አባት ልጁን ካልጠበቀ ማን ይጠብቅ? የሃይማኖትና የብሄር ችግር ቁጥጥሩ ላይ ጫና አሳድሯል
አዲስ ሪፖርተር – በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የገዛ ልጆቻቸውን የሚደፍሩ ወላጆች መፈጠራቸውን ተገለጸ። በአስገድዶ መድፈር ጉዳያቸው በህግ ሲታይ ጥፋተኞቹ ሃይማኖትና ብሄርን እንደመከላከያ እንደሚያቀርቡ፣ ይህም በፍትህ አካሄዱ ላይ ጉዳት ማደረሱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር አስታወቀ።
“በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከአራት እስከ ስምንት ዓመት የሆኑ ሕጻናት በቅርብ ቤተሰቦቻቸው አማካኝነት የሚፈጸምባቸው አስገድዶ መድፍር እየተባባሰ መጥቷል” ሲል የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው ከአዲስ ሪፖርተር ችግሩን አስመልክቶ በተለያዩ ወገኖች ለፖለቲካ የማዋል ፍላጎት ከሰው ልጆች መብት በላይ ገዝፎ በመታየቱ ሳቢያ ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጡ ተጠይቀው ነው።
በጎጃም ፣በጎንደር ፣በወሎ ዞኖች ውስጥ በአባታቸው ፣በወንድሞቻቸው ፣ በአጎቶቻቸው አማካኝነት የሚደፈሩ ሕጻናት ቁጥር እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
“የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ለሕጻናቱ ጥበቃና ከለላ ያደርጋሉ ተብሎ ቢታሰቡም ዋና ጥቃት አድራሽ መሆናቸው እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስጨንቆናል” ሲሉ ለአዲስ ሪፖርተር የተናገሩት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዘካርያስ ደሳለኝ ናቸው።
“በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ‘የገዛ ልጃቸውን አስገድደው የሚደፍሩ ወላጆች ተፈጥረዋል” በማለት የችግሩን ጥልቀትና ህሊናን የሚፈትን ደረጃ መደረሱን አቶ ዘካሪያስ አመልክተዋል።
ከችግሩ በላይ አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ጥቃቱን ከመከላከል ይልቅ ለጥቃት አዳራሾች ከለላ መስጠት በክልሉ የሚስተዋል ሌላ እንቅፋት እንደሆነ አቶ ዘካርያ ተናግረዋል።
ዕድሜያቸው ከ 4 እስከ 8 ዓመት ሕፃናት የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች በአባታቸው ፣በወንድማቸው ፣በአጎታቸው አማካኝነት እንደሚፈጸም በማብራራት ለወንጀሉ የሚደረገው ከለላ አሳሳቢ መሆኑን አሳይተዋል። አክለውም ሕፃናቱን የቅርብ ዘመዶቻቸው ከአደጋ ከመጠበቅና ከመከላከል ይልቅ ስጋት እየሆኑባቸው መምጣታቸው ጠቅሰዋል።
“ድርጊቱ የጦርነት ውጤት ነው ብሎ መናገር አስፈላጊ አይደለም” ያሉት አቶ ዘከርያ፣ አብዛኛው ጥቃት በቤተሰብ አማካኝነት መፈጸሙ ጦርነትን ምክኛት ለማድረግ በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ድርጊቱ በጥናት መታወቁንም አረጋግጠዋል።
የተዘረዘሩት ችፍሮች በጥናት ውጤት መታወቁን በማውሳት፣መሰል ሕገወጥ ድርጊቶች ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግር መሆኑን አመላክተዋል። በአማራ ክልል ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ፣በዜጎችና በሀገር እያደረሱ ያሉት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አመልክተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድርጊቶቹ እየተባባሱ መምጣታቸውን የሚደርሷቸው ጥናቶች እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ችፍሩን ለከመከላከል ተግዳሮት የሆነውን ጉዳይ “አሳዛኝ” ሲሉ የገለጹት ኃላፊው፣ “የአንድ ወገን ብሔር እና የፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጅ ናቸው” በሚል የሚሰጠው ስምና ፍረጃ የሚኒስቴሩን ስራ አስቸጋሪ አድርጎበታል።
ጥቃት የሚደርስባቸውን ሴቶች የመደገፍ ሥራዎች በሚሰሩበት ወቅት በፖለቲከኞች እና በሌሎች አካላት ዘንድ የአንድ ወገን ኃይማኖት፣ ብሔርና ፖለቲካ አራማጆች ናቸው ተብለን መፈረጃችን በስራችን ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል ሲሉ አቶ ዘከርያ አመልክተዋል።
በሴቶች በተለይም በህጻናት ላይ ለሚደርሰውን ጥቃት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ መስጠት እንጂ የየትኛውም ወገን አጀንዳ የማራመድ ስራን እንደማይሰራ አቶ ዘከሪያ አስታወቀዋል። ይሕን መሰሉ አግባብ ያልሆነ አመለካከት የሚያራምዱት የክልሉ ፖለቲከኞች እና ሌሎች አካላት እንደሆኑም ገልጸዋል። አክለውም በዚህ መልኩ መቀጠል ችግሩን ማባባስ እንደሆነ አመልክተዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን የሚያግዛቸው የብሔርና የፖለቲካ አመለካከታቸውን ለይቶ እንዳልሆነ መታወቅ እንዳለበት አቶ ዘካሪያ አስታውቀው “ ይልቁኑ ልጆቻችንና እህቶቻችንን ለመርዳት እንትጋ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በተቋማቸው ላይ የሚሰነዘረው አግባብ የሌለው ፍረጃ ዜጎች እምነት እንዲያጡ እንዳደረጋቸው አመልክተው፣ “አንድ ጥቃት አድራሽ ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ጉዳዩ በሕግ መታየት ሲጀመር ለእስር የተዳረገው በብሔሩ ፣በፖለቲካ አመለካከቱ ነው” በሚል በነዚሁ የተቋሙን ተአማኒነት በሚያቆሽሹ ቡድኖች ዘንድ ሀሰተኛ መረጃዎች ለሕዝቡ እንደሚሰራጩ ጠቁመዋል። በዚህም የተነሳ በፍትህ አሰጣጥ ሂደት ላይ የራሱ ተጽዕኖ ማስከተሉን አመልክተዋል።
እንዲህ ያለው ወንጀልን ፈጽሞ በብሄር፣ ኃይማኖትና በአካባቢያዊ ስሜት መከለል፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንደ ክልል ስር እንዲሰድ ትልቁ ምክንያት እንደሆነ አቶ ዘከርያ በግልጽ ተናግረዋል። ጥቃት አድራሽ ግለሰብ የየትኛውምንም ብሔር፣ፖለቲካ በመወከል ጥፋት እንደማየጠፋ በማወቅ ከመሰል ድርጊቶች መቆጠብ ያስፈልጋል እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
“በፖለቲከኞች ዘንድ መታወቅ ያለበት ነገር አሉ” አቶ ዘከሪያ “ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማንንም ወገን አጀንዳ አያራምድም መሰል ፍረጃዎችን የሚሰነዝሩ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የማይታገስ ትውልድ መፍጠር ላይ ማትኮሩ ይበጃል”
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





