“እንዴት ከወንጀለኞች ጋር ጎን ለጎን ሆነን ሕዝብ ፊት እንወጣለን? የኢህአፓ ዘመን አውጫጪኝ በአብሮነት ጓዳ አወዛገበን”
አዲስ ሪፖርተር – በየቀኑ ስለ ሰላምና ጦርነት አውዳሚነት የሚናገረው ጃዋር መሐመድ ግብጽ እንደነበር የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቃል አቀባይና የጃልመሮ አማካሪ አቶ ጅሬኛ አስታወቁ። አቶ ጅሬኛ ጉደታ ይህን ያሉት በአገር ቤት ህዝባዊ አመጽ ለማስነሳት በተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው። በስብሰባው መሳተፍ የጀመሩት አቶ ጃዋር “ይወክሉኛል” ብለው ነው።
“ጃዋር ስልክ አይመልስም፤ በተደጋጋሚ ስደውል አያናግረኝም፤ እሱን ተክተህ እዚህ እንድትገባ ያደረገው እሱ ነውና እባክህን ደውልና ለስራ እንደምንፈልገው ንገረው” በማለት አቶ ልደቱ ይጠይቃሉ። ጥያቄው የቀረበላቸው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ጃልመሮ አማካሪና ወኪል የሆኑት አቶ ጅሬኛ “ጃዋር ግብጽ ነው፤ ነገ ይመለሳል” በማለት ስልክ የማያነሳበትን ምክንያት አስረድተዋል።
አቶ ጅሬኛ ይህን ሲሉ፤ ተሰብሳቢዎች መደናገጣቸውን እማኞች ገልጸዋል። በዚህ ወር ብቻ ለሁተኛ ጊዜ ግብጽ የተመላለሰው ጃዋር በአርሲ አቅጣጫ ካለው እንቅስቃሴ ጋር ስሙ ሲነሳ ቆይቷል። ከጃልመሮ ጋር አብሮ እንደሚሰራ የሚገልጹ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስን በምክትል ሊቀመንበርነት ማዕረግ መመራቱ እንቆቅሎሽ የሆነባቸው በተደጋጋሚ ይህንን ጥርጣሬያቸውን ሲናገሩ ነበር፤
በትናንትናው ዕለት አቶ እንደተረጋገጠው አቶ ጃዋር አቶ ጅሬኛን በአመጽ አደራጅና አመቻች ቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ መተካታቸው፣ ከአቶ ጅሬኛ የሚታወቅ ኃላፊነት አንጻር አብረው እንደሚሰራ ማረጋገጫ እንደሆነላቸው በስብሰባው የተሳተፉ አመልክተዋል። አቶ ጂሬኛ ጃዋር ለስራ ግብጽ መሄዱን እንጂ ዝርዝር ጉዳይ አልተናገሩም።
ከሁለት ሳምንት በኋላ በበይነ መረብ በሚደረገው የበይነ መረብ የሰማይ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ፣ ሕዝብ ለምርጫ እንዳይወጣ፣ በአመጽ እንዲሳተፍ አስቀድሞ ለመቀስቀስ እንዲቻል ምደባና ውይይት ለማድረግ በተጠራው በቅዳሜው ስብሰባ ላይ ድንገት የደርግ ዘመን አጋልጥ ተጀመረ።
“ኢህአፓ የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግል አውጆ ወጣቱን ካስጨረሰ በኋላ ደርግ በየቀበሌው ባካሄደው ራስህን አጋልጥ ዘመቻ የሆነውን አስታወሰኝ” ያሉት የስብሰባው ተካፋይ “እንዴት ነው ከነዚህ ወንጀለኞች ጋር አብረን ተቀምጠን መግለጫ የምንሰጠው” በሚል ቅሬታ ተነሳ።
ከተሰብሳቢዎቹ ያገኘነው መረጃ እንደሚከተለው አቅርበናል። ለበይነ መረብ ሰልፍ ማስተባበርና ቅሰቀሳ እንዲመደቡ የተፈለገው ሃያ አምስት ሰዎች ነበሩ። ይህ ሳይሆን ቀረና አስራ አምስት ተመደቡ። እነሱም አቶ ልደቱ፣ አቶ ነዓምን፣ አቶ ታማኝ በየነ፣ አቶ አንዳርጋቸው፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ጃዋር፣ ኦባንግ፣ አቶ ጅሬኛ፣ ኢንጂነር ሙሉጌታ፣ ከአብሮነት የአመጽ ቡድን ራሳቸውን በደብዳቤ ያገለሉት አቶ ያሬድ ኃ/ማሪያም፣ ኢንጂነር ሙሉጌታ፣ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል፣ አቶ አባይ እና ዶክተር ኢስማኤል ጎርሴ ሲሆኑ ሁለትም ሶስትም እየሆኑ በሚመደቡበት ሚዲያ እየወጡ ሕዝብ እንዲያነሳሱ አቅጣጫ ተቀመጠ።
የትህነግ ወኪል የሆኑት አቶ አባይ እና አቶ ጂሬኛ በድንገት “እንዴት ከእነዚህ ጎን አብረን ተቀምጠን ሕዝብ ፊት መገለጫ እንሰጣለን፣ እንቀሰቅሳለን?” ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አቶ ነዓምንን፣ አቶ ታማኝ በየነን እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ስም በመጥራት “ወንጀለኞች” አሉዋቸው።
ይህን ጊዜ በየተራ ሁሉም ቁስሉን እያነሳ ክስ ጀመረ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አቶ ነዓምንን፣ አቶ ታማኝ በየነን እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን “ክሪሚናልስ ናቸው” ያሉት አቶ አባይ “የወታደር ልብስ ለብሰው፣ መሳሪያ ይዘው፣ ‘ይህን ህዝብ አጥፋ’ ሲሉ የነበሩ ወንጀለኞች ናቸው” አሉ። አቶ ጅሬኛም አስከትለው “ንጹሃንን ያስጨረሱ ወንጀለኞች ናቸው እንደውም እወጣለሁ” አሉና ቁጣቸውን አሰሙ።
አቶ ጅሬኛ በዚህ አላቆሙም፣ “ አቶ ነዓምንን በደንብ አላውቀውም፤ እስኪ ስለ እሱ ነገሩኝ” በማለት ጥያቄ አነሱ፣ የትህነጉ ተወካይ አቶ አባይ “ ነዓምን ከኤርትራ ጋር እንደሚሰራ እን አውቃለን። እነ አንከር፣ ኢኤምኤስ ዘውዱ ሾው፣ እና ሌሎች ሚዲያዎችን በማስተባበር ይሰራል” በማለት መልስ ሰጡ።
በጥቅል ለቀረበው ክስ አቶ ልደቱ “እነሱን መግፋት አንችልም” በማለት ወደፊት / መንግስት ስንሆን ማለታቸው ነው/ በአገራዊ የፍትህ አግባብና ምክክር ኮሚሽን የሚታይ ጉዳይ እዚህ አንስቶ መካሰስ አግባብ እንዳልሆነ፣ ለትግሉም ጥቅም እንደሌለው አስታውቀው ነገሩን ለማባረድ ሞከሩ።
ይህን ጊዜ አቶ ጂሬኛ “ለምን ይድበሰበሳል” በማለት ግልጽ መሆን ካልተቻለ ጥለው እንደሚወጡ በድጋሚ አስጠነቀቁ። ይህን ጊዜ አቶ ኦባንግ ተነሱና “እናንተ ምንም ያማያውቁ ነጹሃን አማሮችን ትገድሉ አይደለ” በማለት አቶ ጂሬኛ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቃል አቀባይ መሆናቸውን አስታወሷቸው።
አቶ ኦባንግ አክለውም “ከ400 በላይ የአኝዋክ ልጆችን ጭፍጭፋችኋል፤ አቶ ጃዋርም 85 ንጽሃንን አስጭ እርሷል” በማለት ሁሉም እጃቸው ላይ ደም እንዳለባቸው በማንሳት ወቀሱ።
ኢንጂነር ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ “እነዚህን ሰዎች ብናስቀራቸው ጥሩ ነው” በማለት ዝምታቸውን ሰበሩ። “ኢትዮጵያ ይበሉ እንጂ ተሰሚነት የላቸውም። ያደረጉት የሚታወቅ ነው ይውጡ” አሉ።
ሌላ ተሰብሳቢ “ጄል ኦጋዴን እናንሳና እኛም እንክሰስ?” አሉና አንዱ ሌላውን የመክሰስ አቅም እንደሌለው አስታወቁ። አቶ ልደቱ በቅንጅት ወቅት የፈጸሙትንና በሚችሉት ሁሉ ሊያተባብሉት ቢሞክሩም ሊፋቅ ያልቻለው የክህደት ታሪካቸውን በማንሳት ከሳሽና ተከሳሽ ሊኖር እንደማይችል ተናገሩ።
አቶ አባይ ቀበል አድርገው መጀመሪያ ለውጡን አፋፍሞ መንግስት ሲቀየር፣ ችግሩን በህግ አግባብ ማየት እንደሚቻል፣ አሁን ላይ ግን መካሰስ እንደማይገባ በመጥቀስ መነሻቸውን ቀየሩ። “እንዴት ከነዚህ ወንጀለኞች ጋር ጎን ለጎን ቁጭ ብለን ሕዝብ እንቀሰቅሳለን” ሲሉ በስብሰባው መግቢያ የተናገሩትን ቀየሩ።
አቶ ልደቱም እንዲህ መሰል ጉዳዮች በብሄራዊ ምክክር የሚፈቱ መሆናቸውን አጽንተው ተናገሩና ወደ ስብሰባው መነሻ አጀንዳ አመሩ። እዚህ ላይ አንድ ተሰብሳቢ “ግን እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ እነ ኢታና፣ እነ ሚሊኬሳ፣ ወዘተ ለምን እንዲገቡ አይደረገም” የሚል ድንገተኛ ጥያቄ ሰነዘሩ።
አቶ ልደቱ “ኖ ኖ ኖ” አሉ። ጠያቂው “የኦነግ ሰራዊት መጥቶ፣ ጠሃ ቢቀር፣ ኢታና ባይመጣ ምን ችግር አለው” አሉ። አቶ ልደቱ “እነዚህን ካመጣን ችግር ይፈጠራል” በማለት በደፈናው መለሱ።
በአውጫጪኝ ተጀምሮ የተጠናቀቀው ስብሰባ በመጨረሻ ተመዳድበው ሕዝብ ለአመጽ እንዲነሳ ለመቀስቀስ ስምምነት ላይ ደረሰዋል፣ በዚሁ መሰረት ታማኝ በየነ ከትህነግ ተወካይ ጋር ቁጭ ብሎ ህዝብን ለአመጽ ይጋብዛል። በሁለቱ ሳምንታት ውስጥ በጋራ ሁለትና ሶስት እየሆኑ ህዝብ ለአመጽ እንዲነሳ ቅስቀሳ ለማድረግ ሌሎችም ምድብ እንደሚደርሳቸው ተገልጾላቸው ተበትነዋል። እርስ በእርስ በገዳይነትና በአስገዳይነት፣ በበዳይነትና በዳይነት፣ በክህደትና በጨዋነት ተቧድነው የተካሰሱት የአምጽ አቀጣጣጣይ የቴክኒክ ቡድን ዛሬ እኩለ ለሊት ላይ፣ ከስምንት የተለያዩ ቡድኖችና ማህበራት ጋር አንድ ላይ ይመክራል።
በአገር ውስጥ ካላው የሕቡዕ ኃይልና አንዳንድ ምርጫ ውስጥ እየተወዳደሩ ካሉት አጋሮቻቸው ጋር እንዴት በቅንጅት እንደሚሰሩ የሚመከርበት የዛሬው ስብሰባ ሕዝብ ምርጫ እንዳይመርጥ፣ አመጽ እንዲያቀጣጥል ማድረግ ዋና አጀንዳው ነው።
ከተጋባዦቹ በተገኘው መረጃ መሰረት በዋሽንግቶንና በሎንዶን ሊደረግ የታሰበው የተቃውሞ ስልፍ ከሰለሞን ቦጋለ ወደ ኢትዮጵያ መላክና ፋኖ በሽብር ደረጃ ሶስት መመደብ ጋር ተያይዞ ስጋት አንዣቦበታል። የትህነግ ደጋፊዎች በርካታ የአማራ ተወላጆችን እየጠቆሙና እየከሰሱ መሆኑ፣ ክስና ጥቆማ እንዲደረግ ከሁለቱም ወገን በገሃድ በማህበራዊ ሚዲያ የሚታወቁ ፖለቲከኞች አቅጣጫ እየሰጡ መሆናቸው ልዩነቱን አስፍቶታል። ከዚህም በላይ ጥምረት ፈጥረዋል የሚባሉት የትህነግና የፋኖ አንድ ክፍል በወልቃይት ጉዳይ የያዙት አቋም በአማራው ማህበረሰብ እንደ ክህደት መቆጠሩና የትህነግ ሰዎች የያዙት የማያወላዳ አቋም ጥምረቱንና አብሮነቱን ገሎታል። በዚህ መነሻ አብሮ አንድ ላይ ለተቃውሞ መውጣት እንደማይቻል ግምቱ ሰፍቷል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






