ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከመደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚለየው ሃገራቱ በህልውና እና በብሄራዊ ጥቅም ላይ በሚኖራቸው ቁርጠኝነት ነው። ኢትዮጵያ እና ህንድ የተፈራረሙት የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ሀገራቱ አሁን ካሉበት የቀጠናዊ እና የዓለም አቀፍ ጫና አንጻር አንዳቸው ለሌላው “አስፈላጊ” መሆናቸውን ያረጋገጡበት ነው። ለኢትዮጵያ ህንድን የመሰለ የBRICS አባል እና የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃያል ሃገር በስትራቴጂካዊ ደረጃ ማግኘቷ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች ቀጠናዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ “ጋሻ” እንደማግኘት ይቆጠራል።
- አዲስ ሪፖርተር – ሕንድ በኢትዮጵያውን ዘንድ ልዩ ቦታ አላት። በሕንድ መምህር ያልተማረ፣ ኩቺ ኩቺ ሆታሄን ያላንጎራጎረ፣ በማዘር ኢንዲያ አሳዛኝ ፊልም እምባ ያልተራጨ፣ በማህሙዴ ቀልዶች ፈገግ ያላለ፣ በደብተሩ ሽፋን ላይ የሕንድ ፊልም አክተሮችን ምስል ያልለጠፈ ኢትዮጵያዊ ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል፣ በተለይ ለሰማንያዎቹና ለዘጠናዎቹ ትውልድ። በልጅነት የትዝታ ማህደር ውስጥ ታትመው ቀርተዋል። የሰሞኑ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት ይህን ትዝታችን እንደቀሰቀሰው እሙን ነው። ኢትዮጵያ ለሕንድ መንግስትና ሕዝብ ያላትን ክብር የገለፀችበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነበር። ብሄራዊ ኩራትን የመለሰ ነበር። በሃገራችንና መሪዎቿ ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደረገ አንዳች የኩራትና የዜግነት ክብር ስሜትን ቀስቃሽ ነበር። እንኳንም ኢትዮጵያዊ ሆንኩ የሚያሰኝ።
የሕንድ ጠቅላይ ሚንስቴር በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” ያሸጋገረ ነበር። በመከላከያ፣ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተፈረሙት ስምምነቶች ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ እና በህንድ ውቅያኖስ ቀጠና ላይ የሚኖረውን የጂኦፓለቲካ አንድምታ ሰፊ ነው። ወደ አንድመታዎቹ ከማለፋችን በፊት ስትራቴጂክ አጋርነት ምን ማለት እንደሆነ ገልፅ ማድረጉ ሙሉ መልዕክት ስለሚሰጥ ከአለም አቀፍ ግንኙነት አስተምህሮ አንጻር ትርጉሙን ማየት ተገቢ ነው።
ስትራቴጂካዊ አጋርነት (Strategic Partnership) በሁለት ሀገራት መካከል የሚደረግ፣ ከተራ የንግድ ወይም ጊዜያዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከፍ ያለ እና የረጅም ጊዜ የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ጥብቅ ጥምረት ነው። ታዋቂው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ቶማስ ዊልኪንስ (Thomas Wilkins) “Strategic Partnerships: An Emerging Phenomenon in International Relations” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ እንደሚገልጸው፤ ይህ አጋርነት ከመደበኛ ወታደራዊ ስምምነት (Alliance) ለየት ያለና ይበልጥ ተለዋዋጭ የሆነ፣ ነገር ግን በጋራ ስጋቶችና ራዕዮች ላይ የተመሰረተ ትብብር ነው። እንደ ዊልኪንስ ገለጻ፣ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ሀገራቱ በህልውናቸው እና በብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመቆም የሚገቡት ቃል ኪዳን ነው። ይህ ግንኙነት በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ ይቆማል፦ አንደኛው የጋራ ራዕይ ሲሆን፣ ሀገራቱ በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። ሁለተኛው ከፍተኛ መተማመን ነው፤ ይህም ሚስጥራዊ የሆኑ የመከላከያ፣ የደህንነት እና የላቁ የቴክኖሎጂ መረጃዎችን እስከ መጋራት የሚደርስ ጥልቅ ትስስር ይፈጥራል። ሦስተኛውና ዋነኛው ደግሞ ሁለገብነት (Multidimensionality) ሲሆን፣ ግንኙነቱ በአንድ ዘርፍ ሳይገደብ ፖለቲካን፣ መከላከያን፣ ሳይንስን፣ ኢኮኖሚንና ባህልን አቀናጅቶ የያዘ ዘላቂ ትስስር ነው።
ከ“ጓደኝነት” ወደ “ስትራቴጂካዊ ጥምረት” ሽግግር
ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከመደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚለየው ሃገራቱ በህልውና እና በብሄራዊ ጥቅም ላይ በሚኖራቸው ቁርጠኝነት ነው። ኢትዮጵያ እና ህንድ የተፈራረሙት የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ሀገራቱ አሁን ካሉበት የቀጠናዊ እና የዓለም አቀፍ ጫና አንጻር አንዳቸው ለሌላው “አስፈላጊ” መሆናቸውን ያረጋገጡበት ነው። ለኢትዮጵያ ህንድን የመሰለ የBRICS አባል እና የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃያል ሃገር በስትራቴጂካዊ ደረጃ ማግኘቷ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች ቀጠናዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ “ጋሻ” እንደማግኘት ይቆጠራል።
የጋራ ራዕይ፡ በደቡባዊ ዓለም የሚኖራቸው ሚና
ሁለቱም ሀገራት የ”ግሎባል ሳውዝ” (Global South) ድምጽ የመሆን የጋራ ራዕይ አላቸው። ህንድ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን መሪነት ስትረከብ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል በመሆኗ፣ ይህ አጋርነት በዓለም አቀፍ ተቋማት (እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት) ውስጥ የተዛባውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል የሚያስችል “የጋራ አቋም” እንዲይዙ ያደርጋቸዋል።
ከፀጥታ አጋርነት እስከን ቀጠናዊ ተሰሚነት

በኢትዮጵያና በህንድ መካከል የተፈረመው የመከላከያ ስምምነት ከሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ባለፈ፣ የቀጠናውን የጂኦ-ስትራቴጂካዊ የኃይል ሚዛን የሚቀይር ትልቅ አንድምታ አለው። ይህ ትብብር የህንድን “SAGAR” (Security and Growth for All in the Region) የተሰኘውን የውጭ ፖሊሲ ራዕይ በቀጥታ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ትርጉሙም በህንድ ውቅያኖስና በአካባቢው ያሉ ሀገራት ደህንነትና እድገት የተሳሰረ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ለመገንባትና በቀጠናው ያላትን ተጽዕኖ ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት ህንድ በስልጠና እና በቴክኒክ ድጋፍ ለማገዝ መወሰኗ ለሁለቱም ሀገራት ስልታዊ ፋይዳ አለው። ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ የሚኖራትን ወታደራዊ ተሰሚነት ከፍ የሚያደርገው ሲሆን፣ ለህንድ ደግሞ በአለም አቀፍ ንግድና ደህንነት ረገድ ወሳኝ በሆነው በዚህ መስመር ላይ ታማኝና ጠንካራ ስልታዊ ወዳጅ እንድታገኝ ያስችላታል።
የዚህ አጋርነት ሌላው ጥልቅ አንድምታ ከሽብርተኝነት መከላከልና ከቀጠናዊ መረጋጋት ጋር የተያያዘ ነው። ሁለቱም ሀገራት ከአክራሪነትና ከድንበር ተሻጋሪ ሽብርተኝነት የሚመነጩ የደህንነት ስጋቶች ያሉባቸው በመሆኑ፣ በመረጃ ልውውጥ (Intelligence Sharing) እና በወታደራዊ አቅም ግንባታ ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸው በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የፀጥታ ክፍተት ለመሙላት ይረዳል። ይህ ትብብር ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት የምታደርገውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በቴክኖሎጂ እንድታጠናክር የሚያግዛት ሲሆን፣ ህንድ ደግሞ ከአፍሪካ ቀንድ የሚነሱ ስጋቶች ወደ ህንድ ውቅያኖስ እንዳይሻገሩ “የቅድመ መከላከያ ቀለበት” ለመፍጠር ያስችላታል። ባጭሩ፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያን የቀጠናው የፀጥታ ምሶሶነቷን የሚያጠናክርላት ሲሆን፣ ህንድን ደግሞ በምዕራባዊው የህንድ ውቅያኖስ ክፍል ተሰሚነቷን የምታረጋግጥበትን የፖለቲካና የደህንነት ዋስትና ይሰጣታል።
ከአንድ ወገን የኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ
በኢትዮጵያና በህንድ መካከል የተደረገው አዲሱ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ አጋርነት በተለይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅር ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን፣ በተለይም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ረገድ በቻይና ላይ ያላትን ከፍተኛ ጥገኝነት ለመቀነስ አማራጭ የኃይል ማዕከል ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ይደግፍላታል። የህንድ ባለሃብቶች ከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ባለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረጉ ቢሆንም ይህ ስምምነት ግንኙነቱን ከመደበኛ የሸቀጥ ልውውጥ ወደ ጥልቅ የኢኮኖሚ ትስስር አሸጋግሮታል። የዚህ አንድምታ ኢትዮጵያ የአቅርቦት ሰንሰለቷን በማባዛት(Supply Chain Diversification) ፣ ከአንድ ሀገር ብቻ ከሚመነጭ የብድርና የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ እንድትላቀቅና በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ላይ ያላትን የመደራደር አቅም ከፍ እንድታደርግ ያስችላታል። ይህ “የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሚዛን” ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅምና ለኢኮኖሚ ነፃነቷ ወሳኝ የሆነ የስትራቴጂ ለውጥ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በተጨማሪም፣ ህንድ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ፓርኮች የምርቶቿ ወደ መላው አፍሪካ ማሸጋገሪያ በር (Gateway) አድርጋ ለመጠቀም ማቀዷ ለኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል። የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መመረት የሚችሉ ምርቶችን እዚሁ በማምረት ለአህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ለማቅረብ ማሰባቸው፣ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘቱም በላይ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ይህም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል (Logistics Hub) እንድትሆን የሚያደርጋት ሲሆን፣ የህንድን የቴክኖሎጂና የሥራ ፈጠራ ልምድ ወደ ሃገራችን በማስገባት የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ያፋጥነዋል።

ቴክኖሎጂ፡ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድል
በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል የተደረገው የቴክኖሎጂ ስምምነት “የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድል” ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በቀንዱ የሚኖራትን የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል። ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማነቱ የተረጋገጠለትን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት (UPI) እና የተቀናጀ የዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት (Digital Public Infrastructure) ልምዷን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መወሰኗ፣ የሃገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ ከማዘመኑም በላይ የኢኮኖሚ ተደራሽነትን ያሰፋል። ይህም ኢትዮጵያ አሁን ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እያከናወነች ያለችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን 2030 ስኬታማነትን ይጨምራል።
ከዚህም ባለፈ፣ ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከጂኦፖለቲካዊ አንፃር “የስጋት ቅነሳ” (De-risking) ስልትን በተግባር የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ በዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ በቻይና ቴክኖሎጂ ላይ ያላትን ከፍተኛ ጥገኝነት በመቀነስ፣ አማራጭ የአቅርቦት ምንጮችን እንድታገኝ ያስችላታል። ይህም ሀገሪቱ ወሳኝ የሆኑ የመረጃና የቴክኖሎጂ ሥርዓቶቿ በአንድ ወገን የበላይነት ስር እንዳይወድቁ የዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚረዳት ስልታዊ እርምጃ ነው። ህንድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ያላትን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነቷን እንድታጠናክርና በዘመናዊ ሶፍትዌር ልማት ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንድታፈራ የምታደርገው ድጋፍ፣ ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን ሰፊ በር ይከፍትላታል።

በአጠቃላይ የናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት ህንድ በአፍሪካ ያላትን “ለስላሳ ኃይል” (Soft Power) ወደ “ጠንካራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት” (Strategic Partnership) ማሳደጓን ያሳየ ነው። ስትራቴጂካዊ አጋርነቱ በወረቀት ላይ የሰፈረ ስምምነት ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱ ሀገራት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለሚገጥሟቸው ጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎች በጋራ ለመቆም የገቡት ተግባራዊ ቃል ኪዳን ነው። ኢትዮጵያ በታላላቅ ሃገራት መካከል የሚደረገውን የፉክክር ፖለቲካ ለሃገራዊ ጥቅሟ እንዲውል የማድረግ ብልህነት የታየበት ስኬታማ የዲፕሎማሲ እርምጃ ነው። ይህ አጋርነት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የበላይነት የሚያጠናክርላት ሲሆን፣ ለህንድ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስልታዊ ተፅዕኖ የሚያረጋግጥላት ነው።
ለጥቆማ ያህል
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያን ጉብኝት አስመልክቶ የህንድ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያሳዩትን አቀባበል ልዩ፣ ተምሳሌታዊ እና በዲፕሎማሲያዊ አነጋገር ጥልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ያለ አንዳች መዥጎርጎር ነው በተመሳሳይ ቃናና ከፍታ የዘገቡት። የብሄራዊ አጀንዳቸው ባሪያና መሆናቸውንም አሳይተዋል።
የህንድ መገናኛ ብዙሃን ህንድ ከጉብኝቱ የምታገኘውን ጥቅም በተለይም በስትራቴጂካዊ ደረጃ በመዘርዘር ግንኙነቱን አጉልተው አሳይተዋል። የጉብኝቱን ክብደት እና ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ዋጋ በቅጡ በመረዳት ሲተነትኑ አይተናል። በየዘገባዎቻቸው መካከል ኢትዮን ያጎሉበትና ያከበሩበት መጠን ከአገር ውስጥ መገናኛዎቻችን የሚበልጥ ሆኗል። አቀባበሉን የሚያሳየውን ቪዲዮ በዓለም ሲለቁት የከበረችው ኢትዮጵያ ናት!!
Website፡ https://addisreporter.com/
Email፡ info@addisreporter.com
Telegram፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
Phone no ፡ +251981866434 / +251116393393






