋብዘው ጉብኝት ያደረጉ ጋዜጠኞች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ዘመቻ በማድረግ አውግዘዋቸዋል።

ትኩረቴን የሳበው ግን <<እንደ ግብር ከፋይ ዜጋ የሃገራችን የውጭ ጉዳይ ግንኙነት በሰብአዊነት ላይ ወንጀል ከሚፈፅሙ ሃገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት የተገደበ እንዲሆን የመጠየቅና ግፊት የማድረግ መብት አለን>> በማለት በመንግስት ላይም ተፅዕኖ ለማሳደር ያደረጉት እንቅስቃሴ ነው። በስላማዊ መንገድ በመቃወም ሃሳብን መግለፅ የሚበረታታ ጉዳይ ነው። ይህ ሰብአዊነትና የሙስሊም ወንድማማች ላይ መሰረት ያደረገ ትብብር መርህ ላይ ሲመሰረትና በእኩል ደረጃ በሌሎች ላይም ግፍ ሲፈፀም ሃይማኖት፣ ዘር እና አመለካከትን ሳይለዩ መቆ ይደገፋል።

ይህ ማለት ግን ሃገር ግዴታ ከሌላ ሃገር ጋር የምታደርገው ግንኙነት በዘር ፍጅት ውግዘት፣ በሰብአዊ መብት፣ በፓለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ በሃይማኖት ወንድማማችነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን አትገደድም። ይህን በየትኛውም የእምነት፣ ርዕዮትና አመለካከት ጎራ ያለ ሰው ማወቅ ይገባዋል።

ይህን ጉዳይ አንዲት ሃገር በዚህ ውስብስና ተገማች ባልሆነ የዓለምና የቀጠና ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ብሄራዊ ጥቅሟን በማስከበር ሕልውናዋን ለማስቀጠል ልትከተለው ስለሚገባ ገቢር ነበብ የውጭ ጉዳይ ስትራቴጂ (Realpolitik) አንፃር ንድፈ ሃሳቡንና ተግባሩን ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ አንፃር እንደሚከተለው እናያለን።

ገቢር ነበብ የወጭ ጉዳይ ፓለቲካ

የገቢር ነበብ የወጭ ጉዳይ ግንኙነት ፓለቲካ ጽንሰ-ሃሳብ መሠረት የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ግንኙነት በሥነ-ምግባር፣ በሃይማኖታዊ እሴቶች ወይም በሕግ የበላይነት ላይ ሳይሆን በተጨባጭ ኃይል እና በሀገራዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው። ይህ አስተሳሰብ መንግስታት ውሳኔ በሚያሳልፉበት ወቅት “ምን መሆን አለበት?” ከሚለው የሞራል ጥያቄ ይልቅ “ምን ቢደረግ የሀገሬን ህልውና ያስቀጥላል?” ለሚለው ተግባራዊ ጥያቄ ቅድሚያ እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል። በዚህ ረገድ የሀገር ደህንነት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ከማንኛውም ሰብአዊ ወይም ርዕዮተ-ዓለማዊ ግዴታዎች በላይ ሚዛን ይደፋሉ።

የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛው መርህ “ተለዋዋጭነት” (Flexibility) ነው። በገቢር ነበብ ፓለቲካ ውስጥ ዘላቂ ወዳጅ ወይም ዘላቂ ጠላት የለም፤ ያለው ዘላቂ ጥቅም ብቻ ነው። ለምሳሌ፣ አንዲት ሀገር ዛሬ በሰብአዊ መብት ጥሰት የምታወግዛትን ሀገር ነገ ለስትራቴጂካዊ ጥቅሟ ስትል የቅርብ ወዳጅ ልታደርጋት ትችላለች። ይህ የሚሆነው መንግስታት በዓለም አቀፍ መድረክ የሚገጥሟቸውን ስጋቶች ለመቀነስ እና ዕድሎችን ለመጠቀም ሲሉ የግድ የሞራል መርሆዎቻቸውን ወደ ጎን ማለፍ ስለሚኖርባቸው ነው።

ለዚህ መርህ ትልቁ ታሪካዊ ማሳያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የታየው የኃይል አሰላለፍ ለውጥ ነው። በጦርነቱ ወቅት ናዚ ጀርመንን ለማሸነፍ ሲሉ እጅግ ተቃራኒ ርዕዮተ-ዓለም የነበራቸው ካፒታሊስቷ አሜሪካ እና ሶሻሊስቷ ሶቪየት ህብረት “የጋራ ጠላት” ስላላቸው ብቻ ጥብቅ ወዳጅነት መስርተው ነበር። ሆኖም ጦርነቱ እንዳበቃና የጋራ ጠላታቸው እንደጠፋ፣ ሁለቱ ሀገራት ወዲያውኑ ወደ “ቀዝቃዛው ጦርነት” በመግባት የዓለም ቁንጮ ለመሆን ተፋጠዋል። ይህ የሚያሳየው ወዳጅነታቸው በጋራ ፍቅር ሳይሆን በወቅታዊ የጋራ ስጋትና ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንደነበር ነው።

በሌላ በኩል፣ አሜሪካና ጃፓን የነበራቸውን ታሪካዊ ጠላትነት መመልከት ይቻላል። አሜሪካ በጃፓን ላይ ሁለት የአቶሚክ ቦምቦችን ጥላ የሰዎችን ሕይወትና የሀገርን ኢኮኖሚ ካወደመች በኋላ፣ ዛሬ ሁለቱ ሀገራት በዓለም ላይ ካሉ የቅርብ ስልታዊና ወታደራዊ አጋሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ጃፓን ከደረሰባት ጥፋት ይልቅ የሀገሪቱን የነገ ደህንነትና የኢኮኖሚ ትንሳኤ (ብሔራዊ ጥቅም) ስላስቀደመች ከቀድሞ ጠላቷ ጋር ወዳጅነት መርጣለች። እነዚህ ታሪካዊ እውነታዎች የሚያረጋግጡት፣ በዓለም መድረክ ላይ ሀገራት የሚመሩት በልብ ትርታ ሳይሆን በብልህ የታክቲክ ስሌት መሆኑን ነው።

በኛ ሃገርም እንዲሁ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የነበረው ያ ትውልድ፣ “ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ኅብረት” (Proletarian Internationalism Unite!) በሚል መፈክር በማርክሲስት ሌሊኒንስት ርዕዬተ ዓለም በመስከር የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በአንድ ወገን (ወደ ሶቪየት ሕብረት) ብቻ እንዲያዘነብል አድርጓል። በዚህም ሳቢያ “ያንኪ ጎ ሆም” (Yankee Go Home) በሚሉ መፈክሮች፣ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር መሰረት የነበሩ የምዕራባውያን ባለሀብቶችና ተቋማት እንዲባረሩ ተደርገዋል። ይህም የውጭ ኢንቨስትመንትን ከማጥፋቱም በላይ፣ የሀገሪቱን የንግድና የዲፕሎማሲ ሚዛን አዛብቶታል። ሀገራዊ ጥቅም በስሜታዊነትና ባልተጨበጠ “ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት” ሲተካ፣ ውጤቱ ድህነትና የኢኮኖሚ ውድቀት መሆኑን ኢትዮጵያ በአካል ያየችው እውነት ነው።

በተቃራኒው እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ከርዕዮተ-ዓለም ስካር ቀድመው በመንቃት ምንም እንኳን በማኦ መራሹ ኮሙኒስት ፓርቲ የምትተዳደር ብትሆንም፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ “ድመቷ ጥቁር ሆነች ነጭ አይጥ እስካጠመደች ድረስ ግድ የለኝም” በሚለው የዴንግ ዚያኦፒንግ መርህ፣ ርዕዮተ-ዓለማቸውን ወደ ጎን አድርገው ለብሔራዊ ጥቅማቸው ሲሉ ከምዕራባውያን (ካፒታሊስቶች) ጋር አብረው መስራት ጀምረዋል። ዛሬ ቻይና የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ የሆነችው ርዕዮተ-ዓለሟን ከብሔራዊ ጥቅሟ በታች ስላስገዛች ነው። ቬትናምም ከአሜሪካ ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ብታካሂድም፣ ዛሬ ጥቅሟን በማስቀደም ከአሜሪካ ጋር የቅርብ የንግድና የደህንነት አጋር ሆናለች።

ይህ የብሔራዊ ጥቅም የበላይነት መርህ በዘመናዊው የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥም በጉልህ ይታያል።ግብፅ በውስጥ ፖለቲካዋ የሙስሊም ወንድማማቾችን (Muslim Brotherhood) በሽብርተኝነት ፈርጃ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው የነበሩትን መሐመድ ሙርሲንና አባላቶቻቸውን እስከ መግደልና ማሰር የደረሰ እርምጃ የወሰደችው የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነትና የሉዓላዊነት ስጋት በማስቀደሟ ነው። ይህ እርምጃ በሃይማኖታዊ መነጽር ለሚመለከቱት አስደንጋጭ ቢሆንም፣ ለግብፅ መንግስት ግን የውስጥ ሰላምን የማስከበርና የህልውና ጉዳይ ነበር።

በተመሳሳይ፣ በጋዛና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ግብፅ የጋዛ ተፈናቃዮችን ወደ ግዛቷ ለማስገባት ፍቃደኛ አለመሆኗ ሌላው የብሔራዊ ጥቅም ማሳያ ነው። ምንም እንኳን የጋዛ ሕዝብና ግብፅ በሃይማኖትና በቋንቋ ቢገናኙም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን መቀበል ሊያስከትል የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና፣ የደህንነት ስጋትና የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍራት ካይሮ ድንበሯን ዘግታለች። ይህም “ሃይማኖታዊ ወንድማማችነት” ከድንበር ደህንነትና ከብሔራዊ ጥቅም በታች መሆኑን ያረጋገጠ ክስተት ነው።

ኤርዶጋን መራሹ የቱርክ መንግስት ደግሞ የሙስሊም ወንድማማችነት የፖለቲካ ፍልስፍና ዋነኛ አራማጅና ደጋፊ ሆኖ ለዓመታት ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ቱርክ ለጋዛ ሕዝብና ለሃማስ የምታደርገው ድጋፍ ከሰብአዊነት ባለፈ የርዕዮተ-ዓለም መሰረት ያለው ነበር። ሆኖም፣ ይህ ርዕዮተ-ዓለማዊ አቋም ከሀገሪቱ ሰፊ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም ጋር ሲጋጭ ቱርክም ብልህ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምራለች።

ቱርክ ግብፅ በመሐመድ ሙርሲና በፓርቲው አባላት ላይ የወሰደችውን እርምጃ በመቃወም ለ13 ዓመታት የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና የወታደራዊ ግንኙነቷን አቋርጣ በጠላትነት ቆይታለች። ግብፅ ለጋዛ ተፈናቃዮች መጠለያ አልሰጠችም በሚልም የቱርክ ጥላቻ አይሎ ነበር። ይሁን እንጂ፣ አሁን ሁለቱ ሀገራት ከሃይማኖት ርዕዮተ-ዓለም የሚመነጭ ልዩነታቸውን ወደ ጎን አድርገው፣ በምስራቅ ሜዲትራኒያን ካለው የነዳጅ ሀብትና የጋራ የደህንነት ፍላጎት አንጻር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።

ይህ የጥቅም ስሌት እንደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሞሮኮና ሱዳን ባሉ ሀገራትም ታይቷል። እነዚህ ሀገራት “የአብርሃም ስምምነትን” በመፈረም ከእስራኤል ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት የፈጠሩት፣ ከሃማስና ከጋዛ ሕዝብ ስቃይ ይልቅ ለሀገራቸው የሚገኘው የቴክኖሎጂና የደህንነት ጥቅም ስለሚበልጥባቸው ነው። ሶማሊላንድም ብትሆን የራሷን የነፃነት እውቅናና የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ ስትል፣ ከማንኛውም አካል ጋር ስትራቴጂካዊ ስምምነቶችን ለማድረግ ወደኋላ አትልም።

ብሔራዊ ጥቅም ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እየተባበርክ የሀገርን ህልውና ማስቀጠልን ያካትታል። ቱርክ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮና ኤምሬትስ እያደረጉ ያሉት በትክክል ይህንኑ ነው። የአንድ ሀገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችና የሃይማኖት ቀኖናዎች ለድርድር ይቀርባሉ። በጠረጴዛ ዙሪያ ዋጋ የሚሰጠው የሀገርን ህልውና ማስቀጠል እንጂ፣ በመርህና በስሜት ተገዝቶ በድህነትና በብቸኝነት መቆየት አይደለም።

“እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣ አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል” የሚለው የአባቶች አባባል የግቢር ነበብ ፓለቲካ ሕያው አስረጅ ነው። ሀገር ከሌለች ሃይማኖትን በነፃነት ለማምለክም ሆነ የፖለቲካ ፍልስፍናን ለማራመድ አይችልም። ስለዚህ፣ ማንኛውም ዜጋ የሀገሩ ህልውና እንዲቀጥል ሲባል መንግስታት የሚፈጥሯቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችና ስትራቴጂካዊ አጋርነቶች ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም በላይ መሆናቸውን መረዳት ይገባዋል።

ያለንበት ዘመን እጅግ ውስብስብ፣ ተገማች ያልሆነና ተለዋዋጭ ነው። በዚህ መድረክ ላይ ስሜታዊ መሆንና በሃይማኖታዊ መነጽር ብቻ ዓለምን መመልከት ሀገርን ለከፋ አደጋ ያጋልጣል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የግል እምነትህንና የፖለቲካ ፍልስፍናህን እያራመድክ እየመሰለህ፣ ሀገርህን ወደ ገደል አፋፍ እንዳትገፋ መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው።
ይህ መሰረታዊ ሀሳብ ክርስቲያኑን፣ ሙስሊሙን፣ ዋቄ ፈናንና የየትኛውንም እምነት ተከታይ እኩል ይመለከታል። የሀገርን ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶች ከሃይማኖትና ከፓርቲ ፖለቲካ በላይ መታየት አለባቸው። አንድ መንግስት ከሌላ ሀገር ጋር ስምምነት ሲያደርግ፣ ስምምነቱ ለሀገር የሚያመጣውን የኢኮኖሚና የደህንነት ትርፍ እንጂ፣ የአጋር ሀገሪቱን ርዕዮተ-ዓለም አያሳይም።

በተለይ በሉላዊነት ዘመን፣ በሃይማኖት ወንድማማችነት ሰበብ የሌላ ሀገርን አጀንዳ በሀገር ውስጥ ማስፈጸም፣ ወይም በፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ምክንያት የሀገርን ስትራቴጂካዊ ጥቅም አሳልፎ መስጠት ከታሪካዊ ተጠያቂነት አያድንም። አገራት በጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀመጡ የሚያሰሉት ” ለሃገሬና ለሕዝቤ ምን ጥቅም ያስገኛል?” የሚለውን እንጂ “ወዳጅ ሃገሬ የትኛውን ሃይማኖት ወይም ርዕዬተ አለም ይከተላል?” የሚለውን ስላልሆነ በሌላ ሃገር አጀንዳ ተጠልፈን ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን እንዳንሰጥ መጠንቀቅ አለብን።

የሀገር ህልውና—የሁሉም እሴቶች መከታ

በአጠቃላይ ከዚህ ተጨባጭ የገቢር ነበብ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ታሪክ የምንረዳው እውነት ቢኖር፣ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም የአንድ ሰሞን የሃይማኖት፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የቋንቋና ባህል ስሜት ወይም የግል ምርጫ ሳይሆን፣ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ የህልውና ዋስትና መሆኑን ነው። ሃይማኖቶች ሊኖሩ፣ ርዕዮተ-ዓለሞች ሊያብቡና የፖለቲካ ፍልስፍናዎች ሊራመዱ የሚችሉት እነዚህን ሁሉ እሴቶች ተሸክማ የምትቆም “ሀገር” የተባለች ጽኑ መሰረት ስትኖር ብቻ ነው። ታሪክ ደጋግሞ እንዳሳየን፣ በስሜትና በወገንተኝነት የታወረ ዲፕሎማሲ ሀገርን ለውጭ ጣልቃ ገብነትና ለውስጥ መፈራረስ አሳልፎ ይሰጣል። በአንጻሩ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ንቁና ብልህ አካሄድ፣ ዛሬ ካለንበት ውስብስብ የዓለም ፖለቲካ ማዕበል ውስጥ ሀገራችንን በሰላም አሻግሮ ለነገው ትውልድ ኩሩና ሉዓላዊት ሀገርን ያስረክባል። ስለዚህ፣ ከምንም ነገር በላይ ለሀገር ህልውና ቅድሚያ መስጠት የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን አስተዋይነት ነው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የዓለም የነዳጅ ቀውስ እና የኢትዮጵያ ፈተና [ታሪካዊ አርበኝነት ጥሪ] ወቅቱን ለሚመረምሩ ሁሉ

ኢትዮጵያን እንወዳለን፣ ኢትዮጵያ አገሬ ናት፣ ኢትዮጵያ እናቴ ናት፣ ሌላ...

ወሳኙ የአደዋ ድል ሚስጢር – የአፄ ምኒልክ አዋጅ

ይህ ማህበራዊ ውል መላውን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር አስተሳስሯል።...

“አዲሷ” ኢህአፓ፤ ከንፈሯን ቀለም የተቀባች አሳማ – ኢህአፓ አሳማነቷን በሊፒስቲክ ልትደብቅ?

በ1980ዎቹ ነበር፤ በዘመኑ ቀልድ የሚያበዛ ታዋቂ ጋዜጠኛ በአንድ የታወቀ...

ጃዋር መሐመድ የአመጽ ጥሪውን የሰረዘው ለአስቸኳይ ስራ ግብጽ ተልኮ መሆኑ ታወቀ

አዲስ ሪፖርተር - ባለፈው ማክሰኞ በኢትዮጵያ ሕዝብ አመጽ እንዲያቀጣጥል...