አዲስ ሪፖርተር “ጦርነቱ ከተጀመረ አስመራ አፍንጫ ደርሶ አይቆምም። በውጤቱ ኤርትራ የምትቀጥለው ልክ ለዩክሬን እንደቀረበላት ዓይነት ምርጫ መሬት ልውውጥ ነው። በልውውጡ ኢትዮጵያ አሰብን ትወስዳለች” በሚል ከሚነሳው የበርካቶች አሳብ ጋር የሚያያዝ ግምገማ ነው የሰጡት …
“ጅኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል” ለሚለው የፕሮፌሰር ብርሃኑ ንግግር ” ከጠርሙሱ የወጣው ጂኒ ቦዘኔው ነው። ቦዘኔ ለውጥ አምጥቶ አያውቅም” የሚል መልስ በመመለስ በምርጫ 97 ወቅት የተወገዙት አቶ በረከት ስምዖንን አስመልክቶ አንድ መግባቢያ አለ። የሚጠሏቸውም የሚወዷቸውም በፖለቲከኛነታቸው ያደንቋቸዋል።
በ1993 ዓ.ም ትህነግ ውስጥ የተከሰተውን ክፍፍል ተከትሎ በበላይነት ከወጡት የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀ መንበርን አቶ መለስ ዜናዊ ጎን በቁርጠኛነት እንደቆሙ የሚመስከርላቸው አቶ በረከት ኢህአዴግ ውስጥ ዋና ሰው ሆነው መታየት የጀመሩት ከዚያን ጊዜ በሁዋላ ነበር።
“ሃሳባቸውን አደራጅተው በመናገርና የፓርቲውን የርዕዮተ ዓለም የመንግሥትን ፖሊሲዎች በመተንተን በኩልም ከሌሎች ባለሥልጣናት ጎልተው የሚታዩ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል” ሲል ቢቢሲ የሚገልጻቸው አቶ በረከት በስደት ካሉበት አሜሪካ አነጋጋሪ ግምገማ አቅርበዋል።
ለጊዜው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የሚዲያ ሰው አቶ በረከትን አግኝቶ ግምጋማቸውን ካደመጠ በሁዋላ በመገረም ስሜቱንመቆጣጠር እያቃተው ለኢትዮሪቪው የአሜሪካ ተባባሪ የሰማውን አካፍሏል።
ትህነግን አስመልክቶ
አቶ በረከት በአጭሩ የሌቦች ስብስብ ሲሉ ነው የገለጹት። መተካካት ተብሎ ሲጀመር ውሳኔውን ተቀብለው በጥቅም ሳቢያ ተግባራዊ ሳያደርጉ አሁን ድረስ መቆየታቸው እንደፈረካከሳቸው አቶ በረከት ገልጸዋል።
ኢህአዴግ ወደ ፓርቲ ካልተቀየረ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ከመፈራረሱ ሁለት ዓመት በፊት ሪፖርት አዘጋጅተው ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ አንዱ እንቅፋት የነበሩት እነዚሁ “ሌቦች” ያሉዋቸው የትህነግ ሰዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። የተባለው አልቀረም ኢህአዴግ በፈጣሪው ትህነግ ስግብግብነት የተነሳ እያዩት ሟሟ።
እሳቸው እንዳሉት ትህነግ ካሁን በሁዋላ የመታደስ ደረጃውን ቀርጥፎ በልቷል። የመለወጥ፣ የመጠገንም ሆነ የማገገሚያ ጊዜ የለውም።
የትህነግና ሻዕቢያን ጥምዶ አስመልክቶ
ኢሳያስ አፉወርቂ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንዲወገዱ ቀጠሮ የተያዘላቸው መሪ መሆናቸውን እንዴት የትህነግ አመራሮች እንደሳቱት ለአቶ በረከት ግራ ነው። ከዚህ ዓለም “በቃው” ካለውና ጊዜውን ከሚጠባበቅ ሰው ጋር መቀናጀት ሌላ ዓለም ዓቀፍ ሸምቀቆ ባራስ አንገት ላይ ማጥለቅ እንደሆነ አንዳልተረዱ ይገልጻሉ።
“ከሁሉም አቅጣጫ የተዘጋን መሆን የለብንም። መተንፈሻ ያስፈላግል” በሚል የትህነግ ሰዎች ምጽዋን ለመጠቀም አማራጭ እንዳላቸው ለሚናገሩት ” ስለ ምድራዊ መከበብ ሲያስቡ ወደ ባሰው የፖለቲካ ዓለም ዓቀፍ ከበባ ውስጥ ወድቀዋል” ሲሉ አቶ በረከት አስታወቀዋል።
የጋዛን ጉዳይ ያነሱት በረከት፣ ጋዛ የባህር አማራጭ ቢኖራትም እስራኤል ካልፈቀደች ከቶውንም መጠቀም እንደማይችሉ አመልክተው፣ አሁን ባለው እውነታ የኢትዮጵያ መንግስት ሳይፈቅድ በምጽዋ ወይም በሌላ ወደ ስለመጠቀም ማሰብ እጅግ አስገራሚ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዋናነት ያነሱት ግን ኢሳያስ ሲወገድ ሁሉም ነገር አብሮ እንደሚያከትም አስቦ መንቀሳቀስ ብልሃት መሆኑን ነው። እሳቸው ባይገልጹትም ኤርትራን ከኢሳያስ በሁዋላ እንዴት ማስኬድ እንደሚቻል የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ዓቀፍ ወዳጆችና ተመሳሳይ የፖለቲካ አቋም ካላቸው ጋር እየተሰራ መሆኑን አንዳንድ ምንጮች ይጠቁማሉ።
አቶ ልደቱ
አቶ በረከት አቶ ልደቱን ያነሱት ራሳቸውን በማወዛወዝ ” ሄዶ ሄዶ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ልደቱ እጅ ይውደቅ?” በሚል ለራሳቸው ሲጠይቁ ነው።
የአቶ ልደቱን ፍጥርጥር ጠንቀቀው የሚያውቁት አቶ በረከት፣ ብልጽግና ለአቶ ልደቱ ኢህአዴግ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት እንደማይሰጥ አመልክተዋል። አያይዘውም ብልጽግና አቶ ልደቱ ልደቱ ለሚያደርጋቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ስጋትም እንደሌለው ገልጸዋል። ብልጽግና አቶ ልደቱን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ወደፊትም በዚሁ የሚቀጥል እንደሚሆን ግምታቸውን አኑረዋል።
አቶ ልደቱ የሚወረውረው ድንጋይ የብልጽግናን ጀርባ እስካልመታ ድረስ ብልጽግና ዞሮ እንደማያይ ያመለከቱት አቶ በረከት፣ “አቶ ልደቱ የሚወረውረው ድንጋይ የብልጽግናን ጀርባ እንዳይመታ እሱ ያለው አሜሪካ ነው” ብለዋል።
ብአዴን
በመተካካት ነባሮቹ ሲወጡ በጥንቃቄ ባለመሰራቱ የማይረቡ አመራሮች መምጣታቸው ለድርጅቱ እዚህ ደረጃ መድረስ ዋና ምክንያት እንደሆነ አቶ በረከት አውስተዋል።
በዚሁ መሠረት ወደ አመራር የመጡት የድርጅቱ ኃላፊዎች እዛም እዚህም ተበጣጥሰው ክልሉን ለዚህ ደረጃ እንዳበቁት ከመናገር በዘለለ ብዙ ማብራሪያ አልሰጡም። አቶ በረከት ብአዴንን ለመተካት ቀደም ሲል አብን ውስጥ አመራር የነበሩ አክራሪ ብሄርተኞችን ማደራጀታቸው አሰራሩን በሚያውቁ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።
ኦህዴድ
መተካካቱን በኢህአዴግ ደረጃ ተቀብለው በማናበብ ያከናወኑ መሆናቸውን በጥንካሬ ያነሳሉ። አባ ዱላ ይመሩት የነበረው ኦህዴድ መተካካቱን በወጉ ካካሄደ በሁዋላ ክንዱ መፈርጠሙና ድርጅታዊ ኃይል ገንብቶ ሊወጣ እንደቻለ አቶ በረከት ገልጸዋል።
ጃዋር መሐመድ
አቶ በረከት ጃዋር የተረዱበትና የገለጹበት አግባብ ከዚህ ቀደም ከሚባለው ሁሉ ለየት ያለ ነው። “ተጫወቱበት፣ ተጠቀሙበት” ብለዋል። ብልጽግና ጃዋርን እንደ ሕዝብ ግንኙነት እንደተገለገለበት የገለጹት አቶ በረከት፣ ጃዋር ኝ ይህ ሳይገባው ብቻውን ሁሉንም ጉዳይ እንደተቆጣጠረ በማመን ራሱ በሰራው ተራራ ላይ ወጣ፤ በመጨረሻም ራሱን እስር ቤት እገኘ።
ከአምስት እና ስድስት ዓመት በፊት ተናጋሪው፣ በለሚዲያው፣ አስተባባሪው ጃዋር ብቻ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በረከት፣ ጃዋር ዛሬም ልክ እንደቀድሞ Dominate ተጽዕኖ የሚፈጥረው እሱ ብቻ ይመስለዋል። እወነቱ ግን ሌላ ነው ብለዋል።
“ድሮ” ይላሉ አቶ በረከት ጃዋርን ብቻ ለመስማት ስላካቸውን የሚጎረጉሩ ነበሩ። ዛሬ ግን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ተናጋሪዎች መፈጠራቸውን ጃዋር ዛሬ ድረስ የገባው እንደማይመስላቸው ” ዛሬም እዛው የድሮው ሰፈሩ ነው” በማለት ነው የገልጹት።
አቶ ኃይለማሪያ
አቶ ኃይለማሪያም በስልጣን ላይ እያሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ፓርቲያቸውን ማተናከር ሲችሉ አላደረጉትም። ሁሉን ለማስደሰት ላይ ታች ሲሉ የደቡብ ህዝቦችን ፓርቲ አፈራረሱት። አቶ በረከት ስለ ደቡብ ፓርቲ ብዙም አላሉም።
ኤርትራና አፍሪቃ ቀንድ
ኤርትራና ኢትዮጵያ ከተታኮሱ ጦርነቱ እንደቀድሞው አስመራ አፍንጫ ደርሶ አይቆምም። በረከት እንደሚሉት ኢሳያስ ፋኖንና የትግራይ ኃይሎችን ይዘው ነው ለመዋጋት የሚያስቡት። እነዚህን ኃይሎች በመያዝ ከሺህ ኪሎሜትር በላይ ለመጓዝ ሲያስብ ስልሳ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለው አሰብ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያውቁ ያውቁታል።
አቶ በርከት ጦርነቱን ማን እንደሚያሸንፍ ሳይሆን ከጦርነቱ በሁዋላ ሊሆን የሚችለውን ሲናገሩ የዩክሬንና ሩይሲያን ድርድር አንስተዋል። አሁን ላይ ሁለቱ አገራት መሬት እንዲቀያየሩ አሳብ መቅረቡን ያወሱት በረከት ቀጣዩ የኤርትራ ፖለቲካ አመራር ኤርትራን ለመረከብ የሚሰጠው መሬት እንደሚኖርና ድርድሩም ከዚህ ሊያልፍ እንደማይችል እይታቸውን አካፍለዋል።
አቶ በረከትን ያናገራቸው የትህነግ ደጋፊ የሆነው የሚዲያ ባለሙያ በአቶ በረከት ማብራሪያ ቢበሳጭም ትንታኔው ትርጉም እንደሰጠው ጠቅሶ ነው ለዲሲ ተባባሪያችን መረጃውን የሰጠው። በረከት ብዙ ጉዳይ አንስተው በተናገሩበት ጭውውት ላይ አሁን ባለው ትርምስና ስብስብ ወይም ሕብረት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንደማይወድቅም “እንቅጩን ነገሩኝ” ሲል ለተባባሪያችን ነግሮታል።
አቶ በርከት አሁን እዛም እዚህም ተጀመረ የሚባለውን ሕብረት ” ያሳዝናል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጠቅልሎ ልደቱ እጅ ይውደቅ” በሚል አዘኔታ ከመግለጽ ውጪ ያሉት ነገር የለም። አቶ ልደቱ ከርዕዮት ሚዲያ፣ አቶ ነአምን ዘለቀና ታማኝ በየነ ጋር በመሆን እየመሩት ያለው ሕብረት የኤርትራን መንግስት የሚደግፍ፣ በውል ሕዝብ ሳይፈቅድ፣ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች አመራሮች ሳይስማሙበት የተጀመረውን “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት” የተባለውን ፖለቲካ በአደባባይ የሚደግፍ መሆኑ ይታወሳል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






