ሀጎስ መስፍን ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በፊትና በሁዋላ ሁለት መልክ ያለው “ሽፍታ” ነው። ይህ አንድ ክፍለ ጦር ወይም ከሺህ በላይ ጭፍራ እንዳለው የሚነገርለት ሽፍታ መቶ ሰባ የሚጠጉ አመራሮቹን ይዞ እንጁን መስጠቱ እያነታረከ ነው።
የጠለምት ወይም ጸለምት ነዋሪ እንደሆነ የሚታወቀው ሀጎስ በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ ነጻ አውጪ ሰራዊት ጋር እስከተቀላቀለበት ቀን ድረስ ሽፍታ ነበር። በሽፍትነቱም ከብት ሲዘረፍ ተዋግቶ በማስመለስ ሲሶውን ይወስድ ነበር። ወርቅ ከሚቆፍሩት ዘንዳም እየሂደ ተዋግቶ ያስገብር ነበር።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተቋጨው ጦርነት ሙሉ ጭፍራውን ይዞ ትህነግን ተቀላቅሎ ሲዋጋ የነበረው ሀጎስ ” ተከዜን አልሻገርም” ብሎ ወደፊት መራመዱን እስካቆመ ድረስም የጄነራል ምግበይ ጦር ስር ጭፍራውን ይዞ ሲዋጋ ነበር። ተከዜን መሻገር እንደማይፈልግ አስታውቆ የምግበን ጦር ከነጭፍራው የተለየው ሀጎስ በዛው ከትህነግ ጋር መለያየቱን የሚያውቁት ያስረዳሉ።
ሀሃጎስ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በሁዋላ ወደ ቀድሞ ሽፍትነቱ በመመለስ ከቀድሞ አለቃው ጄነራል ምግበይ ሃይሎች ጋር ሁለት ጊዜ ገጥሞ ጉዳት አድርሷል። በቅርብ የሚያውቁት እንደሚሉት ሀጎስ ከአንድ ሺህ በላይ ጭፍራ ያለው፣ ወርቅ የሚያወጡትን የትህነግ ሰራዊት አመራሮችን ተኩስ በመክፈት እየገጠመው ያዘጋጁትን ወርቅ ሲቀማ የኖረ ጦረኛ ነው።
በወርቅ ቁፍሮ ላይ የተሰማሩትን ከፍተኛ መኮንኖችን በጦርነት እያስገበረ ሲኖር የነበረው ሀጎስ ነው መቶ ሰባ አመራር የሚላቸውን አባላቱን ይዞ ለአገር መከላከያ እጁን የሰጠው። ይህ ዜና እንደተሰማ የትግራይ አክቲቪስት መሆናቸውን የሚናገሩ “በአያያዝ ጉድለት ከጃችን ወጣ” በማለት ንትርክ ላይ ናቸው። አንድንዶቹም በብስጭት “ዘራፊ” እያልይ እየሰደቡት ነው።
“የትህነግ ታጣቂ” የሚሉት ደግሞ ሀጎስ መስፍን እጅ ቢሰጥም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ቢኖሩም እሱ ግን በወርቅ ዘረፋ ውስጥ እንዳልተሳተፈ ይናገራል። ይህንኑ አስመልክቶ ቃለ ምልልስ እንደሚያደርግ ቃለ መግባቱ ተሰምቷል።
ከተለያዩ ወገኖች የተለያየ አስተያየትና መረጃ እየወጣበት ያለው ሃጎስ በምዕራብ ጠለምት ዞን ማይጠብሪ ወረዳ ማይተክሊት ቀበሌ እጁን ለአገር መከላከያ ሰራዊት መስጠቱ ይፋ ሆኗል። ዜናውን ያረጋገጠው የአገር መከላከያ ሃጎስ ማይጠብሪ ከተማ ደጀን አባይ ሆቴል ማረፉን አስታውቋል።
ተቸካይ ክላሽ ስድስት፣ብሬን ኮሮኖፈ አንድ፣ስናይፐር አንድ፣ክላሽ መቶ ስልሳ ሁለት፣ሽጉጥ (እስታር) ሶስት። ይዞ ለጊዜው እጅ የሰጠው ሃጎስ በጫካ ያለው ቀሪ ኃይሉን እንደሚያስከትል አዲስ ሪፖርተር ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ አካላት ሰምታለች። መረጃው ስጋት የሆነባቸው የትህነግ ደጋፊዎች ሃጎስ አዲስ እየተገነባ ያለውን የትግራይ ሰላም ኃይሎችን ሊቀላቀል የመቻሉ ጉዳይ ነው።
ሃጎስን ካረፈበት በስልክ ያነጋገሩ ለአዲስ ሪፖርተር እንዳሉት ከሆነ ሃጎስ የሚመራው ጭፍራ ከሺህ በላይ ነው። በሚታወቀው የትህነግ ታጣቂዎች አደረጃጀት አንድ ክፍለ ጦር ነው። ይህ ኃይል ሻለቃ አዲስ ከሚመሩትና በማይጠብሪ ከሰፈረው የሰላም ኃይሎች ጋር እንደሚቀላቀል ፍንጭ ሰምተዋል።
ሃጎስን ጠንቅቀው የሚያውቁት በጦርነቱ ወቅት ከትህነግ ጋር ሆኖ በራያ በኩልም ተዋግቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ክልል እንዳባጉና ወረዳ ራህዋ ቀበሌ በሚገኘው የወርቅ ማውጫ ቦታ በህገ ወጥ መንገድ ሶስት የወርቅ ማጣሪያ ማሽን ተክሎ ይሰራ ነበር። እሱ ራሱን ከዘረፋና ከወርቅ ንግድ ቢያርቅም በርካቶች አይቀበሉትም።
እጅ በምስጠቱ የተናደዱ “ይህ ግለሰብ ወርቅ ማውጣቱን እንዲያቆም የትግራይ ፖሊስ ሲያግደው አንድ ፖሊስና ሁለት ሲቪሎችን በመግደል ከዚያም ከመቶ ሃያ ታጣቂዎች ጋር በመሆን ሀራ መሬት ካሉ የትህነግ ተገንጣይ ኃይሎች ጋር ተቀላቅሏል” ሲሉ ይከሱታል።
“ሀጎስ መስፍን እጅ ለመስጠት የመረጠው በራሱ ምርጫና ዕምነት ሳይሆን የግል ጥቅሙ በመነካቱ እና የትህነግ መሪዎችን ቅር በማሰኘት የብሽሽቅ ፖለቲካ ለመጫወት ነው” ሲሉ የሚያጣጥሉትም አሉ። መረጃውን በግምቶች ደረጃ የሚያቀርቡም አልታጡም።
ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚወጣው ጥቆማ ግን “አንዳንድ የደህንነት ባለሙያዎች ግለሰቡ እጁን የሰጠው ሌላ አማራጭ በማጣቱ ቢሆንም ለወደፊት ትህነግ ለምትነኩሰው ትንኮሳ ዓይነተኛ ሚና ለመወጣት እና በመንግስት በኩል አመኔታ ለማግኘት ታስቦበት ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት” በሚል የሰጡት ምክር ነው።
ግለሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው የስለላ ስራ ለመስራት የተላከ ወይም የተዘጋጀ የትህነግ መልዕክተኛ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግበት በግል የተናገሩም አሉ።
ሃጎስን አስመልክቶ የተለያዩ መረጃዎች ቢወጡም፣ እንጁን ሲሰጠው የተረከበው የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የአካባቢው አስተዳደር ዝርዝር የሰጡት መረጃ የለም። ትህነግም ቢሆን በደጋፊ አክቲቪስቶቹ አማካይነት በቁጭት እሱን ማጥYአት እንደሌለባቸው ከማስታወቃቸው በቀር በኦፊሳል ያለው ነገር የለም።
ትህነግ ሰሞኑን በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር በኩል ባወጣው መግለጫ የትግራይ ህጋዊ ክልል ነው በሚላቸው አወዛጋቢ አካባቢዎች ድርድር እንደማያደርግ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ሃጎስ አወዛጋቢ ከሚባሉት አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ማይጠብሪ ተወላጅ ነው።
አዲስ ሪፖርተር
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






