አዲስ ሪፖርተር – የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በዓባያ፣ ጫሞ፣ ጣና ሀይቅ፣ ባሮ ወንዝ፣ ተከዜና በጊቤ ሰባት ውሃማ ስፍራዎች ላይ የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ትግበራ በቅርቡ እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማሪታይም ባለሥልጣን የሎጀስቲክና ትራንስፎርሜሽን ቢሮ ዳይሬክተር ወርቁ ለማ ለአዲስ ሪፖርተር እንደገለጹት፤ በአስር ዓመት የትራንስፖርት ዘርፍ መሪ የልማት ዕቅድ የውሃ ትራንስፖርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
“የውሃ ትራንስፖርት ደህንነቱ የተጠበቀና በሚፈለገው ደረጃ በሀገራችን ያለውን ለውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት አመቺ የሆኑ ወንዞችና ሐይቆች በአግባቡ በመጠቀም፤ ለሕዝብና ለጭነት ትራንስፖርት አመቺ ሆነው ይገኛሉ” ብለዋል።
የውሃ ትራንስፖርት አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ሆኖ እንዲያገለግል እንዲሁም፤ ለመዝናኛና ለቱሪስት መስህብነትም እንዲያገለግሉ ሀይቆቹ መሰረተ ልማቶች በስፋት እንደተሟላላቸውም አብራርተዋል።
ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ለጣና የውሃ ትራንስፖርት እንዲያገለግሉ ከተገዙት ሁለት ዘመናዊ ጀልባዎች መካከል፤ ሁለተኛዋ ጣናነሽ ሁለት ጀልባ ከቀናት በፊት ወደ ሀገር ቤት መግባቷን አስታውሰዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ የሚገኘው ገቢ በአግባቡ በመጠቀም የሀገር እድገትን ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ካለው የሐይቆች ሀብት አንጻር እየተገኘ ያለው ገቢ ተመጋጋቢ እንዳልሆነ የገለጹም ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች መገኘት የነበረበት ጥቅም አለመገኘቱን አያይዘው አንስተዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ በሰለጠኑ ሀገራት የውሃ ላይ ትራንስፖርት በላቀ ደረጃ እንደሚገኝ አንስተው፤ ለሀገራቱ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆን ባሻገር የስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት ተጨማሪ ገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንኑ ልምድ በመቅሰም እንደ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ቅድመ ሥራዎች ተጠናቀው፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ሀይቆች ለአገልግሎት አመቺ ተደርገው እንደተቀመጡ አብራርተዋል።





