1.7 ቢሊዮን ብር ከዜጎች ላይ ዘርፈዋል የተባሉና ተባባሪዎቻቸው ክስ ተመሰረተባቸው፤ ተባባሪዎቹ መኪና ወስደዋል

Date:

አዲስ ሪፖርተር – በዜጎች ላይ የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ መመሥረቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ። ተባባሪዎቹ እስከ ስምስንት ሚሊዮን የሚያወጣ መኪና በስጦታ ወስደው ለዘረፋው ተባባሪ እንደሆነ ፖሊስ ማስረጃ አግኝቷል።

የፊንቴክ ኢንቨስትመንት የግል ድርጅት መስራችና ባለቤቶች የሆኑት ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገብረሚካኤል ይህደጎ የተባሉ ተጠርጣሪዎች፣ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመጠቀም ከ1,200 በላይ ዜጎችን በማጭበርበር የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረሳቸው ፖሊስ በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራውን አጣርቶ ለዓቃቤ ሕግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትባቸው ማድረጉን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነው።

መጀመሪያ ላይ ክሱ የቀረበው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የነበረ ቢሆንም፣ ወንጀሉ ውስብስብ፣ ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅና ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ምርመራው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በኩል በሰፊው ሲጣራ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪ ዳንኤል ዮሃንስ ክስ ተመስርቶበት በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል የተደረገ ሲሆን፣ ሌላኛው ተጠርጣሪ ግርማይ ገብረሚካኤልን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

ግርማይ ገብረሚካኤል በአውሮፓውያኑ 2010 የደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ወቅትም “አስካሉካን” በተባለ ድርጅት ስም ዜጎችን በማጭበርበር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ከሀገር ቢሰወርም፣ በወቅቱ በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዞ ለሕግ መቅረቡን የወንጀል ሪከርዱ ያመላክታል።

ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋለን በማለት የ950 ሺህ ብር (50%) ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙና ቀሪውን ገንዘብ ያለወለድ በ5 ዓመት በባንክ ብድር እንደሚጨርሱ በማሳመን ነው ወንጀሉን የፈጸሙት።

ሕዝብን ለማሳመን ሲሉ 148 መኪኖችን ከጅቡቲ በማስገባት 100ዎቹን ለተወሰኑ ሰዎች ማከፋፈላቸውንና ቀሪዎቹን 48 ዘመናዊ መኪኖች በድብቅ መሸጣቸውን ፖሊስ አረጋግጧል።

በተጨማሪም 350 መኪኖች ወደ ሀገር መግባታቸውንና 400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን የሚገልጽ የሐሰት መረጃ ለተጎጂዎች ሲሰጡ እንደነበር በምርመራው ተደርሶበታል።

ተጠርጣሪዎቹ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው የቻይናው BYD ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው በማስመስልና በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች በትውስት ያሰባሰቧቸውን መኪኖች ድርጅቱ ያስገባቸው በማስመሰል የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

በጅቡቲ “አልፋቲዞ” የተባለ ድርጅት በማቋቋም መኪኖቹን በ10% ቅድመ ክፍያ ተረክበው፣ ቀሪውን 90% ክፍያ ሳይፈጽሙ ጅቡቲ ላይ መልሰው መሸጣቸውም በምርመራው ተረጋግጧል።

ፖሊስ እንዳረጋገጠው ተጠርጣሪዎቹ ከእያንዳንዱ ተጎጂ ለቅድመ ክፍያ፣ ለመንግሥት ታክስና ለቻርጀር ማሰሪያ በሚል በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 365 ሺህ ብር ተቀብለዋል።

የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን ባልተገባና በተጋነነ መልኩ በማስተዋወቅ፣ በሕገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጋሪ በመሆን የተጠረጠሩት አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ አብርሃም ግዛው፣ ይገረም ደጀኔ፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስር በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ፍርድ ቤቱም በእነዚህ ግለሰቦች ላይ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። እነዚህ ግለሰቦች ዕውቅናቸውን በመጠቀም የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨትና እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የ”BYD Song Plus” መኪና በስጦታ በመቀበል ወንጀሉን በማሳለጥ ተጠርጥረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማጭበርበር፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ይህ ውስብስብ ወንጀል ተጣርቶ ክስ እንዲመሰረት ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሠራው የፍትሕ ሚኒስቴር እና መረጃ ሲሰጥ ለነበረው ማኅበረሰብ ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረቡን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ስብሰቡን “ሸፍጥ ይመስላል” ያሉት ዶ.ር ሚኒሊክ ከመጪው ቅዳሜ የአመጽ ጥሪ ምድብ ውጪ ሆኑ፤ የዲሲና ሎንዶን ሰላማዊ ሰልፍ ይሳካል?

አዲስ ሪፖርተር - በኢትዮጵያ ምርጫ እንዳይካሄድ ለመበጥበጥ የተቋቋመው ጥምር...

“ዓለም አቀፍ ጫና ሲደርስ ችግሩን መሻገር የሚቻለው ከምክንያት በላይ ኾኖ በመገኘት ነው” የኢኮኖሚ ምሁር

አዲስ ሪፖርተር - በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው ጦርነት በሀገራት ኢኮኖሚ...

የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ደህንነት ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ጥበቃ የወቅቱ ጥያቄ

አዲስ ሪፖርተር - በኢትዮጵያ በፍጥነት እየገሰገሰ የመጣውን የዲጂታል ፋይናንስ...

በመጨረሻ ሰዓት ራሳቸውን ከምርጫ ለማግለል ውጭ ካሉ ኃይሎች ጋር ውል ከገቡት መካከል አቋም የቀየሩ መኖራቸው ተሰማ

በመጪው ምርጫ በርካታ ተቃዋሚዎች በፓርላማና በክልል ምክር ቤቶች...