አዲስ ሪፖርተር – ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ብሎ የሚጠራው ቡድን ዋና መርሁ “ማበስበስ” እንደሆነ ተገለጸ። በቅርቡ ለአርሚ አዛዦች በሞሮኮ የንግድና መኖሪያ ቤት የተገዛላቸው በዚሁ መርሁ መነሻ እንደሆነ ተመልክቷል።
በሞሮኮ ንብረት የተገዛላቸውን የትግራይ ሰራዊት አርሚ አዛዦች ስም ዘርዝረው መረጃ የላኩ ክፍሎች እንዳሉት፣ “የትህነግ ርዕዮተዓለም ማበስበስ ነው” ነው። ከህዝብና ከአገር በሚዘረፍ ሃብት ወታደራዊ አመራሮችን ታዛዥ ለማድረግ በውጭ አገር ንብረት እንዲያፈሩ ይደረጋል።
ትህነግ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ አመራር ያሉትን በሌብነት ሆን ብሎ ይነክራቸው እንደነበር ያስታወሱት እነዚሁ መረጃውን የላኩት ክፍሎች “ይህ የሚሆነው አመራሩ ለትህነግ ጸጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ፣ እተነፍሳለሁ ካለ የሚወነጀልበት ፋይል ለማዘጋጀት ነው” ሲሉ “ማበስበስ” ስለሚባለው ስልታቸው አስፈላጊነት አመልክተዋል።
አቶ አባተ ኪሾ በዚሁ ክስ ተመስርቶባቸው እስር ቤት ከቆዩ በሁዋላ ትህነግ በየክልሉ ኃላፊዎችን ሆን ብለው ሙስና ውስጥ የሚዘፍቁ ሰዎችን ይመድብ እንደነበር ማናገራቸው ይታወሳል።
አሁን ወርቅ ነጋዴ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞው “የሰው ልጆች መብት ተሟጋች” አቶ ኦባንግ ሜቶም በአንድ ወቅት ጎልጉል ከተባለ የድረ ገጽ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት “ኢህአዴግን በበላይነት የሚመራው ትህነግ ባለስልጣናቱን ሆን ብለው በሙስና የሚያጠምዱ ስኳድ አለው። በዚሁ ስኳድ አማካይነት ሁሉእንም አነካከተዋቸው አፋቸውን አዘግተዋቸዋል” ብለው ነበር።
ይህ ትህነግ እንደ ርዕዮተዓለም ይዞታል በሚል የሚገለጸው “ማበስበስ” በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክብረ ነክ በሆኑ ተግባራት በማጥመድና በማሳተፍም ይገለጽ እንደነበር በድንገት ከፖለቲካው ድምጻቸውን በማጥፋት ራሳቸውን የሰወሩትን ምሳሌ በማድረግ የሚናገሩ አሉ።
በመጠጥ በማስከር፣ የተለያዩ ቪዲዮዎች በማቅረጽ የሚፈታተኗቸውን ፖለቲከኞች አፍ እንዳዘጉ የሚናገሩ፣ እንዲህ ያሉ ወንጀሎች ሊጠኑና ሊጋለጡ የሚገባቸው ናቸው።
“በትግራይ በዚህ ደረጃ ወነጀልና ግፍ ተፈጽሞ እያለ ለምን ለውጥ ሊካሄድ አላቻለም” በሚል በርካቶች የሚያነሱትን ጥያቄ አስመልክቶ አዲስ ሪፖርተር ጥያቄ የሚያቀርብላቸው በክልሉ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው “ትግራይ በሌብነትና በቤተሰብ መዋቅር በተሳሰሩ ቡድኖች እጅ ስር ወድቃለች” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። ይህ ከሁሉም የተቃዋሚ አሰላለፍ ውስጥ ካሉ ፖለቲከኞች የሚሰማ ምክንያት ነው።
በዚህ መነሻ የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ዲሲ ተባባሪ አሁን ላይ ትግራይን እየመራ ካለው የትህነግ መዋቅር ጋር ጥብቅ ቁርጭት ካላቸው የውጭ አገር ክንፍ ቡድን አባላት ባገኘው መረጃ በሞሮኮ ንብረት የተገዛላቸውን የአርሚ አዛዦች ስም ዝርዝር አግኝቷል።
ተባባሪያችን “ይበቃል” የሚል አቋም ከያዙ አንድ የቡድኑ የውጭ ድጋፍ ሰጪ እንዳገኘውና በተለያዩ መንገዶች እንዳጣራው ገልጾ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፣ በስም ለተዘረዘሩት በሞሮኮ ሃብትና ንብረት የገዙት የሞንጆሪኖ ወንድም አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሄር ናቸው።
አሁን ላይ አዲስ የተጀመረውን የሻዕቢያና የትህነግ ጽምዶ ወይም ቅንጅት በማስተባበርና ተግባራዊ እንዲሆን በማስቻል ግንባር ቀደም ሆነው የተንቀሳቀሱት አቶ ዳዊት፣ ንብረቱን የገዙላቸው በወርቅ ሽያጭ ከሚገኘው ሃብት እንደሆነ መረጃውን የሰጡት አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት አሁን ትግራይን እያስተዳደሩ ያሉት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ የድቡብ ግንባር አዛዥ የሆኑት ጆን መዲዲ፣ የሰሜን ግንባር አዛዥ ምግበይ፣ ፍስሃ ማንጁስ የትግራይ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ፣የአርሚ 60 ሚካናይዝድ ኃይል አዛዥ ወዲ እምበይተይ በሞሮኮ ንበረት የተገዛላቸው ናቸው።
እነዚህ መኮንኖች በትግራይ በተለያዩ አካባቢዎች የወርቅ ማውጪያ እንዳላቸው ፈቃዱን ከሚሰጡት አካላትና ከስር በሚዘርዘሩት የወርቅ ማውጪያ በሽርክና ከሚሰሩ መረጃ በማሰባሰብ የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ እንዳለው ሓራ መሬት ካሉት በስተቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ የሰራዊት አዛዦች ወርቅ ዝወረፋ ላይ ተሰማርተዋል። ወሩንም በኤርትራ በኩል በማውጣት የሚሸጡላቸው አቶ ዳዊት የሚባሉት የሞንጆሪኖ ወንድም ናቸው።
ጄኔራል ምግበይ በእህታቸው ልጆችና ከዚህ በፊት ሚቲከ ውስጥ ይሰሩ ከነበሩ ጋር በመሆን በአስገደ ወረዳ ጣብያ ሕጻጸ የሚገኘውን የወርቅ ስፍራ ባለቤት ናቸው። ሕጻጻ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ተፈናቃዮች የችግር ጣር ድምጽ የሚያሰሙባት ስፋ ናት።
ተክላይና ዓለም ገብረዋህድ ደግሞ በጽንብላ ወረዳ ጣቢያ አምደ ማሪያም የተወሰኑ ነጋዴዎች ጋር በአንድነት ወርቅ እያመረቱ መሆኑን ተባባሪያችን አመልክቷል።
ዓለም ገብረዋህድና ሞንጆሪኖ በማዕከላዊ አድያቦ፣ ጣቢያ ዛግር እና በአዴት ወረዳ ጣቢያ ደብረ ገነት ከሚቴክ ከተባረሩ ጋር ሆነው በማህበር ስም ወርቅ እያመረቱ ነው። ስሙ ወረዒ የሽርክና ማህበር ሲሆን ሕዝብ በይፋ ንብረትነቱ የማን እንደሆነ የሚያውቀው ነው።
ጀነራል ድንኩል እና ጄነራል ህንጻ ይጭላ ወረዳ ላይ ሳፒር / sapphire የከበረ ድንጋይ እንደሚያመርቱ ያስታወቁ እንዳሉት እነዚህ የጦር መኮንኖች የአንድ ቤተሰብ አባል ከመሆናቸው በዘለለ፣ በሌብነት መዋቅር ውስጥ ገብተው እንዲበሰብሱ ስለተደረገ ጥቅማቸው እንጂ የትግራይ ህዝብ ስቃይ አይታያቸውም። ለውጥ ቢመጣ ስለሚጠይቁ “ማበስበስ” በሚባለው መርህ ተጠምቀው “የማበስበስ ርዕዮተ ዓለም ጠባቂና አምላኪ ሆነዋል” ሲሉ መረጃውን የሰጡ አመልክተዋል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






