በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ የትሕነግ ቡድን ከኤርትራው የሻዕቢያ መንግስትና ከሌሎች የክልሉ ጠላቶች ጋር “ህገ-ወጥ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ፅምዶ” በመፍጠር የትግራይን ህልውና ለአደጋ አጋልጧል ሲሉ ከሰሱ።
ፓርቲዎቹ ህወሓት በትግራይ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችን፣ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችንና የፀጥታ አመራሮችን እያፈነ መሆኑን በመጥቀስ፣ ድርጊቱ ክልሉን ወደ አዲስ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊከታት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)፣ ውድብ ነፃነት ትግራይ፣ ዓረና ትግራይ፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ እና ውድብ ወለዶ ትግራይ በጋራ በሰጡት በዚህ መግለጫ፤ በትግራይ ሁሉንም ፖለቲካዊ ኃይሎች (የታጠቁና ያልታጠቁ) ያካተተ አካታች የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ በትህነግ እምቢተኝነት ሂደቱ መደናቀፉን ገልጸዋል።
ፓርቲዎቹ ህወሓት ስልጣንን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ሲል “ትግራይን የማፍረስ” ስራ ተያይዞታል ሲሉ ወንጅለዋል።
የትግራይ ጉዳይ በትግራይ ተወላጆች እንዳይወሰን፣ የትግራይ ብሄራዊ ጥቅም እንዳይረጋገጥ እና ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዳይመለሱ ቡድኑ መሰናክል ሆኗል ብለዋል።
ይህ አካሄድ በክልሉ የተፈጠረውን ሁለንተናዊ ቀውስ ይበልጥ እያባባሰው መሆኑንም አክለዋል።
በተለይ የህወሓት ቡድን የትግራይን የፖለቲካ ምህዳር ለሰላማዊ ትግል ዝግ በማድረግ፣ ቀደም ሲል የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፈጸሙና የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላቶች ከሆኑት “የሻዕቢያ እና የፋኖ” ኃይሎች ጋር ወታደራዊ ቅንጅት ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መግለጫው በዝርዝር አስፍሯል።
ይህ የሻዕቢያ ጣልቃ ገብነት ትግራይን ዳግም የግርግርና የጦርነት ማዕከል ለማድረግ የታለመ “አደገኛ እንቅስቃሴ” ነው ሲሉ ፓርቲዎቹ ኮንነውታል።
የሻዕቢያ መንግስት ከተመሰረተ ጀምሮ ፀረ-ትግራይ አቋም ያለውና በቅርቡ በነበረው ጦርነትም ህዝቡን የጨፈጨፈ ኃይል መሆኑን ያስታወሱት ፓርቲዎቹ፣ “ከዚህ ኃይል ጋር የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ምስጢራዊ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥምረት ለትግራይ ዕዳ እንጂ ፀጋ አይደለም” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተም፣ የህወሓት የፀጥታ ኃይሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን እያፈኑ መሆኑን ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል።
በተለይም ነባሩ የትግራይ ፀጥታ ኃይል ከፍተኛ አመራር ብርጋዴር ጀነራል ጉዕሽ ገብረና ሌሎች በርካታ አባላት ታፍነው እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ያሉበት ቦታ እንደማይታወቅ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ይህ የአፈና ተግባር በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የነበረውን የሰላማዊ ትግል ተስፋ የሚያጨልም መሆኑን የገለጹት ስድስቱ ፓርቲዎች፣ “ሰዎች አማራጭ አጥተው ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ በር የሚከፍት አደገኛ ተግባር ነው” ሲሉ ድርጊቱን በጥብቅ አውግዘዋል። ፓርቲዎቹ የህወሓት ቡድን በአካል ጉዳተኞችና በተፈናቃዮች ስም ከህዝቡ 6 ቢሊዮን ብር በግዳጅ ለመሰብሰብ ያቀደውን ዕቅድም ተቃውመዋል።

ይህ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት በጦርነት የደቀቀውን የትግራይ ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ የሚሰብርና ህዝቡን ወደ ከፋ መከራ የሚከት “ለገዢዎች እጅ መንሻ” የሚውል ነው ብለዋል።
ህዝቡ “አንከፍልም” በማለት ብሄራዊ እምቢተኝነት እንዲያካሂድ ጥሪ ያቀረቡት ፓርቲዎቹ፣ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ስም የተሰበሰበ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉንና ቡድኑ በገንዘብ ረገድ የማይታመን መሆኑ በተደጋጋሚ መረጋገጡን አስታውቀዋል።
ስድስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትግራይ ያለውን አምባገነናዊ አፈና ለመታገል ቆርጠው መነሳታቸውንና ህዝቡም በሚቀጥሉት ቀናት በሚያደርጉት የተጠናከረ የፖለቲካ ትግል ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጥሪ በማቅረብ መግለጫቸውን አጠቃልለዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






