የጃዋርና የታዬ የ50+1 “ጽምዶ”፤ የጃዋር የከሸፈው ኦፌኮን ለኦሮሞ ብልጽግና አሳልፎ የመስጠት ድራማ

Date:

አዲስ ሪፖርተር – ጃዋር የኦሮሞ ፊደራሊስት ኮንግረንስን፣ ኦፌኮን ለኦሮሞ ብልጽግና መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብና የፖለቲካ ፍላጎቱን ለማሳካት ተስማምቶ እንደነበር “መላው የፓርቲው ደጋፊ ይወቀው” ሲሉ ድርጅቱን የተለዩ በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር አስታወቁ። ከዚህ ዕቅድ መክሸፍ በፊት ጃዋር ከአቶ ታዬ ደንደአ ጋር አዲስ ፕሮጀክት መመስረቱንም እነዚህ አካላት አስታውቀዋል። የኦፌኮ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ በወሬ ደረጃ ጉዳዩን መስማታቸውን ተናግረዋል።

ከኦፌኮ ራሳቸውን ያሰናበቱና ስማቸው ለጊዜው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በፓርቲው ውስጡ ያሉ አባላቱ ለአዲስ ሪፖርተር እንዳሉት በ2014 በተደረገው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ጃዋር 50+1 ድምጽ በመያዝ ፓርቲውን ከተቆጣጠር በሁዋላ አፍርሶ ለኦሮሞ ብልጽግና ለማስረከብ ተስማምቶ እንደነበር ። ይሁን እንጂ ከስምምነቱ በሁዋላ ከኦሮሞ ብልጽግና በኩል ሆነ ተብሎ ሚስጢሩን ለኦፌኮ የሚታወቁ አመራሮች እንዲደርስ መደረጉንም ገልጸዋል።

በተጠቀሰው ዓመት በተደረገው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ጃዋር 50+1 ድምጽ በመያዝ በአብላጫ ድምጽ ፓርቲውን ከተቆጣጠረ በሁዋላ በዚሁ ስሌት ከኦሮሞ ብልጽግና ጋር ለመቀላቀል የያዘውን ዕቅድ የሰሙት የፓርቲው አመራሮች ወዲያውኑ ” የተለመደ” በተባለ የምርጫ ሂደት ሃሳቡን ማክሸፋቸውን ዜናውን የነገሩን አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ የካድሬዎች ምልመላና የህዝብ አደረጃጀት ውስጥ ሰፊ ስልጣን ከነበራቸው አቶ ታዬ ጋር ከፍተኛ ጽብ ውስጥ የነበረው ጃዋር፣ ከአቶ ታዬ ጋር ከዚያን ጊዜ ጀመሮ በዓላማና በስትራቴጂ ላይ ያተኮረ ግንኙነት መስርተው እንደነበር እነዚህ ክፍሎች አክለው ያስረዳሉ።

አቶ ጥሩነህ ገምታ በኦፌኮ ጉባኤ ወቅት ግርግር እንደነበር ይጠቅሳሉ ” ኦፌኮ እንዲህ ያሉ መሰናክሎችና ሴራዎችን የማለፍ ልምድ ስላለው አልፈነዋል” በማለት ወቅቱን ከማስታወስ በዘለለ ብዙም አስተያየት ለመስጠት አልወደዱም። ይሁን እንጂ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውንና እሳቸው “ግርግር” ያሉት ጉዳይ በደንብ የተሰራበት እና ዝግጅት የተደረገበት እንደሆነ ለተጠየቁት ” ጃዋር ይህን ያደርጋል ብዬ ለመናገር ይከብደኛል፣ መታወቂያ ሁሉ አሰርተው ምርጫ ለመግባት የሞከሩ ነበሩ። ለሁሉም ግን አልፈነዋል። አሁንም ፓርቲ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ያሉ አሉ” የሚል ጥቅል ምላሽ ሰጥተዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ/ ብልጽግና ኦሮሚያ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባርና (ኦዴግ) በዋናነት የተካተቱበት የጋራ ሕብረት “ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ” ሲቋቋም ብዙ ተብሎለት ምንም ሳይራመድ እንዴት እንደፈረሰ በስካይ ላይት ሆቴል ድራማውን የተከታተሉ እንደሚያውቁት ኦፌኮን የለቀቁት አካላት ያስታውሳሉ።

ይህ ህብረት ውህደቱን ይፋ ለማድረግ በስካይ ላይት ሆቴል ዝርዝር የስምምነት ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለመፈራረም ስነስርዓቱን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሲያሰራጭና፣ ልክ እንደሌሎች ፓርቲዎች ኦህዴድ መፍረሱ በአቶ ለማ በኩል ለማወጅና “ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ” የተባለው ጥምረት ኦሮሚያን እንደሚመራ ለማስታወቅ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ራሳቸው ድንገት ከመድረሳቸው ውጪ ተጋብዘው እንዳልነበር ያስታወሱት እነዚሁ የዜናው ሰዎች፣ “ጃዋር በተመሳሳይ ኦፌኮን አፍርሶ ሊሸጥ ነበር። ከሸፈበት” ብለዋል።

ኦሮሚያን እያስተዳደር ያለው ፓርቲ ምን ቃል እንደገባለት በዝርዝር ባያብራሩም፣ ” ስልጣን እንደሚጋራ ነግረውት ብዙ ርቀት እንዲጓዝ ካደረጉት በሁዋላ ጃዋርን የፖለቲካ ኪሳራ አድረሰውበታል። ከእስር ከወጣ በሁዋላ የብልጽግና ካድሬ እስኪመስል ድረስ ይከራከር የነበረውም በዚሁ መነሻ ነበር። ኦፌኮንም እንደ ፓርቲ ዋጋ አስከፍሎታል” ያሉት ፓርቲውን የለቀቁ አመራሮች፣ በጃዋር ምክንያት በፓርቲ ውስጥ ብዙ ዋጋ የከፈሉ መገፋታቸውንም አመልክተዋል።

“ኦፌኮ ተሽጧል። አቶ በቀለ ገርባና ጃዋር መጨረሻ ላይ የተለያዩትም በዚሁ በኢኮኖሚ ጉዳይ ነው” በማለት ሃዘናቸውን የሚገልጹት የቀድሞ የፓርቲው አባላት ” ኦፌኮ ጃዋር ከመጣበት ቀን ጀምሮ አመራሮቹ በወቅቱ በነበረው ሙቀትና በተነሳ አዋራ ኦፌኮ የቀድሞ መሰረቱን ለቆ፣ በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንዳ ያለውን ከበሬታና ተዓማኝነት ከስሯል” በማለት በወቅቱ ግለት በመነዳት ድርጅታቸውን ዋጋ ያስከፈሉትን አመራሮች ይወቅሳሉ። ጃዋር ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በውጭ አገር ያሰባሰበውን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይና ሚዲያዎች በማስላት ኦፌኮን በስጦታ እቃ ጠቅልለው ያስረከቡ አንድ ቀን በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደሚጠየቁም ያክላሉ። በየዋህነትና በዕምነት አብሮ ለመስራት የተጉ መኖራቸውን በማንሳት ሁሉንም መውቀስ እንደማይቻልም ያብራራሉ። ይህን ሲናገሩ ” ለሆዳቸው ያደሩ” በሚል የተለመደና ውሃ የማያነሳ ስም እንደሚሰጣቸውም ያብራራሉ።

አቶ ጥሩነህ ገምታ ” ኦፌኮ ለጃዋር ተሽጧል” መባሉን አብዝተው ይኮንናል። ከአዲስ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ “ከጃዋር የተገኘ ቤሳ ቤስቲኒ የለም። የአባልነት ክፍያውን ብቻ ይከፍላል” ሲሉ ኦፌኮ የሚሸጥም ሆነ በቀላሉ ማንም የሚነዳው ፓርቲ እንዳልሆነ፣ ከዚያም በላይ ከድሮ ጀምሮ በሚታወቅበት የሰላማዊ ትግል መርሁ ላይ የማይዛነፍ አቋም ያለው ፓርቲ እንደሆነ እንኳን አባላቱ ሊያፈርሱት የሚተጉት እንደሚያውቁ አመልክተዋል። ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር በገንዘብ ጉዳይ ስለመጣላታቸው የሚያዉቁት ነገር እንደሌለም አስረድተዋል። እንዲህ ያለው ጉዳይ ብዙም ፖለቲካዊ ፋይዳ እንደሌለውም ተናገረዋል። አቶ ጥሩነህ በፓርቲ ውስጥ የሃሳብና የእይታ መለያየት ቢኖር እንደማይገርም አንስተው፣ በዚህ ደረጃ ገኖ የሚወጣ ስጋትና ስህተት እንደሌለም አምልክተዋል።

“ኦህዴድን ዋጋ ያስከፈሉት ከኦህደኤድ የወጡ አባላቱ ናቸው” ያሉት አቶ ጥሩነህ፣ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ዋጋ መክፈል ያለና የተለመደ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህንን ያነሱት በፓርቲያቸው በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የተወሰነ ወረራ ተደርጎ እንደነበር በድጋሚ አስታውሰው፣ ማን ይህን እንዳደረገ ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል። ” ብዙ ጊዜ የሌላ ቆዳ ለብሰው፣ አፋቸውን ቅቤ አድረገው የሚሰሩ አሉ። ኦፌኮ በዚህ ዓይነት አግባብ ብዙ ተፈትኗል” በማለትም አካሄዱ አሁን ድረስ መቀጠሉን አስታውቀዋል። እንዲህ ባለው ተግባር ላይ የሚሳተፉት ቀደም ሲል እንደሚታወቀው ጥቅማ ጥቅም ፈላጊዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

እሳቸው ይህን ቢሉም በርካታ የኦፌኮ አባላትና ስድስት የሚሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በይፋ ፓርቲውን ከሚመሩት የበታች አመራር ጋር መሰናበታቸው ኦፌኮን እንደሚጎዳው እየተገለጸ ነው። ስማቸውን ያልተናገሩ የኦፌኮ አመራር ” ችግር የለውም እንዳውም ፓርቲያችንን ያጠራልናል” ብለዋል።

“ይህን ከማለት የተለያ ምላሽ ሊኖራቸው አይችልም” የሚሉት ደግሞ ኦፌኮ ቀጣዩን ምርጫ የመሳተፍ አቅም እንደማይኖረው፣ ፓርቲው በከፍተኛ ደረጃ መመናመኑን ይገልጻሉ። “በተለይም ኦሮሞን እንደ ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው ‘ ያጋላን መንግስት እናጠፋለን’ በማለት በአደባባይ ድርጅት መስረተው ሃብትና ትጥቅ ከሚያሰባስቡ ጋር አብረው የሚሰሩ የድርጅታችን አመራሮች ኦሮሞን እንደ ሕዝብ ቅር አሰኝተዋል። ይህ ኦፌኮን ዋጋ ያስከፍለዋል” የሚል የከረረ ተቃውሞ ያሰማሉ።

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአንድ ወቅት ” እኛ በድርጅታችን ስም ይህን ስሩ፣ ብለን ያዘዝነውና የላክነው አካል የለም” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። አቶ ጥሩነህም ” ኦፌኮ ጃዋርን ከእነ እገሌ ጋር ተሰብስበህ ይህን አድርግ ብለን ቃለ ጉባዔ ወስነን ያስተላለፍንለት ውሳኔ የለም” ሲሉ የሊቀመንበሩን ሃሳብ ያጠናክራሉ።

ይህን አካሄድ የማይደግፉትና ፓርቲውን የለቀቁና አኩርፈው ያሉ በበኩላቸው ” ጃዋር የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ነው። በገሃድ በአመጽ ተግባር እየተሳተፈ ነው። በዚህ የተነሳ ፓርቲው ላይ ለሚደርሰው ማናቸውም አደጋ አመራሮቹ ይጠየቃሉ” ባይ ናቸው። አቶ ጥሩነህ ግን ” ኦፌኮ አባላቱን እየገበረም ቢሆን፣ ከሰላማዊ ትግል አያፈገፈግም። ለሰላማዊ ትግል ያለው ቁርጠኛ አቋም የታወቀ ነው። ስጋት አለን የሚሉት ወገኖች ለጥቅም ብለው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው” ሲሉ ስጋቱን ያጣጥላሉ።

ከአቶ ጥሩነህ በተቃራኒ የቆሙት ግን እንዲህ ባለው አሰላለፍ ውስጥ የተሰለፉትን አካላት ኦነግ እንደማያውቃቸውና አብዝቶ እንደሚቃወማቸው መግለጫ አውጥቶ በገሃድ “የለሁበትም” ማለቱን በማንሳት “ኦፌኮ የቀደመው የሰላማዊ ትግል እምነቱ ካለተለወጠ ለምን እንደ ኦነግ በይፋ አይቃወምም” በማለት “ጨዋታዋ” ሲሉ የጠሩትን አካሄድ እንዳልወደዱት አስታውቀዋል።

ጃዋር ወደ ኦፌኮ እንደመጣ ለፓርቲው ስራ መኪና እንዲገዛ ተጠይቆ “የለኝም” ብሏል። በቢሮ ደረጃ ከደሞዝ ጀምሮ ሰፊ ችግር ስላለ እንዲረዳ ተጠይቆ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ያነሱት ወገኖች፣ ጃዋር በግለሰብ ደረጃ የኢኮኖሚ ውል መፍጠሩን በማስታወስ፣ የአቶ በቅለ ገርባና የሱም ጸብ በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ጃዋር ኦፌኮን ሲቀላቀል በመቶ ሚሊዮኖችና በርካታ መገናኛዎች ባለቤት እንደነበር ይታወሳል።

“ከጃዋር ይልቅ ብልጽግና ይሻለናል” የሚሉት የቀድሞ የኦፌኮ አመራሮች ” ብልጽግና ትልቅ ቢሮ ሰጥቶናል። ቢሯችንን አምስት ሚሊዮን ብር አውጥቶ አድሶልናል። ሁለት መኪኖች ሰጥቶናል። ብዙ ነው ባይባልም ገንዘብ ደጉሞናል” ሲሉ ጃዋር ከውጭ ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ለፖለቲካ ስራ ብሎ ለምኖ ይዞ ገብቶ የፈየደው አንድም ጉዳይ አለመኖሩን በንጽጽር ያሳያሉ። ይልቁኑም አድብቶ ገንዘብ በመርጨት 50+1 አብላጫ ድምጽ በመያዝ ፓርቲውን ከተቆጣጠር በሁዋላ አፍርሶ ብልጽግና ጉያ ውስጥ ለመግባት እንደተጠቀመበት ይናገራሉ።

ጃዋር መሐመድ በግልም ሆነ በጋራ አደረገ ስለሚባለው ማናቸውም ጉዳዮች ምንም እንደማያውቁ ያስታወቁት አቶ ጥሩነህ ” እንዲህ ያለው ወሬ አሉባልታ ከመሆን አያልፍም። በጽህፈት ቤት ኃላፊነቴ እስከማውቀው ድረስ ቤሳቤስቲኒ ከጃዋር የተሰጠን ነገር የለም” ብለዋል። ጃዋር የተባለውን ያደርጋል የሚል ዕምነት እንደሌላቸውም አስታውቀዋል።

አቶ ጥሩነህ ባያውቁትም ሌሎቹ እንደሚሉት ጃዋር እጅግ ከሚጠላቸው አቶ ታዬ ደንደአ ጋር ግንኙነት የጀመረው ኦፌኮን በ50+1 የብልጫ ድምጽ ኦሮሚያን እየመራ ላለው ድርጅት ገጸ በረከት ለማድረግ የዘረጋው ዕቅድ ከከሸፈበት በሁዋላ እንደሆነ አስታወቀዋል። ሂሳቡ ግልጽ አይሁን እንጂ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጋር ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብተው ከነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ በዛው ሰሞን ኝኙነት ጀመረው እንደነበር እውቀቱ እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ይህን ጉዳይ አስመልክቶ አቶ ጃዋር አስተያየት እንዲሰጥ፣ ደጋግመን በግል ስልኩ ለማነጋገር ብንሞክርም አልተሳካም። አቶ ታዬ እስር ቤት በመሆናቸው ከሌሎች ወገኖች ሰፊ ማጣራት በማካሄድ በኦሮሚያ የመንግስት ለውጥ ለማካሄድ የተከወነውን የምናቀርብ ይሆናል። ዜናውን አስመልክቶ ጃዋርም ሆነ የኦሮሞ ብልጽግና ምላሽ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ዝምታን መርጠዋል። ምላሽ ካላቸው በማናቸውም ጊዜ የምናስተናግድ እንደሆነ ከወዲሁ እንገልጻለን።

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related