በ1980ዎቹ ነበር፤ በዘመኑ ቀልድ የሚያበዛ ታዋቂ ጋዜጠኛ በአንድ የታወቀ ሪዞርት ሽንት ቤት ውስጥ አሳማ ያስቀምጣል። አሳማዋንም የከንፈር ቀለም (ሊፕስቲክ) ቀብቶ እንደ ሰው አስመስሎ። ዓላማው ሌላ ሳይሆን ፕራንክ ነበር። ክስተቱ የሪዞርቱን ባለቤት ፕራንክ አድርጎ ቢያልፍም ከዚያ በኋላ ግን አሳማ የከንፈር ቀለም ቢቀባ እንደ አሳማ መጮኹ (ኦይንክ ማድረጉ)፣ ጭቃ ላይ መንከባለሉ፣ አሰሱንም ገሰሱንም መብላቱ፣ … ባጠቃላይ አሳማነቱ አይቀርም ማለት ነው በሚል አባባል ተተካ።
ከዚያም በ90ዎቹ ለቴክሳስ ሀገረግዢነት ይወዳደሩ የነበሩት አን ሪቻርድስ አባባሉን ተጠቀሙበት። ትልቁ ቡሽ በምርጫ ውድድር በነበሩበት ጊዜ የቡሽ አስተዳደር ለውጥ እንደማያመጣ አን ሲናገሩ “ዌል የአሳማዋን ከንፈር ሊፕስቲክ ቀብቶ ሞኒካ ነሽ ሊሏት ይቻላሉ፤ ግን አሳማነቷ ፈጽሞ አይቀየርም” ነበር ያሉት።
በሀገራችን ፖለቲካ ከንፈሯን ቀለም ተቀብታ የመጣች ፓርቲ ኢህአፓ ነች። የሚገርመው ደግሞ አለማፈሯ፤ እና አሳማ አይደለሁም ብላ ለማሳመን መላላጧ።
የተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚባለው እየተጋጋለ ሲሄድ ያንን ደሙ የተቆጣ ወጣት ጠልፋ ኢህአፓ የምትባል ፓርቲ ተመሠረተች። ማንነቷ አሁን ሊያሰማምሯት እንደሚፈልጉት ሳይሆን ለማስመሰልና ለማደናገር “ኢትዮጵያ” የሚል ስም የያዘች ግን ጸረ ኢትዮጵያ፣ ሀገር ከፋፋይና እና ተገንጣይ ፓርቲ ነበረች። ይህንን አባላቷ ብቻ ሳይሆኑ ሊቀ ተገንጧዮቹ ሻዕቢያና ትህነግም የሚመሰክሩት ነው።
በሶማሊያ ጦርነት ከወራሪው የሶማሊያ ጦር ጋር በማበር ስንቅና ትጥቅ ውስጥ የተፈጨ ጠርሙስና አሸዋ በመጨመር ኢህአፓ ጸረ ኢትዮጵያዊ ዓላማዋን ለማሳካት ሞክራለች። ስታዲየም ሶማሊያን የተቃወመ ትዕይንት ሲካሄድ ሶማሊያን ደግፋ ጩኸቷን አሰምታለች። ከሰሜን ተገንጣዮች ጋር እጅና ጓንት ሆና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተግታ ሠርታለች፤ ይህ ፈጠራ ሳይሆን የቀድሞ አባሎቿ የሚናገሩት ሐቅ ነው፤ ስፍር ቁጥር ከሌለው የኢህአፓ የክህደት ማንነት በጣም ጥቂቱ።
“የራስን ዕድል በራስ እስከ መገንጠል” የሚል መርዝ ኢትዮጵያ ውስጥ በመትከል የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው አሳማዋ ኢህአፓ ነች። ግን ስሟ ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚል ስለጨመረች ብቻ ኢትዮጵያዊነት አንግቤአለሁ በማለት ከንፈሯን ቀለም ስትቀባ የኖረችው ከቀድሞ እንደሆነ ያስመሰከረች ፓርቲ ነች።
የሻዕቢያው አንበል ኢሳያስ አፈወርቅ ለኢትዮጵያ ያዘነ ይመስል “የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አይመጥንም” ሲል ሁልጊዜ ይሰማል። ትህነግንም ሲያራክስ “የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ላይ ሲያመጡ ልክ አይደለም ብዬ ረቂቅ ሕገመንግሥቱን ተቃውሜአለሁ” ይላል። ነግርግን ሸኔ፣ ፋኖ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ትህነግ፣ … ማንኛውንም ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል የሚሠራ ስሙ በ“ግ” የሚያልቅ ድርጅት ያስታጥቃል፣ ያደራጃል፣ ገዢ መሬት ይሰጣል፤ ወዘተ። አሳማዋ ኢህአፓ ውስጥ ያለው “ኢትዮጵያ” የሚለው ስምም እንዲሁ ነው።
ኢህአፓ ሲበዛ ጨካኝ ናት። የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ሳይቀር ምንም በማያውቁት የሚበተን ወረቀት ቦርሳቸው ውስጥ እያስደረገች በደርግ ታጣቂ በግፍ እንዲገደሉና ያንን ደግሞ ለፖለቲካ ዓላማ የተጠቀመች ስሜት ዓልባ፣ ርኅራኄ ዓልባ ፓርቲ ነች። እነ ጃዋርም እንዲሁ ነበር ያደረጉት፤ አሁንም እንዲሁ ለማድረግ ነው የተለያዩ አሳማዎች ዙሪያ የሚታዩት።
ኢህአፓ የወሰደችው የጭካኔ መንገድ ይህ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ጠብመንጃ አፈሙዝ ላይ ብቻ እንዳለ ዕድሜ ልኩን ሲሰለጥን ከኖረ የወታደር ስብስብ፣ ደርግ ጋር፣ የከተማው ውስጥ ሽብር፣ ነጭ ሽብር በማለት ግድያ የጀመረች ደም አፍሳሽ አሳማ ነች። ከዚያ ደግሞ ደርግ ቀይ ሽብር ፈጸመብኝ ብላ ከቀድሞ የፍቅር ጓደኛዋ ትህነግ ጋር ተስማምታ የነጭ ሽብር ሰለባዎች የሚል ሙዚየም ያስከፈተች ዓይንአውጣ ድርጅት ነች። ተመስገን ማዴቦ የማርያም አራስ ሚስቱን ጋንዲ ሆስፒታል ጠይቆ ሲወጣ አስፋልት ላይ የደፋው ማነው? ነው ወይስ ለቲክቶክ ፖስት በውሃ ሽጉጥ ፕራንክ ነው ያደረጉትና ድራማው ሲያልቅ ተነስቶ ሄዷል?
በሰው በላዋ ኢህአፓ ነጭ ሽብር የተጨፈጨፉትን ማን ያስታውሳቸው? ማን ሙዚየም ይሥራላቸው? ማን ሃውልት ያቁምላቸው? ቤተሰቦቻቸው ጭምር እንዳይናገሩና እንዳይመሰክሩ በኃፍረት ተሸማቅቀው፣ በጥፋተኝነት ስሜት አንገታቸውን ደፍተው እየኖሩ ነው።
ከኢህአፓ ጋር መቃረን አይቻልም። ይቺ ባህርይዋ አሁንም ከንፈሯን ቀይ ቀለም ተቀብታ ወደ አደባባይ ብቅ ያለችው ኢህአፓ ላይም በስፋት ይታያል። ኢህአፓን መቃወም ዋጋ ይስከፍላል፤ ሒደት አለው፤ አንድ ሰው በሃሳብ ማፈንገጥ ወይም ለየት ማለት ሲጀምር አንጃ በሚል ይፈረጃል፤ ከዚያ ጠላት ተብሎ ዒላማ ውስጥ ይገባል፤ ቀጣዩ ግምባሩን ብሎ መድፋት ነው። እነ ብርሃነመስቀል እና እጅግ ብዙዎች ለምንና በማን እንደተገደሉ ሞት የረሳቸው ኢህአፓዎች በራሳቸው አንደበት አሁንም የሚመሰክሩት ነው።
ኮሚኒስቷ ኢህአፓ ጸረ ሃይማኖት ነች። ሞራል የሚባል ነገር ከውስጧ ተመጥጦ የወጣባት፤ የሰብዓዊነት ጠብታ የሌለባት፣ ጭከና ዋነኛ መሣሪያዋ የሆነ ድርጅት ናት። ሞራልና ሃይማኖትን ከወጣቱ አእምሮ ማጥፋታቸው በብዙ መልኩ ተገልጿል። ልጆች አዛውንት እናትና አባታቸውን፣ ዘመዶቻቸውን፣ አጎቶቻቸውን፣ ወዘተ ደርግ፣ ቡርዧ፣ ወዘተ እያስባሉ አሳልፈው ሰጥተዋል፤ ገድለዋል፤ አስገድለዋል። ይቺ ከጭከና ክምራቸው ቁልል አንዷ ሰበዝ ናት።
የሚገርመው ግን ቀይ ቀለም ተቀብተው የመጡት ያሁኖቹ አሳማዎች “ሃይማኖተኛ” መሆናቸው ነው። መሪው “መጋቢ ብሉይ” ተብለው ነው የሚጠሩት። ይህ የሃይማኖት ማዕረግ ነው። ብሉይ ኪዳንን የሚያስተምር አዋቂ፣ ምሑር ማለት ነው። ሰሞኑን “የዘመናችን ልደቱ” እየተባለች (ስያሜው ትንቢታዊ ይመስላል) የማኅበራዊ ሚዲያ ትኩሳት የሆነችው የምርጫ ክርክሩ ምሽት ባለማተብነቷን በገሃድ ማሳየት በጣም መፈለጓ ሌላ ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው። ሤራ ቀለቧ የሆነው ባለሊፕስቲኳ ኢህአፓ ምን አስባ ይሆን?

ከንፈሯን ቀይ ቀለም በደማቁ ተቀብታ፣ ዓይኗን በጨው አጥባ ኮሚኒስት ሳልሆን ሶሻል ዴሞክራት ነኝ ብላ ስለመጣችው አሳማዋ ኢህአፓ የዱሮም ሆነ ያሁኑ ማንነት ማውራት እጅግ ይደክማል። ደግነቱ በሊፕስቲክ አይደለም በእንዶድ ሆነ ዓለም ላይ ባለ ቆሻሻ ማስለቀቂያ ቢያጥቡት የማይጸዳው ታሪካቸው ይጮኻል። ስለዚህ ብዙ ማለት አያስፈልግም። ግን በአንድ ነገር ላብቃ …
የቀድሞዋ ዋና ጸሐፊ ደስታ ጥላሁን ለሦስት ጊዜ መልቀቂያ አቅርባ በሦስተኛው ወጥታለች። የለቀቀችበት ምክንያቶች በቀጥታም በተዘዋዋሪ መንገድ ያለችው፤ ድርጅቱ አዲስ ሃሳብ ለመቀበል ራሱን ያላበቃ፣ የተቸከለ፣ ውስጣዊ ዴሞክራሲ የሌለው፣ አሁንም በሤራ የሚንቀሳቀስ፣ መረጃ የሚያፍን፣ ወገንተኛ፣ የሚቃወሙትን በአንጃነት የሚያይ፣ ለዘመናዊ አስተሳሰብ ራሱን ያላበቃ፣ በቀድሞው መሪዎቹ የሚዘወር፣ ወዘተ ነው።
ባጭሩ ኢህአፓ ቦጌ ቀይ ቀለም ከንፈሯን ተቀብታ ብትመጣም አሁንም ያው አሳማ ነች ማለት ነው።
ከጾታ እስከ ሥልጣን ደስታ ጥላሁን የተተካችው በባለማተቧ ሚስጥረሥላሴ ነው።
መክብብ ማሞ ለጎልጉል
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






