አዲስ ሪፖርተር – “የተወሰኑ በአማራ ትግል ስም የሚምሉ ቡድኖች ህዝባችን መራር መስዋትነት ከፍሎ ከመሃል ሀገር ፖለቲካ ያሰነበታቸውን ሃይሎች ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ ያልተቀደሰ ጋብቻ መፈጸማቸው በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት እንደሆነ አብን በጽኑ ያምናል፡” ሲል አብን መግለጫ አውጣ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ አጀንዳዎችን በተመለከተ ተወያይቶ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አቋሙን ይገልጻል፡፡
በአማራ ክልል የተከሰተው የጸጥታ ችግር ባለፉት ጥቂት ጊዜያት አንፃራዊ መረጋጋት የታየበት ቢሆንም ሰሞኑን ከአንዳንድ አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን መነቃነቅ ተከትሎ ህዝባችንን ለዳግም ሰብአዊ ቀውስ የሚዳርግ ሁነት ተከስቷል፡፡
አሁን ላይ የአማራን ሕዝብ ትግል ማዕከል አልባ በማድረግ ጥያቄዎቹን ከስርዓታዊ ማዕቀፍ የሚያወጣ ፣ የአማራን ህዝብ የሃሳብ መሪ የሚያሳጣ፣ ተቋምና መንግስት አልባ የሚያድረግ እንዲሁም ሕዝቡን ለከፋ የሰበአዊ ቀውስ፣ ለደህንነት ስጋት፣ ለኢኮኖሚ ድቀት አልፎም ለህልውና አደጋ የሚያጋልጥ እንቅስቀሴ አይሎ መምጣቱን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል::
እየተካሄደ ያለው የትጥቅ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያና በህዝባችን ላይ የሚጋሩት ጠላትነት ያስተሳሰራቸው ኃይሎች አንድም የአማራን ህዝብ ዘላለማዊ ዕረፍት የመንሳት አላማቸውን ለማሳካት ሁለትም ሀገር ለማፍረስ የእጅ አዙር አመራር የሚሰጡበትና የሚሳተፉበት እንዲሁም ክስተቱን ለኢኮኖሚ ዓላማ የሚጠቀሙ አካላት የተሰማሩበት እየሆነ መምጣቱን አብን ይገበነዘባል፡፡
እንቅስቃሴው የህዝባችን ውጫዊና የውስጥ ጠላቶች በራሳቸው አቅም ማሳካት ያልቻሉትን እኩይ ዓላማ እንዲያስፈጽሙ በር እየከፈተ ያለ እና የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲዘነጉም እንዲወሳሰቡም የሚያደርግ መሆኑ ስራ አስፈጸሚ ኮሚቴው አስምሮበታል፡፡
አብን የግጭትና የጦርነት ፖለቲካ ለህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ የማያስገኝ ፤ በጎበዝ አለቆች የሽምቅ ውጊያ ዘላቂ የህዝብን ጥቅም ማረጋገጥ፣ ማህበራዊ ፍትሕ ማስፈን እና አሻጋሪ የፖለቲካ ስርዓት ማምጣት አንደማይቻል እና ቅኝቱም ታላቁን የአማራ ህዝብ የማይመጥን ከመሆኑም በላይ የታሪካዊ ጠላቶችን እኩይ አላማ ማስፈጸሚያ ነው ብሎ ያምናል::
በተለይም የተወሰኑ በአማራ ትግል ስም የሚምሉ ቡድኖች ህዝባችን መራር መስዋትነት ከፍሎ ከመሃል ሀገር ፖለቲካ ያሰነበታቸውን ሃይሎች ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ ያልተቀደሰ ጋብቻ መፈጸማቸው በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት እንደሆነ አብን በጽኑ ያምናል፡፡
በመሆኑም የአብን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚከተሉትን ድርጅታዊ ጥሪዎች ያቀርባል፡-
1) የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኃይሎች
በአማራ ህዝብ ስም የሚደረገው የነፍጥ እንቅስቃሴ ጠላፊ እጆች እየበዙበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የህዝባችን ውጫዊና የውስጥ ታሪካዊ ጠላቶች በራሳቸው አቅም ማሳካት ያልቻሉትን እኩይ አላማ እንዲያስፈጽሙ በር እየከፈተ ያለ እና የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲዘነጉም እንዲወሳሰቡም የሚያደርግ በመሆኑ የሰላም አማራጭንና የፖለቲካ መፍትሄን በመቀበል የአማራ ህዝብ ከዚህ የባሰ የመከራ ዶፍ አንዳይወርደበት ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን አንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::
2) ለመላው የአማራ ህዝብ እና የክልሉ ህዝብ
የአማራ ህዝብ በዘላቂ ሰላሙ፣ በህልውናው እና በማህበረ-ኢኮኖሚው ላይ የተጋረጠውን አሁናዊ አደጋ በልኩ ተጋፍጦ ራሱን አርነት እንዲያወጣ እየጠየቅን ህዝባችን ከዚህ ታሪካዊ ቀውስ ለመላቀቅ የሚያደርገው ትግል ከግብ እንዲደርስ ያላሰለሰ ጥረት እንደምናደርግ ማረጋገጥ እንወዳለን።
3) ለፌደራል እና አማራ ክልል መንግስታት
በወቅታዊው የጸጥታ ችግር ምክንያት ህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ ደህንነት አደጋ እና የማህበረ-ኢኮኖሚ ቀውስ ዳፋው ለነገው ትውልድ ጭምር የሚሻገር በመሆኑ የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግስታት ቀደም ሲል የህግና የፖለቲካ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ስናቀርበው የነበረውን ጥሪ ደግመን ለማቅረብ ተገደናል።
በመሆኑም፡-
ሀ). የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና አንደየአካባቢዎቹ ነባራዊ ሁኔታ የተመጠነ የጸጥታ አካላት ስምሪት ያለመኖር እና የህግ ማስከበር ስራዎች መላላት ብሎም ህዝባችን የግጭት ነጋዴ ደላሎችና የሁለት ረገጥ ካድሬወች መፈንጫ በመሆኑ ህዝቡን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሉት ሲሆን የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግስታት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት አንዲሰጡት አንጠይቃለን፤
ለ). ህዝብን ያሳተፉ የጸጥታና የደህንነት ትንተናዎችና የሰላም ማጽናት ተልዕኮዎችን በማጠናከር እና ህዝቡ የራሱን ሰላም እንዲያስከብር ተቋማዊ የማብቃት ስራዎችን በማከናወን ሰብአዊ ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዲወጡ እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶችን በማስጀምር እና የመልካም አስተዳደር ስርዓቱን በማሻሻል ለሰላም መስፍን መደላድሎች እንዲፈጠሩ አንጠይቃለን፤
በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ተዋናይ ከሆኑ አካላት ውስጥ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፉና በህዝቡ ላይ የማይሽር ክህደት በፈጸሙ እና ከጠላት ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻን የተጸየፋ ኃይሎችን በተለያየ ሚዛን እንዲለኩና የሚቀርብላቸው የመፍትሄ አማራጭም በየፈርጃቸው እንዲሆን እናሳስባለን፤
ሐ). ለልዩ ልዩ አካላት
በአማራ ሕዝብ ስም የተደራጁ የተለያዩ ማህበራት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ሚዲያዎች፣ የኢኮኖሚ ልሂቃኖች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የድያስፖራው ማህበረሰብ ወዘተ በአማራ ህዝብና ክልል እየደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ቀውስ እንዲያበቃ የጋራ እርብርብ አንዲያደርጉ እንዲሁም ተናጠላዊ የሰላም ጥረቶችንም አንዲያጠናክሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የካቲት 03/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






