ነጭ ሽብርም ሆነ ቀይ ሽብር በቀለም መጠሪያቸው ካልተለያዩ በቀር ሁለቱም ሽብር ናቸው። መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሞርጌጅ ህንጻ ውስጥ ትሠራ የነበረችውን ባለቤታቸውን መኪናቸው ውስጥ ሆነው በመጠባበቅ ላይ እያሉ አድብተው ይጠብቁ በነበሩ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸው ያለውፈው በወቅቱ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት የጊዜያዊ ጉዳዮች ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ ነጭ ሽብር ከበላቸው ዜጎች አንዱና ነጭ ሽብር ራሱን ያስተዋወቀበት ኦፕሬሽኑ ነው።
ሚስታቸውን ጋንዲ ሆስፒታል ጠይቀው ሲወጡ ቀይ መስቀል አካባቢ አድፍጠው ሲጠብቋቸው በነበሩ የኢህአፓ ነፍሰ ገዳዮች የተገደሉት ሌላው ነጭ ሽብር የበላቸው ዜጋ የወቅቱ የኢሰማኮ ሊቀመንበር የነበሩት ተመስገን ማዴቦ ናቸው።
የሸዋ ልዑል መንግሥቱ ገጣሚ እና ዜማ ደራሲ ጋዜጠኛ እንዲሁም ፀሃፊ ተውኔት ነበረች። ገና በ32 ዓመት ዕድሜዋ ነው ነጭ ሽብር የበላት። የሸዋ ልዑል መንግሥቱ አምስት ልጆች እናት ነበረች። ግንቦት 1969 ዓ.ም ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየቸው የሸዋ ልዑልና መስለ ዜጎችን ነጭ ሽብር በልቷል።

በእነዚህ የተጀመረው ነጭ ሽብር በርካታ ዜጎችን በፖለቲካ እምነታቸውና በአሰላለፋቸው መነሻነት ደፍቷቸዋል። ይህ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። ኢህአፓ እንዲነሳ አይፈለገውም እንጂ ነጭ ሽብር የበላቸውን ዜጎች ታሪክና አበላል አይክደውም። በአንድ ወቅት አንድ ለጊዜው ስማቸውን ማስታወስ ያልቻልናቸው ዜጋ “ነጭም ሆነ ቀይ፣ ሽብር ሽብር ነው” ሲሉ በእኩል ደረጃ ምርመርና ፍርድ ሊሰጠበት እንደሚገባ አሜሪካን አገር በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ተናግረው ነበር።
ዛሬ ዘመን ቆጥሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ “ነጭ ሽብር ግን ለምን ተዘነጋ?” በሚል ጥያቄ አዘል ማመልከቻ ማቅረባቸው የጉዳዩ ባለቤት፣ ”ነጭ ሽብርን የጽድቅ ተግባር” አድርገው በሚያዩና “ጉዳዩን አታንሱብን” በሚሉ ወገኖች ከወዲሁ ተቃውሞ እየተነሳበት ነው።
“በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ሁለት ዓይነት “ሽብሮች” ተካሂደዋል። ነጭ እና ቀይ። ስለ ቀይ ሽብር ይነገራል። ክስ ተመሥርቷል። ፍርድ ተሰጥቷል። ሙዝየም ተመሥርቷል። ነጭ ሽብር ግን ለምን ተዘነጋ? ለምንስ ከሙዝየም ውጭ ሆነ? ቀይ ሽብርን ፈጻሚ ተቋማቱስ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው እንዲመጡ ለምን ተፈቀደ? ነገሩን እንደገና ማየት የለብንምን?” ሲሉ የጠየቁት አማካሪ ሚኒስትሩ ጥያቄውን ከማንሳትና ሁለት ዓይነት ሽብር በኢትዮጵያ ታሪክ ተካሂዶ አንዱ ላይ መፈጸም ያለበት የሕግና ተመሳሳይ ጉዳዮች ተግባራዊ ሲደረጉ አንዱ ዝም መባሉ አግባብ እንዳልሆነ በጥያቄ መልክ ከማቅረባቸው በዘለለ ዝርዝር አላቀረቡም።
በዘመን ኢህአዴግ የቀይ ሽብር ሰማዕታትን ሃውልት ከመገንባት ጀምሮ የፍርድ ሂደት መካሄዱን ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ሲሠራበት ”በነጭ ሽብር ቤተሰቦቻችን የተገደሉብንስ?” በሚል ጥያቄ ላቀረቡ የሰጣቸው ምላሽ እንዳልነበር ይታወሳል። ቢፈለጉና የሚያስታውሳቸው ቢገኝ የዚያን ጊዜ ቅሬታ ያቀረቡና የሕግ ጥያቄ ያነሱ ዛሬም አይጠፉም። ምን አልባትም የዲያቆን ዳንኤል የተቆርቋሪነት ጥያቄ እነዚህን ወገኖች ከያሉበት ያስነሳ ይሆናል። ጉዳዩ የተነሳው በአንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከመሆኑ አንጻር ብዙ እርምጃ ሊሄድ የሚችል እንደሆነ ያመላክታል።
ፕሮፌሰር መረራ “ዋጋ ቢስ፣ ውሸት” በማለት ምሥጢሩን እንደገለጡት እንደ አኖሌ ሃውልት፣ ትህነግ የቀይ ሽብርን ጉዳይ ለጊዜያዊ ፖለቲካ ሲል ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ አዋለው እንጂ ለኢህአፓ አባላት፣ ኢህአፓ በመሆናቸው ለተገደሉና ለቤተሰቦቻቸው አስቦና ተጨንቆ እንዳልነበር በወቅቱ ተመልክቶ ነበር።
ትህነግ ለቀይ ሽብር ሰለባዎች የመታሰቢያ ለቅሶ አውጆ ፕሮፓጋንዳውን ሲያስኬድ ጎን ለጎን ድንኳን የጣለለትን ኢህአፓ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባና በወቅቱ የአገሪቱ የሽግግር ፖለቲካ እንዳይካፈል ከማገድ ጀምሮ ያልፈጸመበት ደባ አልነበረም። ይህም በወቅቱ ተጽፏል። አጽማቸውን ለፕሮፓጋንዳ፣ ተሳትፏቸውን ለጥይት!!
ታሪክ እንደሚያስረዳው ትህነግ አዲስ አበባ ድንኳን ጥሎ፣ አጽም እየሰበሰበ ሲያላቅስና ፕሮፓጋንዳ ሲሸምትበት የነበረውን ኢህአፓን ከደደቢት ጀምሮ እስከ አሲምባ ከሻዕቢያ ጋር ሆኖ ደምስሶታል። በረሃ ለረሸነው ኢህአፓ አዲስ አበባ ላይ “ቀይ ሽብር ተፋፋመብህ” ብሎ ለቅሶ የተቀመጠው፣ ብይን የሰጠውና ሃውልት የተከለው ትህነግ፣ “በነጭ ሽብር ቤተሰቦቻችንን፣ ልጆቻችንን፣ ባሎቻችንን፣ ሚስቶቻችንን ያጣን ማን ፍርድ ይሰጠን?” በሚል ላቀረቡት ጥያቄ ምላሹ “ዘወር በሉ” የሆነው፤ ለወቅቱ ፕሮፓጋንዳ ገበያ ስለማይበቃ እንጂ ነጭም ሆነ ቀይ ሽብር ሽብር መሆኑን ከትህነግ በላይ የሚረዳ፣ ወይም የሽብር ፋብሪካ ለሆነው ትህነግ ምሥጢር ሆኖ አልነበረም።
ኢትዮጵያ በዚያድ ባሬ ስትወረር፤ ኢህአፓ በይፋ ሶማሊያን መደገፉ የዘለዓለም መለያው እንደሆነ ታሪክ ያሳየናል። ሌሎች ለማስተባበል ቢሞክሩም እንደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አይነቶች መረጃ በማውጣት የኢህአፓን የወቅቱን የክህደት ሰነድና ዓቋም ለዚህ ትውልድ አውርሰዋል። ነጭ ሽብርም ታሪካቸው ነው። ቀይ ሽብር ያወደመውን የሰው ልጅና ያፈረሰውን ቤት የሚያስቡ ሁሉ ነጭ ሽብርም ሽብር ነውና በልኩ ሊመዘንና የሕግ ብያኔ፣ የመታሰቢያ ሃውልትና ሙዚየም ከቀይ ሽብር ጎን ለጎን ሊደረግለት እንደሚገባ ሲከራከሩ ለነበሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ያነሱት አሳብ፤ የሰነዘሩት ጥያቄና ያስገቡት ማመልከቻ “ዘገየ” ካልተባለ በቀር ተራ የማኅበራዊ ሚዲያ ገበያ የሚመስለው ካለ ስህተት ነው።
ነጭ ሽብር በኢትዮጵያ እንዴት ተጀመረ? ለምን ተጀመረ? ማን አስጀመረው? ለሚለው ጥያቄ ኢህአፓ የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግል ለመጀመር ሲወስን ተከትሎ የመጣ የትግሉ ፍሬ እንደሆነ አባላቱ በተለያዩ ጊዚያት መስክረዋል። በዚሁ ምስክርነታቸው ሳቢያ “ነጭ ሽብር ቅዱስ ተግባር ነው” ከሚሉት ጋር ጎራ ለይተው መካሰሳቸው አይዘነጋም። አሁንም ይህ ጎራ የለየ መካሰስ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
በውጭ አገር ያሉ ተቃዋሚዎች በሰላማዊ ትግል ሽፋን አሁን ላይ በኢትዮጵያ እንዲደገም እየቀሰቀሱና ሃብት እያሰባሰቡ ያሉት ይህንኑ የነጭ ሽብር ታሪክ ለመድገም እንደሆነ አብሮነት ውስጥ ያሉ ለአዲስ ሪፖርተር መናገራቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም፤ እነዚህ ወገኖች ከሚረዷቸው የውጭ ኃይሎች ጋር ሆነው “ይህ መንግሥት በጦርነት አይወድቅም” በማለት ይህን ስልት እንደሚጠቀሙ ይፋ ባደረጉ ቀናት ውስጥ ዘመነ ካሴ ፋኖ ትግሉን ከገጠር ወደ ከተማ ውስጥ ትግል እንደሚቀይር ማስታወቁ አይዘነጋም።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






