በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት ተከትሎ የሚወጡ መረጃዎች የሚረብሹ ናቸው። ዛሬ ይፋ በሆነ መረጃ በክልሉ የምክርና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት፣ የተላላፊ በሽታዎች ላይ የሚደረገውን ልዩ ክትትል አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለው ችግር ሳቢያ፣ በክልሉ ኤች አይ ቪ ኤድስ ወረሽኝ ሊሆን የሚችልበት ስጋት መኖሩን አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች። ለዚህም ነውማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት ተከትሎ የሚወጡ መረጃዎች የሚረብሹ ናቸው።
ዛሬ ይፋ በሆነ መረጃ በክልሉ የምክርና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት፣ የተላላፊ በሽታዎች ላይ የሚደረገውን ልዩ ክትትል አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለው ችግር ሳቢያ፣ በክልሉ ኤች አይ ቪ ኤድስ ወረሽኝ ሊሆን የሚችልበት ስጋት መኖሩን አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች። ለዚህም ነው ችግሩ የገባቸውና ያሳሰባቸው “የሰላም ያለህ” የሚል ድምጽ እያሰሙ ነው።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመው ለአዲስ ሪፖርተር እንደተናገሩት በክልሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2024 የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው የበሽታው ስርጭት 1 ነጥብ 09 በመቶ እንደሆነ አንስተዋል። ይህም ከሀገሪቱ አማካይ ሥርጭት በዜሮ ነጥብ 19 ብልጫ እንዳለው ነው የገለጹት። በክልሉ ቫይረሱ በወረርሽኝ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የሥርጭት ምጣኔው ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ መጨመር አሳይቷል። በክልሉ 84 ወረዳዎች ደግሞ ይበልጥ ተጋላጭ ሆነው ያሉን ሲሆን ክልሉ በፋኖ ምክንያት በተከሰተው መፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት፣ የትምህርት ቤቶች መቋረጥ ለሥርጭቱ መጨመር እንደምክንያት አስቀምጠዋል።
በአማራ ክልል አሁን ላይ 173 ሺህ 442 የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያነሱት ዳይሬክተሩ ከእነዚህ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ ናቸው። ከተመረመሩት ውስጥ ደግሞ 99 በመቶ የሚሆኑት ሕክምና መጀመራቸውን ነግረውናል።
አሁንም የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ እንደተጠበቀ ሆኖ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የባሕርይ ለውጥ ሥርጸት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል። ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው የተገኘባቸውንም በመለየት ሕክምና እንዲጀምሩ እየተሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ሲደረጉ የነበሩ ድጋፎች መቀነስ አንዱ ችግር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለከፋ ችግር ዳርጓል ነው ያሉት።
በክልሉ በፋኖ ምክንያት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመመርመሪያ ኪቶችን እና መድሃኒቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል።እንዲሁም የሕክምና ተቋማት መውደም ፣የጤና ባለሞያዎችን ፖለቲካ ሽፋን በመሰጠት ማገትና መግደል ለስርጭቱ መጨመር ግብዓት መሆኑን ጠቁመዋል።በነዚህ በመሰል መንስኤዎች ሳቢያ በአማራ ቫየረሱ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ መሸጋገሩ አይቀርም ሲሉ አሳስበዋል።
“ኤች አይ ቪ አሁንም የተዳፈነ እሳት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመፍታት በክልሉ የተከሰተውን የሰላም ችግር በመቅረፍ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሮ እንዲኖሩ ቢደረግ ቫይረሱን የመቀነስ እድል እንደሚኖር ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሚሠራው ሥራ ባለፈ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሁሉም ማኅበረሰብ ኀላፊነትን በመውሰድ ድርሻን መወጣት ያስፈልጋል ተብሏል።






