አደራ የተሰኘው አዲሱ ሚስጥራዊ የሙስና ጥቆማ መስጫ ስርዓት በይፋ ተጀመረ

Date:

አዲስ ሪፖርተር – የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ከ40 በላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (ኢኢኤች)፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ሙስናና ብልሹ አሠራር ለመዋጋት ያለመ አዲስ ዲጂታል የጥቆማ መቀበያ ስርዓት ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።’አደራ’የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አዲስ ስርዓት፣ ማንኛውም ግለሰብ ባለበት ሆኖ ሚስጥራዊነቱ ሙሉ በሙሉ በተጠበቀ መልኩ የሙስና እና ብልሹ አሠራር ጥቆማዎችን ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል። ይህ እርምጃ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሀብት የማስመለስ አቅም ከፍ የሚያደርግና የድርጅቶቹን አፈጻጸም የሚያሻሽል ነው ሲል ሆልዲንግሱ ገልጿል።

በመግለጫው ላይ የተናገሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል፣ ይህንን የጥቆማ መስጫ ስርዓት መዘርጋት ያስፈለገው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ሙስና እንዳይፈጸም መከላከል እና ከተፈጸመ ደግሞ ተጠያቂነትን በአግባቡ ለማረጋገጥ በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል።

ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፣ ምንም እንኳን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የራሳቸው የሆነ ውስጣዊ የአሠራር ሥርዓት፣ የኦዲት ሪፖርትና ሌሎች የቁጥጥር መዋቅሮች ቢኖራቸውም፣ የበለጠ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ግልጽነትን ለማምጣት ሲባል አዲስና የተጠናከረ የሙስና ጥቆማ መስጫ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሀብታሙ፣ ይህ አዲሱ ‘አደራ’ስርዓት የልማት ድርጅቶችን ሀብት የማስመለስ አቅማቸውን ከፍ ከማድረጉ ባሻገር፣ ሙስና እንዳይፈጸም በመከላከል የተቋማቱን አጠቃላይ የመፈጸም አቅም እንደሚጨምረው ጠቁመዋል። ይህም የድርጅቶቹን ዘላቂ ዕድገትና ውጤታማነት ያረጋግጣል።

አቶ ሀብታሙ  ኃይለሚካኤል አክለውም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከዚህ በፊት በእዳ ጫና፣ በውጤታማነት ማነስና በብልሹ አሠራር ችግሮች ሲፈተኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተቋቋመባቸው ዋና ዓላማዎች አንዱ እነዚህን መሰል አሠራሮች እንዳይደገሙ ማድረግና የተቋማቱን ውጤታማነት ማሳደግ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሆልዲንግሱ ሠራተኞች ተዘጋጅቶ በድረ ገጽ (website) መልክ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ‘አደራ’ ስርዓት፣ በቅርቡ ደግሞ በሞባይል መተግበሪያ (አፕልኬሽን) መልክ ተዘጋጅቶ ለተገልጋዮች እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

የሙስና ጥቆማዎችን የማቅረብ ሂደቱን በተመለከተ፣ ድረ ገጹን በመጠቀም በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ጥቆማዎችን ማቅረብ እንደሚቻል አብራርተዋል።ሆልዲንግሱ በቀጣይ ግን በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ቋንቋዎች ጭምር የሙስና ጥቆማዎችን ማቅረብ እንዲቻል ሥርዓቱን እንደሚያዘምን ዛሬ ሐሙስ በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

በልማት ድርጅቶች ውስጥ ተጠያቂነትን ለማስፈን ይረዳል የተባለውን አዲሱን ድረ ገጽ በመጠቀም የሚላኩ የሙስና ጥቆማዎችን የሚያዩት የተቋሙ ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች ብቻ እንደሆኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በተጨማሪም ጥቆማዎቹን የሚያጠናና ወደሚመለከታቸው አካላት የሚልከው ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የሚቋቋም ቡድን እንደሚኖር ተመልክቷል።

በመግለጫው ወቅት የጥቆማ መስጫ ድረ ገጹ ጠቋሚዎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ ማስገደዱን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። አንዳንድ የሙስና ጥቆማዎች በቅጽበት ማስረጃ ላይኖራቸው ስለሚችል፣ ይህንን እንዴት ለመፍታት እንደታሰበ ተጠይቋል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የሆልዲንግሱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶ/ር እስማኤል ከድር፣ ማስረጃ እንዲቀርብ መፈለጉ ትክክለኛ የሙስና ጥቆማዎችን መስጠት የሚችሉ ሰዎች ችግር እንዳይገጥማቸው እና ሁሉም ሰው ወደ ድረ ገጹ እየመጣ አሉባልታዎችን እንዳይጠቁም በሚል ታስቦ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ሆኖም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የብልሹ አሠራርና የሙስና ጥቆማ መስጫ ዲጂታል ስርዓት ይፋ ሲደረግ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር ከሚተዳደሩት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ኢኢኤስ)፣ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ “EEU Anti-corruption” የሚል ስያሜ ያለው የሞባይል መተግበሪያ አስተዋውቆ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሞባይል መተግበሪያውን ስራ ላይ ማዋል ያስፈለገው፣ በድርጅቱ በሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ የሙስናና ብልሹ አሠራር ቅሬታ ሲኖራቸው ደንበኞች በቀላሉ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ለማድረግ ነበር። ያ መተግበሪያ ደግሞ ደንበኞች ለሚያቀርቡት ጥቆማ ማስረጃ የሚሆኑ ምስል፣ ቪዲዮ እና የጽሑፍ ሰነዶችን መጫን ያስችላል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በ40 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የተጠያቂነትና የቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር፣ የሀገርን ሀብት ለመጠበቅና የተቋማቱን ውጤታማነት ለማሳደግ ያለመው “አደራ” የተሰኘው አዲሱ የጥቆማ መስጫ ስርዓት ሥራ ላይ መዋሉ ለሙስና ትግል አዲስ ምዕራፍ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ፕሬዝዳንት ማክሮን አውሮፓ “ከየዋህነት ወደ ስትራቴጂካዊ ጥንካሬ” መመለስ አለባት አሉ

አዲስ ሪፖርተር ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  ባልተለመደ መልኩ ጥቁር መነፀር...

“ግሪንላንድ ለድርድር አትቀርብም”

አዲስ ሪፓርተር - የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር...