አዲስ ሪፖርተር – “የትግራይ ሉዓላዊነት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። የትግራይ ሉዓላዊነት የሪፈረንደም ጉዳይ አይደለም” በማለት የትግራ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አማኑኤል አሰፋ መናገራቸው፣ አፈጻጸሙ ወደ ጉልበት ማምራቱን የሚያሳይ እንደሆነ ተመለከተ። ከትግራይ ኃይሎች ጋር ጥምረት የፈጠሩት የፋኖ ታጣቂዎች አቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ እያነጋገረ መሆኑ ተሰማ።
ሰሞኑን የትህነግ ከፍተኛ አመራርና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አማኑኤል አሰፋ ከድርጅቱ ልሳን ‘ወይን’ ሚድያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ያነሷቸው ነጥቦች በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ አዲስ የሥጋት አደጋ መደቀኑ አሳሳቢ እንደሆነ ያመለከቱ መንግስት ዝምታውን ሰብሮ በይፋ ለሕዝብ ምን እየሆነ እንደሆነ በግልጽ ሊያስታውቅ እንደሚገባም የጠቆሙ አሉ።
አቶ አማኑኤል “የትግራይ ሉዓላዊነት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። የትግራይ ሉዓላዊነት የሪፈረንደም ጉዳይ አይደለም” ማለታቸው፣ የፖለቲካ ተንታኞች ድርጅቱ ካለፈው ጦርነት በኋላ ስትራቴጂውን እንደቀየረ ማሳያ ነው በማለት እየገለጹት ይገኛሉ። ድርጅቱ መንግስት ሲመራ ጭምር በተገንጣይ ስም የጸናበት ምክንያት ምን እንደነበር ያሳየና፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠው በህግ የማይታቀብ ስልጣንም የዓላማው ማስጠበቂያ እንደሆነበር በርካቶች “ለዚህ ነበር” በማለት እየገለጹት ነው።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ትህነግ ከዚህ ቀደም የነበረውን “አዲስ አበባ ገብቶ ማዕከላዊ መንግሥቱን የመቆጣጠር” ፍላጎት ትቶ፣ አሁን ትኩረቱን የትግራይን ‘ሉዓላዊነት’ በተግባር ወደ ማረጋገጥ (De facto state) አዙሯል። ለዚህም ዓላማው ማስፈጸሚያ ከፋኖ ውስን ክፍሎች ጋር ህብረት ፈጥሯል።
ይህ አዲስ አካሄድ ደግሞ በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትና በሕዝበ ውሳኔ (Referendum) ከሚመጣ ነፃነት ይልቅ፣ በጉልበትና በወታደራዊ የበላይነት የሚረጋገጥ የራስ ገዝነት ጥያቄ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል።
ለዚህ ስትራቴጂ መሳካት ደግሞ ወልቃይትና ራያን በኃይል ማስመለስ እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል። ተንታኞች እንደሚጠቁሙት፣ ትህነግ እነዚህን አካባቢዎች ዳግም መቆጣጠር የሚፈልገው ለግዛት ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ አገራት (በተለይም ሱዳን) የሚያደርሰውን ስትራቴጅክ መንገድ ለመክፈትና የኢኮኖሚና የደህንነት ዋስትናውን ለማረጋገጥ ነው።
ይህ የትህነግ ግልጽ አቋም በኢትዮጵያውያን ሉኣላዊነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። የአገሪቱ ሉዓላዊነትና አንድነት አደጋ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ዜጎች በሁለት አማራጮች መካከል እንዲቆሙ ተገደዋል።
አንደኛው የኢትዮጵያን አንድነትና የግዛት ታማኝነት ማስከበር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አገርን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ መተባበር ነው። በዚህ ረገድ “የኢትዮጵያ አንድነት ለድርድር አይቀርብም” የሚለው ድምፅ ከምንጊዜውም በላይ እየጠነከረ መጥቷል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ከትህነግ ጋር አላቸው ስለሚባለው ‘ስልታዊ ትብብር’ ተንታኞች ጠንካራ ትችት እያቀረቡ ነው። ትህነግ ግልጽ የሆነ አገር የማፍረስና የመገንጠል አጀንዳ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሁኔታ፣ ከዚህ ኃይል ጋር የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ትብብር ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ።
ይህ ትብብር በአጭር ጊዜ ያነጣጠረ ፖለቲካዊ ትርፍ ቢመስልም፣ በረጅም ጊዜ ግን የአማራን ሕዝብና የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ይገልጻሉ።
ተንታኞች አክለውም፣ በወሎ በኩል ከትህነግ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩት የፋኖ መሪዎች—እነ ምሬ ወዳጆ፣ ድርሳን ብርሃኔ፣ ሄኖክ አዲሴና አበበ ሙላት—ድርጊታቸው በሕግም ሆነ በሞራል የሚያስጠይቅ መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ ያሳስባሉ። “ከታሪካዊ ባላጋራ ጋር ተባብሮ አገርን ማፍረስ ለትውልድ የሚተርፍ ጠባሳ ነው” የሚሉት ተንታኞቹ፣ እነዚህ አመራሮች ከዚህ አደገኛ ጥምረት በአስቸኳይ እንዲወጡና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል፣ የአገር ውስጥ ልሂቃንና የፖለቲካ ድርጅቶች የትህነግን አዲስ አቋም በቀላሉ ሊመለከቱት እንደማይገባ ይመከራል። ድርጅቱ “ሉዓላዊነት የሪፈረንደም ጉዳይ አይደለም” ማለቱ፣ በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ ነው።
ይህ ደግሞ ማዕከላዊ መንግሥቱን ብቻ ሳይሆን፣ አጎራባች ክልሎችንና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለከፋ የደህንነት ስጋት የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ይነገራል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በውስጥና በውጭ ኃይሎች ብርቱ ፈተና እየደረሰባት ይገኛል። የትህነግ የ‘De facto state’ ፍላጎትና የፋኖ ታጣቂዎች ያልተገራ ትብብር አገሪቱን ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ሊከታት ይችላል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም የሕዝብ አመኔታ ያላቸው መሪዎች፣ ከጊዜያዊ የሥልጣንና የጥቅም ፉክክር ይልቅ ለአገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ዘብ መቆም ያለባቸው ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






