አዲስ ሪፓርተር (አዲስ አበባ ) — የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ ኢትዮጵያ በጋዛ ሰርጥ ለሚሰማራው አዲስ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል የሰራዊት አባላትን እንድታዋጣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ።
እንደ “ዘ ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል” ዘገባ ከሆነ፣ ማርኮ ሩቢዮ ይህንን ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው። ጥያቄው የቀረበው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የጋዛ ሰላም ዕቅድ ተፈጻሚ ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረት አካል መሆኑ ተገልጿል።
የዕቅዱ ዝርዝር
የፕሬዝዳንት ትራምፕ የ20 ነጥብ የጋዛ ዕቅድ፣ ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው ጦርነት ክፉኛ ለተጎዳችው ጋዛ የሽግግር ወቅት የሚቆይ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል እንዲቋቋም ጥሪ ያደርጋል። ይህ ኃይል፦ በአካባቢው መልሶ ግንባታ እንዲፋጠን ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥራዎችን ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም የሐማስን ታጣቂ ቡድን ትጥቅ የማስፈታት ተልዕኮ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የምልመላ ተግዳሮቶች
ዘገባው አክሎ እንደገለጸው፣ ዋሽንግተን ለዚህ የፀጥታ ኃይል የሚሳተፉ ሀገራትን ለማግኘት ከፍተኛ ፈተና እየገጠማት ነው። ብዙ ሀገራት የሐማስን ታጣቂዎች ትጥቅ የማስፈታት ተልዕኮ “አደገኛ ነው” በሚል ስጋት ለመሳተፍ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ትራምፕ ለኃይሉ የሚያስፈልጉ ወታደሮችን ለማሰባሰብ በሚጥሩበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ከተጠየቁ ሀገራት መካከል አንዷ ሆናለች።
ለምን ኢትዮጵያ ተመረጠች?
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያላት የረጅም ጊዜ ልምድ እና በምስራቅ አፍሪካ ያላት ወታደራዊ ተሰሚነት ለምርጫው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል።
እስካሁን ባለው መረጃ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአሜሪካው ጥያቄ የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም። ጉዳዩን አስመልክቶ ከሁለቱ ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አሜሪካ ሌሎች ሀገራትንም የማሳመን ሥራዋን ቀጥላለች።
መልካም አጋጣሚና ስጋት
አዲስ ሪፓርተር ይህ ሰላም ማስከበር ለኢትዮጵያ የሚያስገኝላትን መልካም አጋጣሚና ስጋት በተመለከተ ጥያቄ ያረበችላቸው የአዲስ አበባ የዩንቨርስቲ የውጭ ግንኙነት መምህር እንደገለፁት ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ውስጥ መሳተፏ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረትና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርላት ሲሆን፣ በተያያዥነትም ተልዕኮው በአብዛኛው በአሜሪካና በአረብ ሀገራት የሚደገፍ በመሆኑ ለሀገሪቱ ጠቃሚ የውጭ ምንዛሬ ምንጭና የፋይናንስ ድጋፍ በማስገኘት ረገድ የጎላ የኢኮኖሚ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
Website፡ https://addisreporter.com/
Email፡ info@addisreporter.com
Telegram፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
Phone no ፡ +251981866434 / +251116393393






