ስጋት ትልቁ ምክንያት ነው። ሻዕቢያ በተግባር የተፈተሸ ከሃጂ በመሆኑ አይታመንም፤ መንግስት ሻዕቢያን ካጠፋ እኛንም አይለቀንም የሚለው ድንቁርና የተጫነው እሳቤ አይሰራም። ሻዕቢያ ከሚጠፋ እኛ አስቀድመን እንጥፋለት። ትግራይን ለሻዕቢያ ስንል የጦርነት አውድማ እናድርጋት የሚለው አመክንዮ አልባ፣ ትርጉም የለሽ ቅስቀሳ ዛሬ ላይ በትግራይ ሰሚ የለውም።
አዲስ ሪፖርተር – ህወሃት የፖለቲካው ክንፍ በከፍተኛ የውስጥ ለውስጥ መፈረካከስ ውስጥ መሆኑ፣ አሁን ላይ የሚሰማው ይህ መለያያት ከሻዕቢያ ጋር ከተፈጠረው አለመተማመን መጨመር ጋር ተያይዞ እንደሆነና የሚታወቁ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች ከወዲሁ የእነ ሞንጆሪኖን ቡድን እየተለዩ መሆኑን አዲስ ሪፖርተር ከታማኝ ምንጮች አረጋግጣለች።
በዶክተር ደብረጽዮንና ሞንጆሪኖ ይመራል የሚባለው የህወሃት አንድ ቡድን ውስጥ የተጀመረው መከፋፈል ወደ ጦር አመራሮቹም እየተዛመተ መሆኑን የገለጹልን በትግራይ የሚገኙ ከፍተኛ የሰራዊት አመራር ሲሆኑ ያገኘናቸው በቤተሰብ አማካይነት ነው። ወደ ከፍተኛ ጦር አመራሮቹ የተዛመተው ይህ መከፋፈል ዋና ምክንያቱ ደግሞ ስጋት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመጣቱ ነው።
አዲስ ሪፖርተር ያነጋገረቻቸው በትግራይ ያሉ ሁለት የሚዲያ ባለሙያዎችና ለከፍተኛ የሰራዊት አዛዥ ቅርበት ያላችው ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ከሆነ በከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች መካከል የተፈጠረው የአካሄድ ልዩነት ዋናው ጉዳይ ሻዕቢያን አስመልክቶ ነው።
በትግራይ የሚታየው ወቅታዊ አሰላለፍ የጦርነት ኩኔታ
አሁን ባለው ወቅታዊ አሰላለፈ የእነ አቶ አለም ገብረዋህድ ቡድን ሰፊ ድጋፍ ያለው ሲሆን፣ ይህ ቡድን አቋሙ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመያዝ በሰላማዊ ንግግር መፍትሄ የማፈላለግ ፍላጎት ያለው ነው። መረጃ አጣቀሰው ግምገማቸውን ያካፈሉን እንደሚሉት የክልሉ ጊዜያዊ መሪ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ከዚህኛው ምድብ ናቸው። ይህ አሰላለፍ ከሻዕቢያ ጋር የተጀመረውን ግንኙነት አይደግፍም። ይቃወማል።

ከወትሮው በተለየ ሰሞኑን በከፍተኛ ደረጃ እያነጋገረ ያለው ጉዳይ መነሻና መድረሻቸው ሻዕቢያ ሲሆን፣ “መንግስት ሻዕቢያን ካጠፋ እኛንም ያጠፋናል፤ ስለዚህ ከሻዕቢያ ጎን እንሁን” በሚል እነ ሞንጆሪኖን የሚከተለው ኃይል “ ሻዕቢያ ከሚጠፋ እኛ ቀድመን እንጥፋለት። ሻዕቢያ ከሚመታ እኛ ትግራይ ላይ ጦርነቱን አድረገን ትግራይን አናፍርሳት” እንደማለት መሆኑን ጠቅሰው ለሚከራከሩ ወገኖች በአመክንዮ የተደገፈ ምላሽ ማቅረብ አልቻሉም። እናም እየዋለ ባደረ ቁጥር ይህ ጥያቄ ወደ ጦሩ ከፍተኛ አመራሮች እየዘለቀ ሄዶ አሁን እየተሰማ ላለው መከፋፈል ምክንያት ሆኗል። ይህ ብቻ አይደለም እንደ መረጃው ከሆነ አዲስ ስጋት መፈጠሩ የኃይል አሰላለፉን መለያየት አፋጥኖታል።
በውጤቱም ቀደም ሲል ጀምሮ በስጋት “ጽንፈኛ” ከሚባለው የእነ ዶክተር ደብረጽዮን / ሞንጆሪኖ ቡድን ጋር የተቀላቀሉት ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች አሁን ላይ ሌላ ተጨማሪ ስጋት ታክሎባቸዋል። ስጋቱም አሜሪካ በቀጥታ ከሻዕቢያ ጋር ንግግር በመጀመሯ የተፈራውን የጦርነት ወሬ መላዘቡ ነው።
ከበረሃው ትግል ጀምሮ ሻዕቢያ ታማኝ የትግል አጋር እንዳልሆነ የሚናገሩት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ስጋታቸው ስምምነት የሚፈጠር ከሆነ እነሱ ወደ ህግ ያመራሉ ወይም ሕግ ይጠይቃቸዋል። በተለይም የቀድሞ የደህንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ በሌሉበት 18 ዓመት የተፈረደባቸው በመሆኑ ስጋቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚመለከታቸው ናቸው።
አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ ከፍተኛ መኮንን እንዳሉት ሲጀመር ጀምሮ ሻዕቢያ አብረውት እየሰሩ ላሉ የትህነግ ኃይሎች ዕውቅና አልሰጠም። ግንኙነቱ ሁሉ በጓሮ በመሆኑ ምንም ዓይነት ዋስትና የለም። ሰሞኑን አቶ ጌታቸው ረዳ ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት እንደማይጀመር መናገራቸው፣ አሜሪካ በቀጥታ ከሻዕቢያ አመራሮች ጋር ግንኙነት መፍጠሯ በህግ የሚፈለጉ ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮችን ስጋት ላይ እንደጣላቸው እንደሚያውቁ አመልክተዋል። ስጋቱ ከፍተኛ በመሆኑ ከሻዕቢያ ጋር ከተጀመረው ግንኙነት ጋር ሳይፍለጉ ለመጣበቅ አስገድዷቸዋል።
ሰሞኑን የአንዳንድ ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች ስም እየተጠቀሰ ስለሚወራው የተጠየቁት ከፍተኛ የሰራዊት አመራር፣ “አንድ ወይም ሁለት ሰው ሳይሆን በአቋም ደረጃ ሻዕቢያ እንደማያዋጣና ታሪኩ ሊታመን የማይችል ከሃጂ ድርጅት መሆኑን ስለሚያረጋግጥ አሁን ላይ ከሻዕቢያ ጋር የተጀመረው ጥምረት እየፈረሰ ነው” ብለዋል።
“ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ አሁን ላይ የእነ ሞንጆሪኖን ቡድን ተለይተዋል” በሚል ለቀበላቸው ጥያቄ “ እሱ አንዱ ሊሆን ይችላል። መታየት ያለበት ጥቅል ጉዳዩና እየሆነ ያለው የልዩነት ደረጃ ወዴት እያመራ ነው? መንግስት ይህንን ተከትሎ ምን ማድረግ ይገባዋል? ባለስልጣናት በየመድረኩ የሚያሰሙትን ‘ህወሃትን እናጠፋዋለን’ ቀረርቶ በማቆም እንዴት በማስተዋል መስራት እንደሚገባቸው ነው” በማለት እኚሁ ከፍተኛ መኮንን ምክር አዘል አስተያየት ሰጥተዋል። አዲስ ሪፖርተር የመኮንኑን ምክር አዘል አስተያየት ሙሉ አሳብ በቀጣይ ያቀረባል።
እኚሁ ከፍተኛ መኮንን ከሻለቃ በታች ያለው አብዛኛው ጦር የሚገባው ጥቅማ ጥቅም ተፈቅዶለት በሰላም ወደቤቱ መመለስና ሰላማዊ ኑሮ መጀመር እንደሚፈልግ ገልጸዋል። ይህ አብዛኛ የሰራዊት ክፍል ጦርነትን ሊዋጋ ቀርቶ የጦርነት ወሬ መስማት አይፍለግም። “እመኑኝ” ሲሉ የተናገሩት እኚሁ ከፍተኛ መኮንን አጋጣሚውን ስራና የመኖሪያ አማራጭ ያደረጉ ከኮርና አርሚ በላይ ያሉ የሰራዊት አመራሮችም እንዳሉ አልሸሸጉም።
ተጥለው የነበሩ ነባር ታጋዮች በጥበቃና አነስተኛ ስራ ተሰማርተው እንደነበር የሚናገሩት መኮንኑ፣ በዳግም ጥሪው እነዚህ ወገኖች ወደ ኮርና አርሚ አመራር ከፍ ብለዋል። በዚሁ ሹመታቸው ሳቢያ መኪና፣ ከፍተኛ ደሞዝ፣ በጀትና መኖሪያ ቤት ወዘተ አግኝተዋል። እነዚህ ወገኖች ጦርነትን የኑሮ ማስቀጠያ ስላደረጉት ከጽንፈኛው ቡድን ጋር ናቸው። እነዚህ ወገኖች እንደ ሌሎቹ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ያስቸግራል። ማስተማመኛ የሚፈልጉ እንደሆኑ አመልክተዋል።
ከሻዕቢያ ጋር ይኖራል ስለሚባለው ጦርነት አሁን ላይ መላዘብ እየታየ መሆኑን ያመለከቱት ከፍተኛ መኮንኑ፣ የሻዕቢያ መላዘብ አሜሪካ ከጀመረችው ግልጽ ያልሆነ ግፊትና ከትህነግ የሚፈልገውን ድጋፍ በሚጠብቀው መልኩ ስለ ማግኘቱ እርገጠኛ መሆን ባለመቻሉ እንደሆነ አመልክተዋል። ሕዝብ ምንም ዓይነት ጦርነት አለመፈለጉ፣ አብዛኛው የሰራዊቱ አባላት ውጊያ መቃወማቸውና አሜሪካ የጀመረችው ሚስጢራዊ እንቅስቃሴ ተዳምሮ የውጊያውን ጉዳይ ከቀድሞው ግለት አውርዶ እንዳፋዘዘው ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የአፍሪቃ ቀንድ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤርትራ ጋር ጦርነት እንደማይደረግ መናገራቸው ተራ መረጃ እንዳልሆነ አስተያየት ሲሰጥ መስነበቱ አይዘነጋም። እሳቸው ለአልጀዚራ ይህ ከተናገሩ ወዲህ የሁለቱ አገራት መካረር በሚዲያ ደረጃ መቀነሱን በርካቶች በትዝብት ደረጃ ይናገራሉ።
የማዕከላዊ ኮሚቴ ድጋፋቸውን እያጡ ያሉት የእነ ሞንጆሪኖ ቡድን አብዛኛውን የላይኛውን የሰራዊቱን አመራር ይዞ የቆየ ቢሆንም በዚህ አቋሙ ሊቀጥል እንደማይችል እኚሁ ከፍተኛ መኮንን አስታውቀዋል። “ግን” አሉ መኮንኑ “ ግን መንግስትም ሆነ ከፍተኛ ባለስላጣናቱና ደጋፊዎቹ ይህን በጽንፈኛው ቡድን ላይ እየደረሰ ያለውን የውድቀት አደጋ መልሶ እንዲያገግም የሚያደርግ ፉከራና ንግግር በማቆም በማስተዋል ሊያደርጉት ይገባል” ብለዋል። “ህወሓት” እናጠፋለን የሚለው ሃሳብ ስህተት መሆኑን፣ ህወሓት ከህዝብ ጋር ያለውን የታሪክ ቁርኝት ጠንካራ እንደሆነና ህወሓት መጥፋት ካለበትም የሚጠፋው በትግራይ ህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ መሆኑን ከግምት ውስጥ ያስገባ አካሄድ መከተል ጠቃሚ እንደሚሆን መኮንኑ መክረዋል። አግባብ ያለው አካሄድም ይህ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከዚህ የዘለለው የፉከራ አግባብ አሁን ትግራይን ወደ ከፋ መነግድ እየገፋ ላለው ጽንፈኛ ቡድን ነዳጅና ጉልበት ከማቀበል የዘለለ ውጤት እንደማያስገኝም አጠንክረው ተናግረዋል፤
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ እናጠፋቸዋለን” በሚል የሚተላለፉ መልዕክቶችን የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን እንደ መልካም ግብአት እንደሚጠቀምበት የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች በተደጋጋሚ ቢገልጹም እርምት ሲወሰድበት እናደማይታይ በርካቶች ይናገራሉ። በተለይም መንግስትን እንደግፋለን የሚሉ የማህበራዊ ሚዲያ ሰልፈኞች የሚያሰራጩት ስሜት ላይ የተመረኮዘ አካሄድ ሊታሰብበትና ሊገራው የሚገባ አካል ሊቋቋምለት እንደሚገባ በርካቶች ይመክራሉ።
አሁን ላይ ከፈተኛ የሰራዊቱ አመራሮች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ከመንግስት ጋር ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ ለመነጋገር እየሰራ ካለው የእነ ዓለም ገብረዋህድ ቡድን ጋር ለመስራት እየወሰኑና ከሻዕቢያ ጋር ጥምረት የፈጠሩትን እየተለዩ ነው። የተባበሩን የሚዲያ ማለሙያዎች አሁን ላይ “ሻዕቢያ ከሚጠፋ እኛ ቀድመን እንጥፋ፣ ትግራይን የጦርነት አውድማ እናድርግ የሚለው ድንቁርና የተጫነው አመለካከት የሚገዛው የለም። ወድቋል” ብለዋል።
ትህነግ ከነበሩት 700 ሺህ የሚጠጉ ካድሬዎች መካከል ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር በትግራይ “ እንኳን በጥይት በቲማቲም መፈናከት የሚፈልግ የለም። ይህ የሕዝቡ ብቻ ሳይሆን የሰራዊቱም ዕምነት ነው” ያሉት እነዚሁ ወገኖች “ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ላይ በማናቸውም የትግራይ ተወላጆች ዘንዳ ያለው እምነት ተመሳሳይ በመሆኑ መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባ ንገሩልን” የሚል መልዕክት አስተላለፈዋል።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





