አዲስ ሪፖርተር — ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች እንዲፈቱ የሚያስችላቸው ሂደት እየተካሄደ መሆኑን ተከትሎ፣ የህዝባዊ አመጽ አዘጋጆች “አስቸኳይ ዘመቻ እንዲካሄድ” የሚል መመሪያ ማስተላለፋቸው ተሰማ። በይቅርታ ሰነዱ ላይ የፈረሙትን በማጣጣልና በከሃጂነት በመፈረጅ፣ “አንፈርምም” ያሉትን በማጀገን እንዲሰራ የታሰበው ፕሮፓጋንዳ ከወዲሁ የማሸማቀቅ ዓላማ ያለው እንደሆነ ተመልክቷል። እስረኞቹን ያነጋገሩ “በመስከረም ነጻ መሆን እንፈልጋለን” ማለታቸውን ተናግረዋል።
ዜናው በውስጥ መስመር የደረሳቸው የዜናው ባለቤቶች ለአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ እንዳሉት “እስረኞቹ ሰነዱ ላይ እንደተባለው ፈርመው ከተፈቱ ከምክክር ኮሚሽኑ ውሳኔ ጋር ተያያዞ የፖለቲካ ውድቀት ያስከትላል” የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።
በተለይም ተከሳሾቹ በየክስ መዝገባቸው የቀረበባቸውን የሽብር ወንጀል አምነው ኃላፊነት እንዲወስዱ፣ ለደረሰው የሰው ሕይወት ጉዳትና ንብረት መውደም፣ ራሳቸውን ተጠያቂ እንዲያደርጉ የሚጠይቀው ሰነድ፣ “ወደፊት ተመሳሳይ ድርጊት አልፈጽምም” የሚል መሃላ መያዙ ትግሉን እንደሚገድለው “የዲያስጶራ ታጋዮቹ” አመልክተዋል።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ” በየዕለቱ በፈጠራ ዜናዎችና በተዛቡ መረጃዎች ማሰነካከል” በሚል ዝግጅት ሁከት የተሞላበት በማስመሰል ለማቅረብ በተያዘው ዕቅድ መሰረት የጋራ መደረኩ አመራሮች ወደ አክቲቪዝም መመለሳቸውን ጠቅሰን ከውስጥ ያገኘነውን ዜና ይፋ ማድረጋችን ይታወሳል። ለዚሁም በጀት እንደተለቀቀ አመልክተን ነበር።
በተሰጠው አቅጣጫ፣ ልክ በሄራዊ የምክክር መደረኩ ላይ እንደሚደረገው ዓይነት “ማሸማቀቂያ” የተባለ ቅስቀሳ ይዘጋጃል። በተለይም ዋናዎቹን ጠቅሶ “የህዝብን ትግል የካዱ” እንደሚሆኑ በማሳየት የታሪክ ተጠያቂ አድረጎ መሳል የቅስቀሳው አካል ሲሆን፣ ይህ የሚሆነው “ሳንፈርም እንፈታ” በሚል ጠንካራ አቋም እንዲይዙና እስር ላይ እንዲቆዩ ማድረግ ነው።
በአማራ ስም የሚደረገው ትግል አሁን ላይ ባለበት ወቅታዊ ቁመና እስር ቤት ካሉት መካከል ያዘኑ፣ የተበሳጩና ከነሱ ጋር መቀጠል እንደማይቻል ያመለከቱ መኖራቸውን በተለያዩ ጊዜያት ከጎበኟቸው መካከል አንዱ የሆኑ ለአዲስ ሪፖርተር የአዲስ አበባ ዘጋቢ ገልጸዋል። የሰላም ጥሪ ተቀብለው መሳሪያ በማውረድ ወደ ሰላማዊ ትግል የተቀላቀሉት የቀድሞ የፋኖ አመራር እንዳሉት፣ እሳቸው ካገኟቸው መካከል “ስህተት ሰርተናል” ያሏቸው አሉ።
ሰላሳ የሚጠጉ ሲቀሩ የተቀሩት የይቅርታ ሰነዱ ላይ ፈርመዋል። እኚሁ የቀድሞ የፋኖ አመራር “እኔ እስከማውቀው ድረስ የፈረሙት እስረኞች ይቅርታ የጠየቁት አምነውበትና ፈልገው ነው” ሲሉ ያልፈረሙትን አስመልክቶ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ አመልክተዋል።
በአማራ ክልል ከተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ እና ግጭት ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል ተከሰሰው በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከሦስት ዓመታት በላይ በእስር ላይ የሚገኙ ከ300 በላይ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች እና የሕዝብ ተወካዮችን በይቅርታ እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በስፋት እየሰሩ መሆናቸው ቢገለጽም ኮሚሽኑ አስተባብሏል።
ለተከሳሾቹ የቀረበው የይቅርታ ሰነድ፣ ተከሳሾቹ ለተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ጉዳቶች እና የንብረት ውድመት ኃላፊነት እንዲወስዱ እና የተወሰኑ ፖለቲካዊ አቋሞችን እንዲያወግዙ የሚጠይቁ ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ እንደሆነ ጠቅሰው የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል። ሰነዱን እንዳገኘው ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ ሂደቱ በሕግ አተገባበር እና በተከሳሾች አቋም ምክንያት ሰፊ ልዩነት እያስተናገደ እንደሆነ ቢያመልክትም አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በሰነዱ ላይ መፈረማቸው ተርጋግጧል።
አዲስ ሪፖርተር ባደረገችው ማጣራት እስረኞቹ እንዲፈቱ ከመንግስት በኩል ፈቃደኛነቱ የተገለጸው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አባላት ከዓመት በፊት ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ዲፕሎማቶችም በተመሳሳይ ሲጠይቁ መንግስት ፈቃደኛ ነበር።
ፈቃደኛ ያልሆኑት ተከሳሾች “ጥፋተኛ ሳንሆን ወንጀለኛ ነን ብለን አንፈርምም” በማለት፣ መንግሥት ክሳቸውን አቋርጦ በፖለቲካዊ ምህረት እንዲፈታቸው እንደጠየቁ ተሰምቷል። ከላይ የተገለጸው የጋራ መድረክ እነዚህን ወገኖች በማጀገን እና ልዩ ክብር በመስጠት ለዚሁ ስራ የተቋቋሙ ሚዲያዎች እንዲያሞግሷቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።
“ከአገር ቤት የሚወጡ ዜናዎችን እየተከተልን ፕሮፓጋንዳ ስንሰራ ተመልሶ የሚጎዳን እኛኑ ነው። ስለዚህ ቀደም ተብሎ በተያዘው መስከረም ላይ አመጽ ለማነሳሳት አጥብቀን ብንሰራ ይሻላል” ያሉ መኖራቸውን ዜናውን ያጋሩን አመልክተዋል።
ቢቢሲ የጠየቃቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ ጥላሁን በሕጉ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 229 እና የይቅርታ አዋጅ 840/2006) መሠረት ይቅርታ መጠየቅም ሆነ መስጠት የሚቻለው በፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ወይም ቅጣት በተወሰነባቸው ሰዎች ላይ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።”በዚሁ የህግ አመክንዮ መሰረት ፍርድ ያላገኙት እነዚህ ተከሳሾች ሊፈቱ የሚችሉት በይቅርታ ሳይሆን፣ መንግሥት ክሳቸውን በማቋረጥ ወይም በምህረት (Amnesty) ነው” ብለዋል።
መንግስት ክሱን እንዲያነሳ በመካከል ሆነው ይህንን በሚያመቻቹ አካላት የቀረበው “የይቅርታ ሰነድ” ላይ በቀረበው አግባብ መሰረት ታሳሪዎቹ ይቅርታ ካልጠየቁ መንግስት ክሱን ሊያነሳ እንደማይችል ተመልክቷል።
በዚህ አመክንዮና ከላይ በቀረቡት ምክንያቶች መነሻነት በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረጉን ጨምሮ ከሁለት መቶ ሰባ በላይ ተከሳሾች፣ መንግሥት ያቀረበላቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ የምኅረት መጠየቂያ ሰነድ መፈረማቸውን ዋዜማ አስታውቋል። አዲስ ሪፖርተር ባላት መረጃ አሁን ላይ ከጥቂት ታሳሪዎች በቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ የቀረበውን የይቅርታ ሰነድ ፈርመው ለመጪው አዲስ ዓመት ነጻ መሆን የሚፈልጉ ሆነዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






